የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች የማለፊያ ነጥብ ያስመዘገቡት 40 በመቶ ብቻ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ

በአማኑኤል ይልቃል

የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናን ከወሰዱ 150 ሺህ ገደማ ተማሪዎች ውስጥ ያለፉት 40.6 በመቶ ብቻ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካስፈተኗቸው ተማሪዎች ውስጥ የማለፊያ ውጤት ያስመዘገቡት 17.23 ብቻ መሆናቸውንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ያስታወቀው ትላንት አርብ የተጠናቀቀውን የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና አፈጻጸም አስመልክቶ ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 8፤ 2015 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ መሰጠት የተጀመረውን የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና፤ ተማሪዎች ከባለፈው ሳምንት ሰኔ 30 እስከ ትላንት አርብ ሐምሌ 7 ደረስ ሲወስዱ ቆይተዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ዓመት “240 ሺህ ገደማ ተማሪዎች ፈተናውን ይወስዳሉ” ብሎ ግምት ቢያስቀምጥም፤ ለመፈተን ብቁ ሆነው የተመዘገቡት 194 ሺህ መሆናቸውን የዛሬውን መግለጫውን የሰጡት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ተናግረዋል። ከተመዘገቡት ተማሪዎች ውስጥ ለፈተና የተቀመጡት ደግሞ 150,184 መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

በትክክል ፈተናውን የወሰዱ ተማሪዎች ቁጥር ከተጠበቀው አንጸር በ100 ሺህ ገደማ መቀነሱ፤ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል በተፈጠረ “ጉድለት” የመጣ አለመሆኑን ዶ/ር ሳሙኤል ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። “ምናልባት ያላቸውን ዝግጅት አይተው፤ በዚህ ጊዜ መፈተኑን ለሌላ ጊዜ አስተላልፈው ነው ብለን እንወስዳለን” ሲሉ ከተመዘገቡ በኋላ ለፈተና ያልተቀመጡ ተማሪዎችን በተመለከተ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። 

ዶ/ር ሳሙኤል በዛሬው መግለጫቸው፤ የመውጫ ፈተና የማለፊያ ነጥብ እንደሌሎች አገር አቀፍ ፈተናዎች ሁሉ 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ መሆኑን አመልክተዋል። በዚህም መሰረት ፈተናውን ከወሰዱት አጠቃላይ ተማሪዎች ውስጥ የማለፊያ ውጤት ያመጡት፤ 40.65 በመቶው መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ዛሬ ይፋ የተደረገው የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፤ 78 ሺህ ገደማ ተማሪዎችን ያስፈተኑት የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች 62.37 በመቶ ተፈታኞቻቸው አልፈዋል። ሰባ ሁለት ሺህ ገደማ ተማሪዎችን ለፈተናው ያስቀመጡት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በበኩላቸው ያሳለፉት 12,422 ተፈታኞችን ብቻ ነው። ይህም ፈተናውን ከወሰዱ የግል ተቋማት ተማሪዎች ውስጥ 17.2 በመቶ የሚሸፍን ነው። 

የዘንድሮውን የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና ያለፉ ተማሪዎች 40 በመቶ ገደማ መሆናቸው፤ ትምህርት ሚኒስቴር ከገመተው አንጻር እንዴት እንደሚመለከቱት ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ሳሙኤል “ከነበረው ስጋት አንጻር 40 ከመቶ ተማሪ በመጀመሪያው ዙር በማለፉ በጣም የሚያስደንግጥ ውጤት ነው ብዬ አልወሰድኩም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ይሁንና ፈተናውን ያለፉ ተማሪዎች ብዛት ትምህርት ሚኒስቴር ከጠበቀው አንጻር “ትንሽ ዝቅ ያለ” መሆኑን አልሸሸጉም።

የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተናውን ከወሰዱ አጠቃላይ ተማሪዎች ውስጥ 59.3 በመቶው ለመውደቃቸው “አንድ ብቸኛ ምክንያት” እንደሌለ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ምክንያቶቹን ለማወቅ “ዝርዝር የውጤት ትንተና” እንደሚሰራ ተናግረዋል። የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሳለፏቸው ተማሪዎች ብዛት፤ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ካሳለፏቸው አንጻር ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑን በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር ምን አይነት ግምገማ እንዳለው ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለቀረበላቸው ጥያቄ ግን “ቀድሞም ግምት” የነበረ መሆኑን አስረድተዋል። 

በግል እና በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ያለው የማለፍ ምጣኔ ከፍተኛ ልዩነት ያለው መሆኑ፤ ቀድሞም የነበረውን “መላምት (hypothesis) የሳተ አለመሆኑን” ዶ/ር ሳሙኤል አክለዋል። “ ‘በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው አፈጻጸም ትኩረት ይፈልጋል። አንዳንድ ተቋማት የትምህርት ማስረጃ እየሸጡ እንጂ ተማሪ እያበቁ አይደለም’ የሚል ሀሜት ነበር። አሁን በተወሰነ ደረጃ ወደ እውነት እየተቀየረ ያለ ነው” ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል። 

ይህም ቢሆን ከ80 በመቶ በላይ ተማሪዎቻቸውን ያሳለፉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መኖራቸውን በመጥቀስ፤ “ችግሩን ሁሉንም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመለከት አለመሆኑን” ዶ/ር ሳሙኤል ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ከግልም ይሁን ከመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፤ አንድም ተማሪ ሳያሳልፍ የቀረ የትምህርት ተቋም አለመኖሩንም ጠቅሰዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተናን በየስድስት ወሩ እንደሚያዘጋጅ በዛሬው መግለጫ ላይ ተነግሯል። የአሁኑን የመውጫ ፈተና ያላለፉ ተማሪዎች፤ በ2016 ዓ.ም ጥር ወር ላይ በሚዘጋጀው ሌላ ፈተና መፈተን እንደሚችሉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]