የወልቂጤ ኤፍ. ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ሰራተኞች የሰኔ ወር ደመወዝ ስላልተከፈላቸው መቸገራቸውን ገለጹ  

በሃሚድ አወል

በደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ስር የሚገኘው የወልቂጤ ኤፍ. ኤም 89.2 ሬዲዮ ጣቢያ ሰራተኞች፤ የሰኔ ወር ደመወዝ እስካሁን ድረስ ስላልተከፈላቸው መቸገራቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በጉራጌ ዞን የሚገኘው የወልቂጤ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሰራተኞች የሰኔ ወር ደመወዝ ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው ያረጋገጡት የደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ስራ አስፈጻሚ ተወካይ፤ የተፈጠረው መስተጓጎል በቅርቡ መፍትሔ ያገኛል ብለዋል።  

መቀመጫውን በወልቂጤ ከተማ ያደረገው የወልቂጤ ኤፍ ኤም 89.2፤ የጉራጌ ዞንን እና አዋሳኝ አካባቢዎችን የሚሸፍኑ ዕለታዊ ዜናዎችንን እና ፕሮግራሞችን ለስድስት ሰዓታት ያህል ሲያሰራጭ የቆየ ነው። የደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት በስሩ ከሚያስተዳድራቸው 10 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መካከል አንዱ የሆነው ወልቂጤ ቅንርጫፍ፤ የሬዲዮ ስርጭቱን የጀመረው በ2001 ዓ.ም ነው።

የወልቂጤ ኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያ የአስተዳደር እና ድጋፍ ሰጪዎችን ጨምሮ 94 ሰራተኞችን በስሩ የሚያስተዳደር ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አምስት የሬድዮ ጣቢያው ሰራተኞች ከዚህ በፊት በወሩ መጨረሻ አካባቢ ደመወዝ ይከፈላቸው እንደነበር ገልጸው፤ ያለፈው ሰኔ ወር ደመወዝ ግን እስከ ዛሬ ሐምሌ 14፤ 2015 ድረስ እንዳልተከፈላቸው ገልጸዋል።

አንድ ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ የወልቂጤ ኤፍ ኤም ጋዜጠኛ፤ አቤቱታቸውን ለቅርንጫፉ አመራሮች ቢያቀርቡም ምላሽ አለማግኘታቸውን አስረድቷል። በወልቂጤ ኤፍ ኤም በዜና እና ፕሮግራም አዘጋጅነት የሚሰራ ሌላ ጋዜጠኛ “የደቡብ ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ድርጅት አመራሮችን ጨምሮ [ኃላፊዎች] ችግሮችን አድበስብሰው ነው የሚያልፉት። ተገቢውን ምላሽ አይሰጡንም” ሲል ተናግሯል።

የደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት ስራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ ዘላለም ገነሞ በበኩላቸው “አንድም ሰራተኛ እኛ ጋር ቅሬታ አላቀረበም። በስልክ እንኳን [ደውሎ] የጠየቀን የለም” ሲሉ ለተቋማቸው የመጣ አቤቱታ አለመኖሩን አስተባብለዋል። የሰራተኞች ደመወዝ ሲዘገይ “የመጀመሪያ ጊዜ” መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዘላለም፤ “ሌሎች የመንግስት ሰራተኞችም ወር ጠብቀው ደመወዝ እያገኙ አይደለም” ሲሉ ችግሩ የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ብቻ አለመሆኑን አመልክተዋል። 

የወልቂጤ ኤፍ ኤም ሰራተኞች  ደመወዝ የዘገየበትን ምክንያት በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ዘላለም፤ ለጥያቄው ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የተቋሙ ሰራተኞች አቤቱታቸውን ለመገናኛ ብዙሃን ማቅረባቸውን ተችተዋል። አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የደቡብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት አመራር ግን የሰራተኞቹ ደመወዝ እስካሁን ሳይከፈል የቆየው፤ “የካሽ እጥረት ስላጋጠመ ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የችግሩን መንስኤ አስረድተዋል። 

አቶ ዘላለምም ሆኖ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የስራ ኃላፊ፤ የወልቂጤ ቅርንጫፍ ሰራተኞች ደመወዝ ክፍያ “በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት ቀናት” እንደሚፈጸም ቃል ገብተዋል። የደቡብ ቴሌቪዥን እና ሬዲዮ ድርጅት የሰራተኞቹን ደመወዝ ለመክፈል፤ ከጉራጌ ዞን የፋይናንስ መምሪያ ጋር ንግግር ለማድረግ ተወካይ ወደ ወልቂጤ መላኩን አቶ ዘላለም ለዚህ በማሳያነት ጠቅሰዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)