በአማኑኤል ይልቃል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአንድ ወር በፊት የመሬት ሊዝ ጨረታ ባካሄደባቸው ቦታዎች ላይ ተጫርተው አንደኛ ከወጡ አሸናፊዎች ውስጥ፤ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በተሰጣቸው ጊዜ ውስጥ ውል አለመፈጸማቸውን የከተማዋ መሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ። ቢሮው ውል ካልፈጸሙት አሸናፊዎች ውስጥ “የጨረታ ሂደቱን ለማዛባት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የተጫረቱ” ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ግምት እንዳለውም ገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ከአራት ዓመት በኋላ የተደረገውን የመሬት ሊዝ ጨረታ ያወጣው በግንቦት 2015 መጀመሪያ ላይ ነበር። በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ 297 ቦታዎች በቀረቡበት በዚህ ጨረታ፤ ተወዳዳሪዎች ለአንድ ካሬ ሜትር መሬት እስከ 700 ሺህ ብር በሚጠጋ የመወዳደሪያ ዋጋ ተጫርተዋል። የከተማይቱ ቢሮ በግንቦት ወር መጨረሻ የ287 ቦታዎች አሸናፊዎችን በለየበት ወቅት፤ ለአንድ ካሬ ሜትር 414 ሺህ ብር ካቀረቡ ተጫራች ከፍተኛው የማሸነፊያ ዋጋ መመዝገቡ ይፋ ተደርጓል።

የጨረታ አሸናፊዎቹን ዝርዝር ሰኔ 11፤ 2015 ያሳወቀው የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ፤ ተጫራቾች በአስር የስራ ቀናት ውስጥ በጨረታ ሰነዳቸው ላይ ያቀረቡትን ቅድመ ክፍያ ፈጽመው ውል እንዲያስሩ ጥሪ አቅርቦ ነበር። ሆኖም በተሰጣቸው ቀነ ገደብ ውስጥ ውል የፈጸሙት የጨረታ አሸናፊዎች 131 ያህሉ ብቻ መሆናቸውን የመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮው የለማ መሬት ማስተላለፍ ቡድን መሪ አቶ ሀብታሙ ተስፋዬ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የመሬት ጨረታ ሲወጣ “ሁሉም አሸናፊዎች ውል ይፈጽማሉ” ተብሎ እንደማይታሰብ የሚናገሩት አቶ ሀብታሙ፤ “ተጫርተው ቦታውን ለመውሰድ ሳይሆን በተለያየ ህገ ወጥ መንገድ [መሬት] ለመውረር ሲታሰብ ጨረታው ላይ ከፍተኛ ዋጋ ያስገባሉ” ሲሉ ከዚህ ቀደም በነበሩ ጨረታዎች የታዩ አካሄዶችን ያስረዳሉ። ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙት ተጫራቾች “አሉታዊ ተልዕኮ ይዘው” እንደሚንቀሳቀሱ የሚገልጹት የቡድን መሪው፤ ይህንን ከሚያደርጉበት ምክንያት ውስጥ አንዱ ጨረታ የሚደረግበት ቦታን “ይገባኛል” በማለት እንደሆነ ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አሸናፊዎች ውል ያልፈጸሙባቸው 156 ቦታዎችን በተመለከተ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ውሳኔ ማሳለፉን አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ለእነዚህ ቦታዎች በተካሄዱ ጨረታዎች ላይ ሁለተኛ የወጡ ተጫራቾች ከሐምሌ 3፤ 2015 ጀምሮ በአስር የስራ ቀናት ውስጥ ውል እንዲፈጽሙ ቢሮው ጥሪ ማቅረቡን የቡድን መሪው አስታውቀዋል።

“ሁለተኛ የወጣው ከፈለገ ቦታውን ይወስዳል። የሚወስደው ደግሞ፤ ሁለተኛ በራሱ [ባቀረበው] ዋጋ ሳይሆን አንደኛው ባሸነፈበት ዋጋ ነው” ሲሉ አሁንም ቢሆን አሸናፊዎች ያቀረቡት የአንድ ካሬ ዋጋ እና የቅድመ ክፍያ መጠን ተግባራዊ እንደሚሆን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል። ጨረታውን ካሸነፉ በኋላ ውል ያልፈጸሙ ተወዳዳሪዎች፤ በደንቡ መሰረት ጨረታውን ለማስከበር ለቢሮው ያስያዙት ገንዘብ እንደማይመስላቸውም አስረድተዋል።
በዚህ ጨረታ አሸናፊዎች ያቀረቡት የአንድ ካሬ የሊዝ ዋጋን ታሳቢ በማድረግ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከመሬት ሊዝ ጨረታው 12.2 ቢሊዮን ብር የማግኘት እቅድ እንደነበረው ከመሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል። ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 7.7 ቢሊዮን ብሩ ይገኛል ተብሎ የታቀደው፤ ተጫራቾች ቦታውን እንደተረከቡ ከሚፈጽሙት ቅድመ ክፍያ ነው። እስካሁን ውል ከፈጸሙ አሸናፊዎች ምን ያህል ገንዘብ እንደተገኘ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሀብታሙ፤ ገንዘቡ ተሰብስቦ ባለመጠናቀቁ “ይሄንን ያህል ነው” ብሎ መናገር እንደማይቻል ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)