በአማኑኤል ይልቃል
ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን የመጀመሪያውን ዙር 75 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተን (demobilization) ስራ በመስከረም ወር እንደሚጀምር አስታወቀ። በተሃድሶ ፕሮግራም ውስጥ እንዲያልፉ እቅድ ተይዞላቸው የነበሩ የቀድሞ ተዋጊዎች ብዛትም በ122 ሺህ ገደማ መጨመሩን ገልጿል።
ትጥቃቸውን የሚፈቱ ኃይሎች “ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ ለማድረግ” የተቋቋመው የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን፤ 250 ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን በክህሎት ስልጠና እና በስራ ፈጠራ ወደ ማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉ ለማድረግ አቅዶ ነበር። ከተቋቋመ ስምንት ወራት ያስቆጠረው ኮሚሽኑ፤ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ የቀድሞ ተዋጊዎች ከሚገኙባቸው ክልሎች እና የተሃድሶ ፕሮግራሙን በገንዘብ ከሚደግፉ አካላት ጋር ውይይት ሲያደርግ ቆይቷል።
ኮሚሽኑ የሚያካሄደው የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተን ስራ ከሚተገበርባቸው ስምንት ክልሎች ውስጥ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተካሄደባቸው የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ይገኙበታል። “የቀድሞ ተዋጊዎች ይገኙባቸዋል” የተባሉት የኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎችም የዚሁ ፕሮግራም አካል ናቸው።
በፕሮግራሙ ውስጥ ያልፋሉ ተብሎ የሚጠበቁ የቀድሞ ተዋጊዎች ብዛት 371,971 እንደሆነ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽኑ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 12፤ 2015 ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጋር በአዲስ አበባ ባደረገው ውይይት ላይ አስታውቋል። ኮሚሽኑን የሚመሩት የቀድሞው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ተሾመ ቶጋ፤ “ከሚመለከታቸው የክልል፣ የመከላከያ እና የእኛ ተቋም ጋር ሆነን በመነጋገር የደረስንበት ዳታ [ነው]” ሲሉ የቀድሞ ተዋጊዎች ብዛት ቀደም ሲል በእቅድ ከነበረው የጨመረበትን ምክንያት አስረድተዋል።
ኮሚሽነር ተሾመ በተሃድሶ ፕሮግራም ውስጥ የሚያልፉ የቀድሞ ተዋጊዎች ቁጥር ከፍ ማለቱ፤ ለዚሁ ስራ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከፍ ማድረጉን ገልጸዋል። ብሔራዊው ተሃድሶ ኮሚሽን ለዚህ ስራ የሚያስፈልገው ገንዘብ “555 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነው” የሚል መነሻ ይዞ እንደነበር ኮሚሽነሩ በማብራሪያቸው ላይ ቢጠቅሱም፤ በአሁኑ ወቅት ያስፈልጋል ተብሎ የሚገመተውን የገንዘብ መጠን ግን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።
ሰባት አምስት ሺህ የቀድሞ ተዋጊዎችን በመጀመሪያ ዙር ለመበተን ማቀዱን በዛሬው ውይይት ላይ የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ከእነዚህ ውስጥ 50 ሺህ ያህሉ በትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ እንደሆኑ ይፋ አድርጓል። የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሻንቆ ደለለኝ፤ ለመጀመሪያው ዙር ስራ የሚያስፈልገው ገንዘብ 150 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚገመት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን በሚያከናውነው የመበተን ስራ አማካኝነት ወደ “ማሰባሰቢያ ጣቢያዎች” እንዲገቡ የሚደረጉት የቀድሞ ታጣቂዎች፤ ምዝገባ ተደርጎላቸው “ዝርዝር ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ መረጃዎቻቸው” እንደሚያዝ የኮሚሽኑ የመልሶ ማቋቋም ዳይሬክተር አቶ ገመዳ አለሚ ጠቁመዋል። “ቀደም ሲል የነበሩበት ቦታ፣ ይሰሩ የነበረው [ስራ]፣ ወደፊት መስራት የሚፈልጉት፣ የሚቋቋሙበት ክልል፣ ዞን፤ ይሄ ሁሉ መረጃ እንዲጠናቀር ይደረጋል” ሲሉ አቶ ገመዳ የምዝገባ ሂደቱን አብራርተዋል።
የቀድሞ ተዋጊዎቹ ወደ ማሰባሰቢያ ጣቢያዎች ከገቡ በኋላ “አዕምሮን የመለወጥ” ስራ እንደሚከናወን የጠቀሱት የመልሶ ማቋቋም ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ሂደት በኋላ ተዋጊዎቹ መታወቂያ ተዘጋጅቶላቸው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እንደሚደረግ ገልጸዋል። ከማሰባሰቢያ ጣቢያዎቹ በሚወጡበት ጊዜም “የሚቋቋሙበት እና ህይወታቸውን ለመምራት የሚያስችላቸው የመነሻ ድጋፍ” እንደሚሰጣቸውም አክለዋል።
የተሃድሶ ኮሚሽን የመጀመሪያውን ዙር የቀድሞው ተዋጊዎች የመበተን እና ወደ ማህበረሰቡ የመቀላቀል ስራ ለማጠናቀቅ ያቀደው በመጪው ዓመት ታህሳስ ወር አጋማሽ ውስጥ ነው። ይህን ስራ ከግብ ለማድረስ ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያከናወነ መሆኑን ኮሚሽነር ተሾመ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)