የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት፤ በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚፈጸሙ “ተደጋጋሚ” ዘረፋዎች “አሳስበውኛል” አለ 

በአማኑኤል ይልቃል

በመገናኛ ብዙሃን ላይ የተፈጸሙ የዘረፋ ወንጀሎችን፤ መንግስት “በተቻለ ፍጥነት ተከታትሎ የምርመራውን ውጤት ለህዝብ ይፋ” እንዲያደርግ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ጠየቀ። በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ቢሮ እና መሳሪያዎች ላይ “ባልታወቁ ሰዎች በተቀናጀ እና የተናበበ በሚመስል መልኩ” የሚፈጸም ተደጋጋሚ ዘረፋ ጉዳዩን አሳሳቢ እንዳደረገው ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ይህንን ጥያቄ ያቀረበው፤ በመገናኛ ብዙሃን ላይ “እየተፈጸመ ነው” ስላለው “ዘረፋ እና የወንጀል ድርጊት” በተመለከተ ዛሬ አርብ ሐምሌ 14፤ 2015 ባወጣው መግለጫ ነው። ምክር ቤቱ በዚሁ መግለጫው “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ” የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት “ባልታወቁ ግለሰቦች” ቢሮአቸው እየተዘረፈ እንዲሁም መረጃ ለመቀበል እና ለማስተላለፍ የሚጠቀሙባቸው መሳሪያዎችም እየተወሰዱባቸው መሆኑን ጠቅሷል።  

ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ አራት መገናኛ ብዙሃን ዘረፋ እንደተፈጸመባቸው የጠቀሰው መግለጫው፤ ይህ ድርጊት “አራት ኪሎ ሚዲያ”፣ “ኢትዮ 251 ሚዲያ” እና “የኔታ ቲዩብ” ላይ እንደተፈጸመ ዘርዝሯል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የበይነመረብ መገናኛ ብዙሃን ላይ የተፈጸመው ዝርፊያም በዛሬው መግለጫው ላይ ተነስቷል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር”ን የሚያስተዳድረው ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 10፤ 2015 ባወጣው መግለጫ፤ የበይነመረብ ሚዲያው ቢሮ ውስጥ ያለ ካዝና “ባልታወቁ አካላት” ተሰብሮ ንብረቶች መዘረፋቸውን ይፋ አድርጎ ነበር። የተዘረፉት ንብረቶች፤ “ሶስት አዳዲስ እና ዘመናዊ ዲጂታል ካሜራዎች፣ ሁለት ዙም ሌንሶች፣ ሌሎች አራት መደበኛ ሌንሶች፣ አራት ላፕቶፖች እና አንድ ስማርት የሞባይል ስልክ” እንደሆኑ ድርጅቱ አመልክቷል። 

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በዛሬው መግለጫው፤ ይህ አይነቱ በመገናኛ ብዙሃን ላይ የሚፈጸም ተደጋጋሚ ዘረፋ “የቢሮ በር ሳይሰበር፣ በእረፍት ቀናት፣ በተመረጡ ድርጅቶች እና በሚዲያ ቁሳቁሶች” ላይ የተከናወነ መሆኑን ጠቅሷል። ይህ ተደጋጋሚ ድርጊት “ባልታወቁ ሰዎች፣  በተቀናጀ እና የተናበበ በሚመስል መልኩ” መፈጸሙ “ነገሩን ይበልጥ አሳሳቢ እንዳደረገው” የገለጸው ምክር ቤቱ፤ “የዘረፋው መደጋገም ድርጊቱ በተራ ግለሰቦች የተፈጸመ ነው ለማለት ጥርጣሬ የሚጭር ሆኗል” ብሏል።

“[የዘረፋ] ድርጊቱ እንደተፈጸመ በተቻለ ፍጥነት ምርምራ በማድረግ አጥፊዎችን ህግ ፊት የማቅረብ ሂደቱ ዘገምተኛ መሆኑ፤ በአዋጁ መሠረት  ጋዜጠኞች ስራቸውን በነጻነት እንዳይሰሩ፤ እንዲሸማቀቁና የፕሬስ ምህዳሩ የበለጠ እንዲጠብ እያደረገው ነው”

– የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት

በመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ ላይ እየተፈጸመ ስላለው ዘረፋ “ለሚመለከታቸው የፖሊስ አካላት” ሪፖርት ቢደረግም፤ “በድርጊቱ ተሳታፊ በሆኑ ግለሰቦች ላይ የተያዘው የምርምራ ሂደት ምን እንደደረሰ” አለመታወቁም በመግለጫው ላይ ሰፍሯል። ከዝርፊያዎቹ በኋላ ሲደረግ የቆየውን ምርምራ እና አጥፊዎችን ህግ ፊት የማቅረብ ሂደቱን “ዘገምተኛ” ሲል የገለጸው ምክር ቤቱ፤ ይህም “ጋዜጠኞች ስራቸውን በነጻነት እንዳይሰሩ፤ እንዲሸማቀቁና የፕሬስ ምህዳሩ የበለጠ እንዲጠብ እያደረገው ነው” በማለት ተችቷል።  

ወንጀልን “የመከላከል፣ የመመርመር እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት” ያለበት መንግስት፤ “ለመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ተገቢ የሆነ ጥበቃ እንዲያደርግ” ምክር ቤቱ ጠይቋል። መንግስት በመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ ላይ የተፈጸመውን የወንጀል ድርጊት “በተቻለ ፍጥነት ተከታትሎ የምርመራውን ውጤት ለህዝብ ይፋ በማድረግ ሕገመንግስታዊ ግዴታውን እንዲወጣም” ምክር ቤቱ በዛሬው መግለጫው ተጨማሪ ጥያቄ አቅርቧል።

ይህ አይነቱ ጥያቄ በ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ላይ ስለተፈጸመው የዘረፋ ወንጀል ትላንት ረቡዕ ሐምሌ 13፤ መግለጫ ባወጣው ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች (CPJ) በኩልም ተስተጋብቷል። የሲፒጄ ከሰሃራ በረሃ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገራት ተወካይ የሆኑት ሙቶኪ ሙሞ፤ “በተቺ እና በነጻ ጋዜጠኝነት በሚታወቀው ‘ኢትዮጵያ ኢንሳይደር’ ላይ የተፈጸመው ዝርፊያ፤ በስራው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል” ሲሉ ዝርፊያው የሚያደርሰውን ጉዳት አመልክተዋል፡፡ 

ፖሊስ ይህንን ክስተት “ግልጽ በሆነ መንገድ” መመርመር እንዳለበት የተናገሩት ሙቶኪ፤ ዝርፊያ የተፈጸመበትን ምክንያት “መለየት እና ፈጻሚዎቹን ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት” አመልክተዋል። የሲፒጄ ተወካይዋ “ተዓማኒ የምርመራ ስራ”፤ ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን አዲስ አበባ ውስጥ “ደህንነታቸው የተጠበቀ” መሆኑን እስከ ማረጋገጥ ድረስ የሚጓዝ መሆኑንም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)