በአማራ ክልል ስር የሚገኘው አዲ አርቃይ ወረዳ መጠሪያውን ሊቀይር ነው  

በአማኑኤል ይልቃል

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ውስጥ የሚገኘው አዲ አርቃይ ወረዳ ስያሜውን ለመለወጥ ሁለት አማራጮችን ለህዝብ ውይይት አቀረበ። የወረዳው ምክር ቤት ስያሜውን “ሰገነት” አሊያም “ሰላም በር” ወደሚል መጠሪያ ለመቀየር የወሰነው፤ ነባሩ መጠሪያ “የክልሉንም ሆነ የወረዳውን ህዝብ የሚገልጽ ባለመሆኑ ነው” ብሏል።

ከትግራይ ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን አጎራባች የሆነው የአዲ አርቃይ ወረዳ ምክር ቤት የስያሜ መቀየር ውሳኔውን ያስተላለፈው፤ ከሁለት ሳምንት በፊት ሐምሌ 1፤ 2015 ባደረገው ስብሰባ እንደሆነ የምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባኤ አቶ ደረጀ ጌትነት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የወረዳው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት ይህን ጉዳይ በተመለከተ ጥናት የሚያደርግ ኮሚቴ ከስብሰባው አስቀድሞ አቋቁሞ እንደነበር አቶ ደረጀ ገልጸዋል።

ጥናቱን ሲያከናውን የቆየው ኮሚቴ በሐምሌ ወር መጀመሪያ በተካሄደው የወረዳው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ፤ ሶስት የስያሜ አማራጮችን አቅርቦ እንደነበር ምክትል አፈ ጉባኤው አመልክተዋል። ከቀረቡት አማራጮች “ሀገረ ሰላም” የሚለው ውድቅ ሲደረግ “ሰገነት” እና “ሰላም በር” የሚሉት መጠሪያዎች ግን ለህዝብ ውይይት እንዲቀርቡ መወሰኑን አክለዋል። 

በዚህም መሰረት በአዲ አርቃይ ወረዳ ስር የሚገኙ 22 ቀበሌዎች፤ አማራጭ ስያሜዎቹን “ወደ ህዝብ አውርደው” ውይይት እንዲያደርጉ ትላንት ሐሙስ ሐምሌ 13፤ 2015 በደብዳቤ ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል። በአዲ-አርቃይ ወረዳ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት የተሰራጨው ይህ ደብዳቤ፤ ቀበሌዎቹ የመረጡትን ስያሜ እስከሚቀጥለው ሳምንት ሐሙስ ሐምሌ 20 ድረስ እንዲያሳውቁ ቀነ ገደብ አስቀምጧል። 

 “ሰገነት” የሚለው መጠሪያ “የወረዳው ማህበረሰብ በሀሳብ የበላይነት በውይይት እና በመደጋገፍ የላቀ ምኞት ያለው ህዝብ” መሆኑን ስለሚገልጽ፤ እንዲሁም የቃሉ ትርጉም “ከፍታን የሚገልጽ” በመሆኑ በአማራጭነት እንደቀረበ በደብዳቤው ላይ ሰፍሯል። ሁለተኛ አማራጭ ሆኖ የተቀመጠው “ሰላም በር” የሚለው ስያሜ ደግሞ፤ “የአዲአርቃይ ወረዳ ማህበረሰብ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት፣ መተጋገዝ፣ መታገልን የሚገልጽ በመሆኑ” ምክንያት እንደሆነ ደብዳቤው አትቷል። 

የአዲ አርቃይ ወረዳ ምክር ቤት ነባሩን መጠሪያ በአዲስ ለመተካት የተነሳው በሰሜኑ ጦርነት ተፈናቅለው የነበሩት የወረዳው ነዋሪዎች በዚህ ዓመት ታህሳስ ወር ላይ ወደ ቀያቸው ከተመለሱ በኋላ “ጥያቄ በማቅረባቸው” እንደሆነ የወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማው አዲሴ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በሐምሌ 2013 ዓ.ም በህወሓት ታጣቂዎች ተይዞ የነበረው የአዲ አርቃይ ወረዳ፤ ለአንድ ዓመት ከአራት ወር ገደማ ከአማራ ክልል መንግስት ቁጥጥር ውጪ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል። 

በዚህ ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 80 ሺህ የሚሆን የአዲ አርቃይ ወረዳ ነዋሪ መፈናቀሉን የወረዳው ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ ገልጸዋል። የወረዳው ስያሜ ቅያሪ ጉዳይ በጦርነቱ ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው ከተመለሱ በኋላ ይበልጥ ጎልቶ ቢሰማም፤ ማህበረሰቡ “የስም ለውጥ መደረግ እንዳለበት” በቀበሌ ምክር ቤቱ ጭምር ከዚህ ቀደም “ግፊት ሲያደርግ” መቆየቱን የወረዳው ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አስረድተዋል። 

አሁን ያለው “አዲ አርቃይ” የሚለው ስያሜ “የክልሉንም ሆነ የወረዳውን ህዝብ የሚገልጽ እንዳልሆነ” የሚናገሩት አቶ ደረጀ፤ “አዲ” የሚል ስያሜ ያላቸው በቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ ሌሎች አካባቢዎችም “በአብዛኛው” ሌላ ስያሜ እንዲይዙ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። “የቀበሌውን ስም ለውጥ ያላደረገ ‘አዲ አረጋይ’ የሚባል አለ እንጂ፤ ሌሎቹ የጎጥ ስያሜዎች በሙሉ እየተጠናቀቁ ነው። አንዳንዶቹ ጋር የወረዳው [ስያሜ] መጀመሪያ ይጽደቅ የሚል ሀሳብ ስለነበረ፤ አሁን ይሄ ከጸደቀ እስከ ሐምሌ 30 ባለው ሁሉም ያልቃል” ሲሉም አቶ ደረጀ አክለዋል። 

“ሰገነት” አሊያም “ሰላም በር” የሚለውን ስያሜ የሚይዘው አዲሱ የወረዳው መጠሪያ የሚጸድቀው፤ በቅርቡ በሚካሄደው የወረዳው ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንደሆነ ምክትል አፈ ጉባኤው ጠቁመዋል። የአዲ አርቃይ ወረዳ ምክር ቤት ስብሰባውን ያካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው፤ ከመጪው ሳምንት ሐሙስ ሐምሌ 20 እስከ ሐምሌ 25፤ 2015 ባሉት ቀናት እንደሆነም አቶ ደረጀ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)