“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢሮ ውስጥ የተፈፀመውን ዘረፋ በተመለከተ ከሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን የተሰጠ መግለጫ

በሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ሥር የሚተዳደረው “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የበይነመረብ ሚዲያ እሁድ፣ ሐምሌ 9፣ 2015 ለሰኞ አጥቢያ በቢሮው ውስጥ ያለ ካዝና ባልታወቁ አካላት ተሰብሮ፣ ንብረቱ ተዘርፏል። የሚዲያ ተቋሙ በሚሠራቸው ዘገባዎች ሳቢያ ተደጋጋሚ ጫናዎች እየደረሰበት ሲሆን፣ ይህ ዘረፋም የነዚህ ተደራራቢ ጫናዎች ተቀጥያ እንደሆነ ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ያምናል። 

ትላንት እሁድ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ባልደረቦች እስከ ቀኑ 10፡00 ሰዓት በዜና ክፍሉ ውስጥ በሥራ ላይ ቆይተው፣ ቢሮውን ቆልፈው ከወጡ በኋላ፣ ዛሬ ጠዋት 1፡00 ሰዓት ገደማ ቀድመው የደረሱ ባልደረቦች የቢሮው በር እንደተቆለፈ ነገር ግን ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ የዜና ክፍሉ ንብረቶች የተቀመጡበት ካዝና በኃይል ተሰብሮ አግኝተውታል። 

በዘረፋው ካዝናው ውስጥ የነበሩ ሦስት አዳዲስ እና ዘመናዊ ዲጂታል ካሜራዎች፣ ሁለት ዙም ሌንሶች፣ ሌሎች አራት መደበኛ ሌንሶች፣ አራት ላፕቶፖች እና አንድ ስማርት የሞባይል ስልክ ተወስደዋል። ሐቅ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘረፋውን ቦሌ ክፍለ ከተማ ለሚገኘው ለአደይ አበባ ስታዲየም አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ያመለከተ ሲሆን፣ የጣቢያው ፖሊሶች በ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢሮ በመገኘት አሻራ አንስተው፣ የተወሰኑ ባልደረቦችን ቃል ተቀብለዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተመሳሳይ ዘረፋዎች በአስቸጋሪው የኢትዮጵያ የሚዲያ ምኅዳር ውስጥ በሁለት እግር ለመቆም እየተፍጨረጨሩ ያሉ ታዳጊ ሚዲያዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ላይ እየተስተዋሉ ስለሆነ፣ ሐቅ ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን “ጉዳዩ የተቀነባበረ ሳይሆን አይቀርም” የሚል ምክንያታዊ ጥርጣሬ አለው። ለአብነትም፣ ከዚህ በፊት የኢትዮ 251 ሚዲያ ስቱዲዮ እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) የምርምራ ቢሮ በተመሳሳይ ሁኔታ ተሰብረው መዘረፋቸው ተገልጸው ነበር። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ላለፉት ሦስት ዓመታት ነጻና ገለልተኛ የሆኑ፣ ከፍተኛ ሙያዊ ሥነ ምግባራቸውን የጠበቁ ዘገባዎችን ለተደራሲዎች በማቅረብ ተዓማኒነት እና ተቀባይነትን እያፈራ የመጣ የበይነመረብ ሚዲያ ተቋም ነው። ይህንንም ተቀባይነት መሠረት በማድረግ ተቋማዊ አቅሙን በማስፋት ለተደራሲዎቹ የቪዲዮ ዘገባዎችን ለማቅረብ ቁሳቁስ በማሟላት የቪዲዮ ዘገባዎች የመሥራት ሙከራ ጀምሯል። ሐቅ ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ይህ ዘረፋ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥራት ያላቸው ዘገባዎች ለማድረስ እና ተደራሽነቱን ለማስፋት የሚያደርገው ጥረት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል። ይህ ዓይነቱ በሚዲያ እና በሲቪክ ተቋማት ላይ እየደረሰ ያለ ተፅዕኖ እልባት እንዲያገኝ ሁሉም የሚመለከታቸው እና ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ ጥሪ ያቀርባል። 

ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን በዚህ ጉዳይ ላይ የፖሊስ ምርመራ ውጤትን ተከታትሎ ይፋ ያደርጋል።