በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ባለፉት 12 ወራት ከዚህ በፊት ያልነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች “መጠናቸው ሰፍቶ” እየታዩ መምጣታቸውን አስታወቀ። በሰብዓዊ መብት ረገድ በበጎ እርምጃ የሚታዩ ሁኔታዎች መኖራቸውን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ የሰዎች በህይወት የመኖር መብት፣ ሰላም እና ደህንነት ላይ “ትርጉም ያለው መሻሻል አልታየም” ብሏል።
መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም ይህን ያለው፤ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርቱን ትላንት ረቡዕ ሐምሌ 5፤ 2015 ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው። ለሁለተኛ ጊዜ የወጣው የኮሚሽኑ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት፤ ከሰኔ 2014 እስከ ሰኔ 2015 ያለውን ጊዜ የሸፈነው ነው። በሶስት ክፍሎች የተዋቀረው ይህ ሪፖርት፤ በተጠቀሱት 12 ወራት መሻሻል ያሳዩ እና “አሳሳቢነታቸው የቀጠሉ” የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎችን በዝርዝር አስፍሯል።
የሪፖርቱ የመጀመሪያ ክፍል መሰረታዊ መረጃዎች፣ የመረጃ አሰባሰብ ስነ-ዘዴ እና ኮሚሽኑ በህግ የተሰጡትን ኃላፊነቶች የሚያብራራ ነው። የሪፖርቱን አብዛኛው ድርሻ የሚይዘው ሁለተኛው ክፍል ደግሞ ባለፉት 12 ወራት መሻሻል ያሳዩ እና አሳሳቢነታቸው የቀጠሉ የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎችን በዝረዝር ያትታል። ሶስተኛው እና የመጨረሻ የሪፖርቱ ክፍል ቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን እና ምክረ ሃሳቦች የያዘ ነው።
ኢሰመኮ መሻሻል አሳይተዋል በሚል ከጠቀሳቸው ጉዳዮች መካከል አንደኛው፤ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በፌደራል መንግስቱ እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ነው። በጦርነት ወቅት በተጎዱ “አብዛኛው” አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት “አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት” መስፈኑ፤ በኮሚሽኑ ሪፖርት በበጎ እርምጃነት ተነስቷል። የመልሶ ግንባታ ጅማሮ፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መሻሻል፣ የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አማራጭ ሰነድ መዘጋጀቱ እና ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶች “መሻሻል አሳይተዋል” በሚል የተነሱ ሌሎች ጉዳዮች ናቸው።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ እነዚህ ጉዳዮች ባለፉት 12 ወራት ከተመዘገቡ መልካም እርምጃዎች “ዋነኛ” እና “በአንጻራዊ የሰብዓዊ መብቶችን በማሻሻል ረገድ ሰፊውን ድርሻ የሚይዙ” መሆናቸውን በትላትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል። በማረሚያ ቤቶች ያለው የታራሚዎች አያያዝ ላይ እንዲሁም በመሰረተ ልማት እና አገልግሎት አቅርቦት ላይም መሻሻሎች እንደታዩ ኢሰመኮ በዓመታዊ ሪፖርቱ ገልጿል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ መሻሻል አሳይተዋል በሚል ከጠቀሳቸው ጉዳዮች በማስከተል፤ “አሳሳቢነታቸው ቀጥሏል” ያላቸውን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታም በስፋት ዳስሷል። ከሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ጋር በተያያዘ ባለፉት 12 ወራት “ወደ ኋላ የመንሸራተት አደጋዎች፣ ስጋቶችም ደግሞ ተመልክተናል” ያሉት ዶ/ር ዳንኤል፤ “ከዚህ በፊት ያልነበሩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየታዩ መጥተዋል። መጠናቸው ሰፍቷል። አሳሳቢነታቸው ጨምሯል” ሲሉ አብራርተዋል።
ዶ/ር ዳንኤል “አሳሳቢነታቸው ጨምሯል” በሚል ከገለጿቸው የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎች መካከል፤ “የሰዎች በህይወት የመኖር መብት” እንዲሁም “በሰላም እና ደህንነት” ረገድ ያለው ሁኔታ ነው። በአማራ እና የትግራይ ክልሎች ከጥቅምት ወር ጀምሮ “ሰላም እና መረጋጋት የታየ ቢሆንም”፤ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች “በቀጠሉ ግጭቶች፤ “ሲቪል ሰዎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለሥነ ልቦና ጉዳት፣ ለመፈናቀል እና ለንብረት ውድመት ተዳርገዋል” ሲል የኮሚሽኑ ሪፖርት ያትታል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር “ቀዳሚ የሆነው የሰዎች በህይወት የመኖር መብት፣ ሰላም እና ደህንነት [ላይ] ትርጉም ያለው መሻሻል አልታየም” ሲሉ በተቋማቸው ሪፖርት ላይ የሰፈረውን ሃሳብ በመግለጫቸው አጠናክረዋል።
ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት በህይወት የመኖር መብት ጋር በተያያዘ ተፈጸሙ ያላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በጊዜ እና በቦታ በዝርዝር አስፍሯል። ሪፖርቱ በኦሮሚያ ክልል አስራ ሁለት ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች የሚደርሱ ግጭቶች እና ጥቃቶች “አሳሳቢ እና ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ” መሆናቸውንም አመላክቷል። በኦሮሚያ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑት ጥቃቶች በክልሉ “በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች” እና “በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች” የሚፈጸሙ መሆናቸውን ሪፖርቱ አስታውቋል።
ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በሚገኙ ዘጠኝ ቀበሌዎች ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር “በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች” ላይ በተፈጸመ ጥቃት “ከ60 በላይ” ሰዎች መገደላቸውን በሪፖርቱ ጠቅሷል። በተመሳሳይ በምስራቅ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዮ ወረዳ ከስድስት ወራት በፊት የከተማ ፖሊስ እና የቀበሌ ሚሊሺያ አባላትን ጨምሮ 50 ሰዎች መገደላቸው በሪፖርቱ ሰፍሯል። ጥቃቱን ያደረሱት “የወታደር ልብስ የለበሱ የኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎች መሆናቸው ነዋሪዎች መናገራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ከኦሮሚያ ክልል ባሻገር በአማራ ክልልም ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ክስተቶች በኮሚሽኑ ሪፖርት ቀርበዋል። በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን በደብረ ኤልያስ ወረዳ በሚገኝ ገዳም፤ “የጸጥታ አካላት” ወስደውታል በተባለ “የኃይል እርምጃ” ከ15 ሰዎች በላይ መገደላቸው በሪፖርቱ ተካትቷል። በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች “ሰፋ ያለ የመብት ጥሰቶች” መከሰታቸውን ዶ/ር ዳንኤል በትላንቱ መግለጫቸው ተናግረዋል።
ከሁለቱ ክልሎች በተጨማሪ በሲዳማ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ደቡብ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ለሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት የሆኑ ጥቃቶች መድረሳቸው በኢሰመኮ ሪፖርት ይፋ ተደርጓል። ታጣቂዎች እና የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች “ይፈጽሟቸዋል” ከተባሉ ጥቃቶች ሌላ በክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ላይ የሚከሰቱ ግጭቶችም ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት መሆናቸውን ኮሚሽኑ ጠቁሟል።
ኢሰመኮ “አሳሳቢነታቸው ቀጥሏል” በሚል ከዘረዘራቸው ጉዳዮች ውስጥ፤ “በግዳጅ መሰወርን” የሚመለከተው ይገኝበታል። የኮሚሽኑ ሪፖርት ይህን ጉዳይ ሲያብራራ፤ “በተለምዶ ‘ወቅታዊ ሁኔታ’ በመባል በሚታወቁ ምክንያቶች ሳቢያ፤ ሰዎች ለዘፈቀደ እስር እንዲሁም ለአስገድዶ መሰወር የተዳረጉበት በርካታ ክስተቶች ተመዝግበዋል” ይላል። ለአስገድዶ መሰወር ከተዳረጉ ሰዎች መካከል “በርካቶች ፍርድ ቤት አይቀርቡም። አሊያም ከተራዘመ እስር በኋላ የሚቀርቡ ናቸው” ሲል ሪፖርቱ አክሏል።
ለአስገድዶ መሰወር የሚዳረጉ ሰዎች የሚያዙት ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከስራ ቦታ ወይም ከመንገድ ላይ መሆኑን የኮሚሽኑ ሪፖርት ይጠቅሳል። እነዚህ ሰዎች የሚያዙት “የሲቪል እና የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግስት ጸጥታ እና ደህንነት ሰራተኞች” መሆኑን ኢሰመኮ በሪፖርቱ አስታውቋል። ሰዎቹ “ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ከታሰሩ በኋላ ወዳልታወቀ ስፍራ እንዲሰወሩ” መደረጉን የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር በትላንቱ መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት አባልነት መያዛቸው የተገለጸ ሰዎች “ከመደበኛ ማቆያ ቦታዎች ውጭ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ የሚታሰሩ መሆኑን” ኢሰመኮ በሪፖርቱ በተጨማሪነት አመልክቷል። በዚሁ የኮሚሽኑ ዓመታዊ ሪፖርት፤ በአዲስ አበባ ከተማ እንዲሁም በኦሮሚያ፣ አማራ እና ሶማሌ ክልሎች ተፈጸሙ ያላቸውን የአስገድዶ መሰወር ድርጊቶች ተዘርዝረው ተቀምጠዋል።
ኢሰመኮ “በአሳሳቢነት” ከጠቀሳቸው የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎች ውስጥ፤ የፖለቲካ መብቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጥሰት የዳሰሰው አንዱ ነው። የኮሚሽኑ ሪፖርቱ በሸፈናቸው ወራት፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና አመራሮች ላይ የሚፈጸሙ እስሮች፣ ወከባዎች እና ሌሎች እንግልቶች መጨመራቸው ተገልጿል። “ሰፋ ባለ መልኩ ሲታይ ደግሞ የሲቪክ ምህዳሩን በተመለከተ በርካታ አሳሳቢ ክስተቶች ተመዝግበዋል” ሲል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ አስታውቋል።
“ከጭካኔ፣ ኢ-ሰብዓዊና አዋራጅ አያያዝ እና ቅጣት ነጻ የመሆን መብትም” በተመሳሳይ አሳሳቢነቱ የቀጠለ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል። ኮሚሽኑ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች፤ የተጠረጠሩበትን ወንጀል እንዲያምኑ “ድብደባ እና ግርፋትን ጨምሮ ሌሎች ኢ-ሰብዓዊ እና አዋራጅ ተግባራት” እንደተፈጸሙባቸው በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። ኢሰመኮ እነዚህ ተግባራት ይፈጸማሉ ያለው “በእስር ቤቶች እና መደበኛ ባልሆኑ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ቦታዎች” ውስጥ ነው።
ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ላይ የሚጣል ገደብም በተመሳሳይ “አሳሳቢነቱ ቀጥሏል” በሚል በኮሚሽኑ ሪፖርት ተነስቷል። “የሰዓት እላፊ ገደብ በመጣል እና መስፈርቶችን በማስቀመጥ፤ በመንቀሳቀስ መብት ላይ የተደረጉ በርካታ ገደቦች በዘንድሮ በጀት ዓመት ተመዝግበዋል” ብሏል ኢሰመኮ። በኮሚሽኑ ለዚህ በማሳያነት ካነሳቸው ውስጥ “ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች ላይ ተደርጓል” የተባለው ገደብ ይገኝበታል። በሸኖ ከተማ “ከአማራ ክልል የሚመጡ ሰዎችን አስሮ ማቆየት እንዲሁም ወደመጡበት ስፍራ ያለ ፍላጎታቸው እንዲመለሱ በማድረግ የመዘዋወር ነጻነታቸው ተገድቧል” ሲል ኢሰመኮ ጉዳዩን አብራርቷል።
ኢሰመኮ በሪፖርቱ ሶስተኛ እና መጨረሻ ክፍል ላይ ክትትል የሚሹ ያላቸውን ጉዳዮች እና ምክረ ሃሳቡን አቅርቧል። ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች “በሲቪል ሰዎች ላይ” እየደረሰ ነው ያለውን “ግድያና አካል ጉዳት” በተመለከተ ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል። ይህን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል “መጠነ ሰፊ ምርመራን” እንዲያደርግ የጠየቀው ኢሰመኮ፤ የፌደራል እና የክልሉ መንግስት “አፋጣኝ እርምጃ እና ተጨባጭ ዘላቂ መፍትሔ መዘርጋት አለባቸው” ሲል አሳስቧል።
ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ላይ “እጅግ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚኖራቸው” ተብለው የተጠቀሱትን ተግባራት “መንግስት በአፋጣኝ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ሊያስቆመው የሚገባ ነው” ብሏል። ኮሚሽኑ “አሉታዊ ተጽዕኖ የሚኖራቸው” በሚል የዘረዘራቸው ተግባራት፤ አስገድዶ መሰወር፣ የጭካኔ፣ አዋራጅ እና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ መጨመር፣ የኢ-መደበኛ ማቆያዎች መበራከት፣ እንዲሁም የዘፈቀደ እስሮች ናቸው።
ዋና ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በትላንቱ መግለጫው “በዘንድሮው በጀት ዓመት በተለይ ከሰላም ስምምነቱ እና ከሽግግር ፍትህ ሂደቱ በተጨማሪ ሀገራዊውን የሰብዓዊ መብቶችን ሁኔታ ሰፋ ባለ መልኩ የሚያሻሻል ለውጥ እምብዛም አለመኖሩ እና አልፎ አልፎ ከሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ አንጻር ወደ ኋላ የመንሸራተት አደጋ ምልክቶች መታየታቸው፤ ለተስፋ መቁረጥ እና ከሚደረጉ ጥረቶች ለማፈግፈግ ምክንያት ሊሆኑ አይገባም ብለን ለማስታወስ እንወዳለን” ሲሉ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)