በአማኑኤል ይልቃል
ኢትዮ ቴሌኮም በ2015 በጀት ዓመት 75.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡ ተቋሙ ካገኘው ገቢ ውስጥ 18.78 ቢሊዮን ብር የሚሆነው የተጣራ ትርፍ መሆኑም ተገልጿል፡፡
መንግስታዊው የቴሌኮም አቅራቢ ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን ያስታወቀው የተጠናቀቀውን የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን በተመለከተ ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 11፤ 2015 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል እየሰጠ ባለው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ የተቋሙን የስራ አፈጻጸም ለጋዜጠኞች ይፋ ያደረጉት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተቋሙ “ሊድ” የተባለውን ስትራቴጂ የተገበረበት ዓመት መሆኑን አስታውሰዋል።
በዚህ ስትራቴጂ ትግበራ “ውጤታማ” ተግባራት የተከናወኑበት መሆኑን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ በበጀት ዓመቱ 116 አዳዲስ አገልግሎቶች ይፋ መደረጋቸውን ገልጸዋል። በ2015 በጀት ዓመትም 75.8 ቢሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ያገኘው ይህ ገቢ በእቅድ ተይዞ የነበረው 75.05 ቢሊዮን ብር 101 በመቶ መሆኑን ፍሬሕይወት ጠቅሰዋል። ኢትዮ ቴሌኮም በ2015 ያገኘው ገቢ ከ2014 በጀት ጋር ሲነጻጸር የ23.5 በመቶ ጭማሪ ያለው መሆኑንም አመልክተዋል። ተቋሙ በ2014 በጀት ዓመት ያገኘው ገቢ 61.3 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡
እንደ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገለጻ ኢትዮ ቴሌኮም በዚህ ዓመት ካገኘው ገቢ ውስጥ ከፍተኛ የሆነው 43.7 በመቶ ገቢ የተገኘው ከድምጽ አገልግሎት ነው። ከዳታና ኢንተርኔት የተገኘው ገቢ ደግሞ 26.6 በመቶ ድርሻ በመያዝ በሁለተኝነት ተቀምጧል። ኢትዮ ቴሌኮም ለሌላኛው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ሳፋሪ ኮም ከሚያቀርበው የመሰረተ ልማት ኪራይ 758 ሚሊዮን ብር እንዳገኘ ዛሬ ይፋ የተደረገው የተቋሙ መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮ ቴሌኮም በዚህ ዓመት ካገኘው 75.8 ቢሊዮን ብር ውስጥ 25 በመቶው ትርፍ እንደሆነ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አስታውቀዋል። በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተገኘው 18.78 ቢሊዮን ብር ትርፍ፤ ከ2014 ጋር ሲነጻጸር የ109 በመቶ ጭማሪ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)