በሃሚድ አወል
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ፣ ባለፈው ሳምንት አርብ ሰኔ 30 በታጣቂዎች በተሰነዘረ ጥቃት፤ ሶስት የአካባቢ ሚሊሺያዎችን ጨምሮ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። ሌሎች 16 ሰዎች ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና ላይ መሆናቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ ገልጿል።
ኢሰመኮ በታጣቂዎች ጥቃት የሰዎች ህይወት መጥፋት እና አካል ጉዳት መድረሱን የገለጸው፤ ትላንት ሐሙስ ሐምሌ 6፤ 2015 ምሽት ባወጣው መግለጫ ነው። ጥቃቱ የተፈጸመው በግልገል በለስ ከተማ በተለምዶ “ቻይና ካምፕ” ተብሎ በሚጠራው ስፍራ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ከጥቃቱ በኋላ “በርካታ ነዋሪዎች” አካባቢውን ለቅቀው መሸሻቸውን ጠቁሟል።
በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው “ከጉሙዝ ብሔር ውጭ ያሉ ሌሎች ብሔሮች” እና “በተለምዶ ቀዮች” ተብለው የሚታወቁ ነዋሪዎች መሆናቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው አመልክቷል። ኮሚሽኑ ከጥቃቱ በኋላ አደረግኩት ባለው ክትትል፤ ድርጊቱን የፈጸሙት “ከመንግሥት ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት ትጥቅ ለማስፈታት በሚል አንድ ካምፕ ውስጥ እንዲሰፍሩ የተደረጉ የጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉህዴን) ታጣቂ ቡድን አባላት” መሆናቸውን እንደደረሰበት ገልጿል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ከጉህዴን ታጣቂዎች ጋር ስምምነት ከፈጸመ በኋላ፤ ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ጥቃቶች ሲደርሱበት በቆየው መተከል ዞን አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖ ነበር። ኢሰመኮም በትላንቱ መግለጫው፤ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ከሶስት ሺህ በላይ ታጣቂዎች እና “ጫካ ገብተው” የነበሩ ከ68 ሺህ በላይ የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላት ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለሳቸውን አስታውሷል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ከጉህዴን ሊቀመንበር አቶ ግራኝ ጉደታ ጋር የተፈራረሙት ስምምነት፤ “በሰላማዊ መንገድ የገቡ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ፈትተው ያስመዝገባሉ” ሲል ያትታል። በታጣቂዎች ተይዞ የነበረው የጦር መሳሪያ “ወደ መንግስት ካዝና ተመላሽ እንደሚደረግ” እና “ህጋዊ ሚሊሺያዎች እና ግለሰቦች” እንደሚታጠቁትም በስምምነቱ ላይ ሰፍሯል።
ስምምነቱ ይህን ቢልም ኢሰመኮ ትላንት ያወጣው መግለጫ ግን “የሰላም ተመላሽ” የሚባሉት ታጣቂዎች፤ ትጥቃቸውን አለመፍታታቸውን ያመላክታል። መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተቋም በዚሁ መግለጫው፤ “የታጣቂ ቡድኑ አባላት በከተማዋ ከነመሳሪያቸው ሲንቀሳቀሱ የሚታዩ” መሆኑን ገልጿል። በተጨማሪም “በከተማዋ የሚገኙ የምግብ ቤት እና ሌሎች አገልግሎቶችን ሳይከፍሉ ወይም አገልግሎት ሰጪዎችን በማስገደድ በነጻ የሚጠቀሙ” መሆኑን ከአካባቢው ነዋሪዎች መረዳቱን ኢሰመኮ ጠቅሷል። “ከነዋሪዎች በግዳጅ ገንዘብ የሚሰበስቡ የቡድኑ አባላት” እንዳሉም የኮሚሽኑ መግለጫ ጠቁሟል።
ኢሰመኮ የአካባቢውን ነዋሪዎች እና የአስተዳደር ኃላፊዎች በማናገር “ጥቃቱን ያደረሱት የጉህዴን ታጣቂዎች ናቸው” ይበል እንጂ፤ የጉህዴን ምክትል ሊቀመንበር አቶ ደርጉ ፈረንጅ ግን “እነሱ እንደሚያወሩት አይደለም” ሲሉ የኮሚሽኑን መግለጫ ተቃውመዋል። የጉህዴን ታጣቂ ተብለው የሚጠሩት ታጣቂዎች “ትጥቃቸውን እንዲፈትቱ አድርገናል” የሚሉት አቶ ደርጉ፤ በሌሎች የመተከል ዞኖች የገቡ የንቅናቄው ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
አቶ ደርጉ የጉህዴን ታጣቂዎች “ትጥቅ ፈትተው ወደ ሰላማዊ ህይወት ገብተውባቸዋል” ያሏቸውን፤ ማንዱራ፣ ድባጤ፣ ዳንጉር፣ ቡለን እና ወንበራ ወረዳዎችን ለአብነት ጠቅሰዋል። በመተከል ዋና ከተማ ግልገል በለስ የሚገኙት ታጣቂዎች፤ “ከእኛ ተነጥለው ‘የጉህዴን ስምምነት አይወክለንም፤ አይመለከተንም’ ብለዋል። የጉህዴን አይደሉም” ሲሉ አቶ ደርጉ በንቅናቄያቸው ላይ የቀረበውን ውንጀላ አጣጥለውታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)