በሃሚድ አወል
በሽብር ወንጀል የተከሰሱ አራት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና ሌሎች 19 ተከሳሾች ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ፤ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ። የተከሳሾችን በቁጥጥር ስር መዋል በተመለከተ የጸጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ያወጣውን መግለጫ በድረ ገጻቸው የጫኑ መገናኛ ብዙሃን ዘገባዎቻቸውን እንዲያወርዱም ፍርድ ቤቱ አዝዟል።
ይህን ትዕዛዝ የሰጠው ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 12፤ 2015 የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሶስተኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት ነው። ችሎቱ የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጎ ትዕዛዞችን በሰጠበት ቅጽበት፤ ተከሳሾች በጭበጨባ የታጀበ መፈክር አሰምተዋል። የተከሳሾቹ መፈክር እና ጭብጨባ፤ የችሎት ውሎ ተጠናቅቆ ታዳሚዎች ከአዳራሽ ከወጡ በኋላም አላቋረጠም ነበር።
በተከሳሾች ጭብጨባ የተጠናቀቀው ችሎት ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው፤ ጠበቆች ባቀረቡት የተከሳሾች የዋስትና ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት እና ከዚህ በፊት የተሰጡ ትዕዛዞችን አፈጻጸም ለመከታተል ነበር። የተከሳሾችን የዋስትና መብት በተመለከተ ከ20 ቀናት በፊት በነበረ የችሎት ውሎ በተደረገ ክርክር፤ ጠበቆች የደንበኞቻቸው የዋስትና ጉዳይ ሊታይ የሚገባው “የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ እና በህገ መንግስቱ እንጂ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህጉ አይደለም” ሲሉ ተከራክረዋል።

የተከሳሽ ጠበቆች ከዚህ በተጨማሪም ደንበኞቻቸው የተከሰሱበት የሽብር ወንጀል አዋጅ ዋስትና የማያስከለክል አለመሆኑን አንስተዋል። “ዐቃቤ ህግ ያቀረበው የወንጀል ፍሬ ነገር ዋስትና የሚያስከለክል አይደለም” የሚል ሙግት በችሎት ያቀረቡት ጠበቆች፤ ተከሳሾች ቋሚ አድራሻ እና ስራ ያላቸው፣ ቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸው እንዲሁም መልካም ስነ ምግባር ያላቸው መሆኑንም በመጥቀስ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።
በመዝገቡ ውስጥ የተካተቱትን አራት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፤ መስከረም አበራ፣ ዳዊት በጋሻው፣ ጎበዜ ሲሳይ እና ገነት አስማማውን በተመለከተም፤ ጉዳያቸው በመገናኛ ብዙሃን አዋጁ እንዲታይ ሰኔ 23፤ 2015 በጠበቆች ጥያቄ ቀርቦ ነበር። ጠበቆቹ ለዚህ መከራከሪያ ያቀረቡት አመክንዮ፤ ተከሳሾቹ በዐቃቤ ህግ ክስ የቀረበባቸው “ሚዲያ አቋቁመው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ” በነበረበት ወቅት መሆኑን ነው። ተከሳሾቹ በሙያቸው “ጋዜጠኞች” መሆናቸውም ጠበቆች የጠቀሱት ሌላ መከራከሪያ ነው።
በሰኔ 23ቱ ችሎት መከራከሪያውን ያስደመጠው ዐቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ተከሳሾች የተከሰሱት “በዋና ወንጀል አድራጊነት እና በሚሰጠው ውጤት ተካፋይ በመሆን ነው” በሚል የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል። በተጨማሪም ተከሳሾች ፈጸሙት በተባለው የሽብር ወንጀል “የ217 ሰዎች ህይወት ማለፉን” በማንሳት የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቋል። ከጋዜጠኞች ጋር በተያያዘ ለቀረበው መከራከሪያም፤ “እኛ የከሰስናቸው በጋዜጠኝነታቸው ሳይሆን የሽብር ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ነው” ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል። በጠበቆች በኩል የተነሳው መከራከሪያ “የህግ መሰረት የለውም” ያለው ሲልም ተከራክሯል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ የተከሳሾች የዋስትና ጥያቄ ሊታይበት የሚገባው የህግ ድንጋጌን በተመለከተ በጠበቆች በኩል የተነሳውን መከራከሪያ ውድቅ አድርጎታል። የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ የዋስትና ጉዳይን በተመለከተ “ልዩ ስነ ስርዓት ያላስቀመጠ” መሆኑን የገለጸው ችሎቱ፤ “በአዋጁ ያልተሸፈነ ከሆነ መደበኛ ህጉ ተፈጻሚ ይሆናል” ሲል ችሎቱ የጠበቆቹን መከራከሪያ ያልተቀበለበትን ምክንያት አብራርቷል።
ችሎቱ “ተከሳሾች ዋስትና ሊፈቅድላቸው ይገባል” በሚል በጠበቆች የቀረበውን መከራከሪያም መርምሮ ውድቅ ማድረጉን በዛሬው ችሎት አስታውቋል። ችሎቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው “ተከሳሾች ያቀረቡት የዋስትና ክርክር የህግ ክልከላ ያለበት [ነው]” በሚል ነው። ይህን ተከትሎም በአካል ችሎት የቀረቡ ተከሳሾች ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ችሎቱ በሙሉ ድምጽ ወስኗል። ጠበቆችም የክስ መቃወሚያቸውን ለሐምሌ 25፤ 2015 ለሚውለው ቀጣይ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ጉዳያቸው በሌሉበት ሲታይ የነበሩ ተከሳሾችን በተመለከተ፤ ዐቃቤ ህግ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመሆን በቀጣይ ቀጠሮ መጥሪያ ሰጥቶ እንዲያቀርብ ችሎቱ በዛሬው ውሎው ትዕዛዝ ሰጥቷል። ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ በፍትህ ሚኒስቴር የዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሽብር ወንጀል ክስ ከተመሰረተባቸው 51 ግለሰቦች መካከል፤ ጉዳያቸው በሌሉበት እየታዩ ያሉ ተከሳሾች ብዛት 28 ነው። ከእነዚህ ተከሳሾች ውስጥ በሌለበት ክስ የቀረበበት የኢትዮ 251 የዩቲዩብ መገናኛ ብዙሃን መስራች እና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ አንበርብር ይገኝበታል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሶስተኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት የዛሬውን ውሎ ከማጠናቀቁ በፊት፤ ተከሳሾች እነርሱን በተመለከተ በመገናኛ ብዙሃን የተላለፉ ዘገባዎች ላይ ላቀረቡት አቤቱታ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ተከሳሾች ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎት፤ “ፎቶግራፋችን ከጦር መሳሪያ ጋር ተቀነባብሮ ያለ አግባብ ተሰራጭቷል” የሚል አቤቱታ በመገናኛ ብዙሃን ላይ አቅርበው ነበር። ጉዳዩን የተመለከተው ችሎቱ ፤ ተከሳሾችን በተመለከተ “ከጸጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል የተሰጠ መግለጫ” በሚል የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ፋና ቴሌቪዥን፣ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ እና ዋልታ ቴሌቪዥን ያስተላለፏቸውን ዘገባዎች ከድረ ገጾቻቸው እና ከየሚዲያዎቹ ቋት (archive) እንዲያወርዱ ፍርድ ቤቱ አዝዟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)