የቀድሞው የብአዴን ከፍተኛ አመራር አቶ ታደሰ ካሳ በነጻ ከእስር እንዲለቀቁ በፍርድ ቤት ተወሰነላቸው  

በአማኑኤል ይልቃል

 ከተፈረደባቸው ስምንት ዓመት ከአምስት ዓመት ወር እስር ውስጥ ግማሽ ያህሉን ያጠናቀቁት የቀድሞው የብሔር አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ከፍተኛ አመራር አቶ ታደሰ ካሳ፤ ከእስር እንዲፈቱ የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ አስተላለፈ። የሰበር ሰሚ ችሎቱ ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው፤ የአማራ ክልል ጠቅላይ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እንዲሁም የክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጧቸውን ውሳኔዎች በመሻር ነው። 

ከሌላኛው የብአዴን ጎምቱ ፖለቲከኛ አቶ በረከት ስምኦን ጋር በቀረበባቸው ክስ ተፈርዶባቸው የነበሩት አቶ ታደሰ፤ ከቀረበባቸው ክስ ነጻ ያደረጋቸው ውሳኔ በፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት የተላለፈው ትላንት ሐሙስ ሐምሌ 6፤ 2015 እንደሆነ ጠበቃቸው ህይወት ሊላይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሰበር ሰሚ ችሎቱ በትላንትናው ዕለት ውሳኔ ለመስጠት ቀጥሮ የነበረው፤ አቶ ታደሰ ለችሎቱ ያቀረቡትን ቅሬታ ሲመረምር ከቆየ በኋላ መሆኑን ጠበቃቸው ገልጸዋል።  

አቶ ታደሰ በ2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የቀረበባቸው፤ በስራ አስፈጻሚነት ሲመሩት ከነበረው ጥረት ኮርፖሬት ጋር በተያያዘ ነው። ከቀድሞው የአማራ ክልል ገዢ ፓርቲ ብአዴን ጋር ግንኙነት የነበረው ጥረት ኮርፖሬት፤ “በቂ ጥናት ሳይደረግ ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር ለመስራት ውል ገብቷል። በዚህም ድርጅቱ ጉዳት ደርሶበታል” በሚል ነበር አቶ ታደሰ የተከሰሱት።

ከህዳር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተጠሪነቱ ለአማራ ክልል ምክር ቤት እንዲሆን የተደረገው ጥረት ኮርፖሬት፤ ዳሸን ቢራ ፋብሪካ፣ አምባሰል የንግድ ስራዎች የመሳሰሉ ተቋማትን እና በእርሻና የመጓጓዣው ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎችን የሚያስተዳድር ነው። በቀረበባቸው ክስ በግንቦት 2012 ዓ.ም ጥፋተኛ የተባሉት አቶ ታደሰ፤ የአማራ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንት ዓመት ከአምስት ወራት እስር እንዲሁም የ15 ሺህ ብር ቅጣት አስተላለፎባቸዋል።  

ይህ ቅጣት ከተላለፈ በኋላ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ሰበር ሰሚ ችሎት ይግባኝ መጠየቁን የሚያስረዱት የአቶ ታደሰ ጠበቃ፤ በሁለቱም እርከኖች አቤቱታው ውድቅ መደረጉን ገልጸዋል። ይህንን ተከትሎም ጉዳዩን ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ወስደው አቤቱታ ማቅረባቸውን አስረድተዋል። በ2014 ዓ.ም መጀመሪያ አቤቱታውን የተቀበለው የፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎትም፤ “መስተካከል አለባቸው ያላቸውን ነጥቦች ጠቅሶ ወደ ክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት” ጉዳዩን መመለሱን ጠበቃ ህይወት አብራርተዋል። 

የአማራ ክልል ሰበር ሰሚ ችሎት በድጋሚ ጥያቄውን ውድቅ በማድረጉ፤ ጉዳዩ በዚህ ዓመት የካቲት ወር ላይ ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በድጋሚ ተመልሶ ክርክር ሲደረግበት መቆየቱንም አስታውሰዋል። ይህ ክርክር በዋነኛነት በሁለት ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር የሚናገሩት ህይወት፤ አንደኛው መከራከሪያ የአማራ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት “ጉዳዩን ለማየት የሚያስችል ስልጣን የለውም” የሚል እንደሆነ ጠቅሰዋል።

“[በመዝገቡ ላይ] አብረው የተከሰሱ የውጭ ሀገር ዜጎች አሉ። የውጭ ሀገር ዜጋ ጉዳይ በፌደራል ፍርድ ቤት ብቻ ነው የሚታየው” ሲሉ በመከራከሪያቸው ላይ ከቀረቡት ሀሳቦች መካከል የአንዱን ጭብጥ አስረድተዋል። በፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታውን በመቃወም የቀረቡት የአማራ ክልል ዐቃብያነ ህግ በበኩላቸው፤ ጉዳዩን የክልሉ ፍርድ ቤት ለማየት ስልጣን ያለው መሆኑን ጠቅሰው መከራከራቸውን ጠበቃዋ አክለዋል።

በፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ክርክር የተደረገበት ሌላኛው ጉዳይ “አቶ ታደሰ ፈጽመውታል የተባለው የሙስና ወንጀል የተከናወነው፤ በክሱ ላይ የተጠቀሰው የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ነው” የሚል መሆኑን ጠበቃዋ አስረድተዋል። አቶ ታደሰ የተከሰሱበት የሙስና ወንጀሎች አዋጅ በ2007 ዓ.ም የወጣ ነው። የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ዐቃብያነ ህግ “ድርጊቱ ከአዋጁ በፊት የተፈጸመ መሆኑን ክደው አልተከራከሩም” የሚሉት ጠበቃዋ ህይወት፤ ይሁንና “ድርጊቱ ቀጣይነት አለው” የሚል መከራከሪያ ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

በጽሁፍ እና በቃል የተደረጉትን እነዚህን ክርክሮች ሲመለከት የቆየው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በትላንትናው ዕለት ባሳለፈው ውሳኔ፤ በተከሳሽ ላይ በተሰጠው ፍርድ ላይ “የህግ ስህተት ተፈጽሟል” ማለቱን ጠበቃዋ ጠቅሰዋል። በዚህም መሰረት ችሎቱ፤ “ከአማራ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጀምሮ የነበሩ ውሳኔዎች ሙሉ በሙሉ እንዲሻሩ አድርጎ፤ ከእስር እንዲፈቱ በማለት ትላንትና በነጻ አሰናብቶናል” ሲሉ ጠበቃ ህይወት የተሰጠውን ውሳኔ አስረድተዋል።

ላለፈው አራት ዓመት ከስድስት ወር ገደማ በእስር ላይ የቆዩት አቶ ታደሰ፤ አብዛኛውን የእስር ጊዜያቸውን ያሳለፉት በባህር ዳር ማረሚያ ቤት ነው። አቶ ታደሰ ከጥር 2014 ዓ.ም ጀምሮ በህክምና ምክንያት ወደ አዲስ አበባው ቃሊቲ ማረሚያ ቤት መዛወራቸው ይታወሳል። የትላንትናው የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት የፍቺ ትዕዛዝ የተላለፈው ለሁለቱም ማረሚያ ቤቶች መሆኑን የአቶ ታደሰ ጠበቃ ተናግረዋል። “ትዕዛዙ እንደደረሰ ከእስር ይለቀቃል ብለን እናምናለን” ያሉት ህይወት፤ ቀጣዮቹ ቅዳሜ እና እሁድ የእረፍት ቀናት በመሆናቸው በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ  ደንበኛቸው ተፈትተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ይቀላቀላሉ ብለው እንደሚጠብቁ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል፡፡

ከጥረት ኮርፖሬት ጋር በተያያዘ ከአቶ ታደሰ ጋር በአንድ መዝገብ ተከሰው የነበሩት አቶ በረከት ስምኦን፤ ከአራት አመት እስር በኋላ ከስድስት ወር በፊት በጥር ላይ መፈታታቸው ይታወሳል፡፡ የስድስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው የነበሩት አቶ በረከት፤ ከእስር የተፈቱት “የአመክሮ ጊዜያቸውን አጠናቀው” ነው፡፡ የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት በአቶ ታደሰ ጉዳይ ላይ የሰጠውን ውሳኔ አስመልክቶ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር”፤ ከአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ እና ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)