የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች በተመረጠላቸው “የትኩረት መስክ” ብቻ እንዲያስተምሩ የሚያደርገው አዲስ አሰራር እንዴት ይተገበራል?  

በአማኑኤል ይልቃል

በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ 47 የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች፤ ራስ ገዝ መሆንን ጨምሮ አዳዲስ አሰራሮችን ለመተግበር እየተዘጋጁ ይገኛሉ። “አጠቃላይ” የትምህርት ዘርፎችን ለተማሪዎች ሲሰጡ የቆዩት እነዚህን ዩኒቨርስቲዎች፤ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ በተለየላቸው “የተልዕኮ እና የትኩረት መስክ” ብቻ የሚያስተምሩ ተቋማት ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። 

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዕቅድ መሰረት፤ ከመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የተወሰኑት “አጠቃላይ” ሆነው የሚቀጥሉ ሲሆኑ ሌሎቹ ግን የምርምር፣ የ“አፕላይድ ሳይንስ” እንዲሁም የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች ሆነው ይቀጥላሉ። የምርምር ዩኒቨርስቲ ተብለው የተለዩት፤ “የመጀመሪያ ትውልድ” በሚል መለያ የሚታወቁት የአዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ መቐለ፣ አርባ ምንጭ፣ ባሕር ዳር፣ ሀዋሳ እና ሐረማያ ዩኒቨርስቲዎች ናቸው። 

አምቦ፣ ጅግጅጋ፣ ደብረ ብርሃን፣ አክሱም፣ ዲላ እና ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲዎች የተካተቱበት “ሁለተኛው ትውልድ” የ15 ዩኒቨርስቲዎች ስብስብ ደግሞ፤ የተግባር ሳይንስ (አፕላይድ ሳይንስ) ላይ ትኩረት የሚያደርግ ይሆናል። ሃያ አንድ ዩኒቨርስቲዎች ያሉበት “የሶስተኛው ትውልድ” የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምድብ፤ በ“አጠቃላይ” ዩኒቨርስቲነት የሚቀጥል ይሆናል። የ“ሶስተኛው ትውልድ” ዩኒቨርስቲዎች ከሚባሉት ውስጥ ቦረና፣ እንጅባራ፣ ቀብሪ ደሃር፣ ወራቤ፣ ኦዳ ቡልቱም፣ ደባርቅ፣ ጅንካ እና ጋምቤላ ዩኒቨርስቲዎች ይገኙበታል። 

ፎቶ፦ ኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ

በትምህርት ሚኒስቴር አዲስ አሰራር መሰረት የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች ተብለው የተለዩት፤ የአዲስ አበባ እና የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲዎች ናቸው። ኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ ብቻውን “የትምህርት ዩኒቨርስቲ” የሚል ልዩ ምድብ አግኝቷል። ዩኒቨርስቲዎቹ በዚህ ክፍፍል መሰረት ተልዕኮ ቢሰጣቸውም፤ ትኩረት የሚያደርጉባቸው የትምህርት መስኮች የተመረጡ እንዲሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር ሌላ ክፍፍል አዘጋጅቷል። 

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ትላንት ማክሰኞ ሐምሌ 18፤ 2015 በመስሪያ ቤቱ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፤ ዩኒቨርስቲዎቹ የተመረጡ የትምህርት አይነቶችን በስራቸው ባሉ ኮሌጆች እንዲሰጡ እንደሚደረግ ገልጸዋል። “[ዩኒቨርስቲዎች] 70 እና 80 ፕሮግራም አማካይ በሆነ ደረጃ እያስተማሩ አይቀጥሉም። በጣም ጥሩ በሆኑባቸው ውስን ኮሌጆች ላይ፣ በጣም በተመጠነ ደረጃ ፕሮግራሞችን ይዘው፣ የትምህርት ጥራት የሚያመጡበት፣ የራሳቸውን ብቃት የሚያሳድጉበት ስራ ይሰራሉ” ሲሉ ዶ/ር ሳሙኤል ተናግረዋል።  

የመንግስት ዩኒቨርስቲዎቹ ትኩረት የሚያደርጉባቸው የትምህርት መስክ የተመረጠላቸው፤ ያላቸውን “የውስጥ አቅም” እንዲሁም “ያሉበትን የኢኮኖሚ ኮሪደር እና የአካባቢ ጸጋ” ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ በትላንቱ መግለጫ ላይ አመልክተዋል። በዚህ እቅድ መሰረት ብዛት ያላቸውን የትምህርት ክፍሎች ከፍተው ተማሪዎችን እያስተማሩ ያሉ የመንግስት ዩኒቨርሰቲዎች፤ “አንዳንድ ፕሮግራሞች እና ኮሌጆችን ሊያጥፉ፣ ሊያጠቡ እና ወደ ሌላ ዩኒቨርስቲዎች ሊያሸጋሽጉ” እንደሚችሉ ዶ/ር ሳሙኤል ለጋዜጠኞች አብራርተዋል።

ፎቶ፡ ትምህርት ሚኒስቴር

“የአፕላይድ ሳይንስ” ዩኒቨርስቲ እንዲሆን የተመደበው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ፤ ይህንኑ እቅድ ለመተግበር ከወዲሁ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯል። ዩኒቨርስቲው ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ አዲስ ለውጦችን መተግበር እንደሚጀምር ባለፈው ሰኔ ወር መጀመሪያ ለተማሪዎቹ ገልጿል። በዘንድሮው ዓመት ለተቀበላቸው ተማሪዎች፤ በዚህ ዓመት የሚወስዱትን “ፍሬሽ ማን ኮርስ” ካጠናቀቁ በኋላ የመጀመሪያ ዲግሪ ለማግኘት የሚመርጧቸው የትምህርት አይነቶች የተገደቡ እንደሚሆኑም አስታውቋል። 

ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ በዚህ ዓመት 1,200 አዲስ ተማሪዎችን መቀበሉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ንጉስ ታደሰ፤ ዩኒቨርስቲው ለአዲሶቹ ተማሪዎች ገለጻ ሲያደረግ ትኩረት የሚደረግባቸው የትምህርት ዘርፎች ውስጥ ያሉ የትምህርት ክፍሎችን እንዲመርጡ “ማበረታታቱን” ያስረዳሉ። ስምንት ኮሌጆችን እና በስራቸው ያሉ በርካታ ትምህርት ክፍሎች የሚያስተዳድረው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ፤ ከ2016 የትምህርት ዘመን ጀምሮ አዲስ ተማሪ የሚቀበለው “የትኩረት መስክ” ተብለው በተለዩለት አራት የትምህርት ዘርፎች ብቻ ነው። 

ከመጪው ዓመት ጀምሮ ተማሪዎች የሚመርጧቸው የትምህርት ክፍሎች፤ በኢንጂነሪንግ እና ቴክኖሎጂ፣ ቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ፣ ሃይላንድ አግሪካልቸር (highland agriculture) እንዲሁም ሌሎች የጤና ሳይንስ (other health science) በሚባሉት የትምህርት ዘርፎች ውስጥ ያሉ ብቻ ይሆናሉ። በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ያሉ ሌሎች የትምህርት ክፍሎችን በተመለከተ የሚኖረው አካሄድ፤ የተቀበሏቸውን ተማሪዎች “ማስጨረስ” እንደሚሆን የዩኒቨርስቲው የትምህርት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አህመድ መሀመድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።

ፎቶ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ

እነዚህ የትምህርት ክፍሎች የሚሰጧቸው ትምህርቶች ለሌሎች ተማሪዎች “በኮመን ኮርስነት” የሚሰጡ ከሆነ ግን፤ መምህራኑ እነዚሁኑ ትምህርቶች ማስተማር እንደሚቀጥሉ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። የትምህርት አይነቶቹ “እንደ ዲፓርትመንት ሆነው ሳይሆን ኮመን ኮርስ ሆነው ይመረጡና ጠቃሚ የሆኑት ይቀራሉ” ሲሉም ያክላሉ። አቶ አህመድ ለዚህ በማሳያነት የሚጠቅሱት በማህበራዊ ሳይንስ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ስር የሚገኙትን የትምህርት ክፍሎችን ነው። በስሩ ስምንት የትምህርት ክፍሎችን የያዘው ይህ ኮሌጅ፤ ከሚሰጣቸው ትምህርቶች ውስጥ አማርኛ ቋንቋ እና ስነ ጽሁፍ፣ እንግሊዝኛ ቋንቋ እና ስነ ጽሁፍ፣ ሳይኮሎጂ እንዲሁም ሶሲዮሎጂ ይገኙበታል።

ጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን፣ ታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር፣ ጂኦግራፊ እና አካባቢ ጥናት እንዲሁም ስነ ዜጋ እና ስነ ምግባር በዚህ ኮሌጅ ስር የሚገኙ ሌሎች የትምህርት ክፍሎች ናቸው። ከእነዚህ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ከአማርኛ ቋንቋ እና ስነጽሁፍ እንዲሁም ከጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን ውጪ ያሉት የትምህርት ክፍሎች “ኮመን ኮርስ” ሆነው የሚሰጡ በመሆኑ፤ የሚቀጥሉበት እድል መኖሩን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ይናገራሉ። “አማርኛ እስካሁን ኮመን ኮርስ የለም” የሚሉት አቶ አህመድ፤ ይህ ትምህርት ራሱን ችሎ በዩኒቨርስቲው እየተሰጠ እንደማይቀጥል ጠቁመዋል።

ይህ የዩኒቨርስቲው እርምጃ ከሰሞኑ በማህበራዊ ትስስር ገጾች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቶ ነበር። የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ንጉስ ግን የአማርኛ ቋንቋ እና ስነጽሁፍ ትምህርት በሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንዲሰጥ መመረጡን በመጥቀስ፤ “የግድ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ውስጥ መሰጠት የለበትም” የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ። “አማርኛ ደብረ ብርሃን [ዩኒቨርስቲ] ካልተማሩ ወሎ [ዩኒቨርስቲ] ቢማሩ ስህተት ነው ማለት ነው እንዴ?” ሲሉም ሀሳባቸውን በጥያቄ ይደግፋሉ።

ፎቶ፦ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ

የዩኒቨርስቲው ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር በበኩላቸው ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የአማርኛ ቋንቋ እና ስነ ጹሁፍን በትምህርት ደረጃ ባይሰጥም፤ “የቋንቋ ማዕከል” ለመክፈት በሂደት ላይ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ዩኒቨርስቲው ከአማርኛ ቋንቋ ጋር በተያያዘ፤ ከማስተማር ባሻገር ያሉ ስራዎችን ማከናወን እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። 

ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ከትምህርት ክፍሎች መዘጋት ጋር በተያያዘ “የዜና ርዕሰ ጉዳይ” የሆነው፤ በትምህርት ሚኒስቴር “ሪፎርም ላይ ግንባር ቀደም፣ ፋና ወጊ ሆኖ እየሰራ ስለሆነ ነው” ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ሳሙኤል በትላንቱ መግለጫ ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙን እርምጃ ተከላክለዋል። ትምህርት ሚኒስቴር “ካለፈው ዓመት ጀምሮ ዝግጅት ሳደርግበት ነበር” ባለው በዚህ ሪፎርም መሰረት፤ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች ወደተለየላቸው የተልዕኮ እና ትኩረት መስክ ራሳቸውን ሙሉ ለሙሉ የሚቀይሩበት እቅድ ማዘጋጀታቸውን አስታውሰዋል። ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ለዚህ እቅድ ጥሩ የሆነ “entry and exit strategy” ማዘጋጀቱን በመጥቀስም የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙን አሞካሽተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ይህንን ቢሉም “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የሁለት ኮሌጆች ዲኖች ግን፤ በሚቀጥለው ዓመት ትግበራ ስለሚጀመርበት እቅድ እና በስራቸው ስላሉ ትምህርት ክፍሎች እጣ ፋንታ “በወሬ ከሚሰማው በዘለለ በደብዳቤ የተገለጸልን ነገር የለም” ባይ ናቸው። በዩኒቨርስቲው ከሚዘጉት የትምህርት ክፍሎች አንዱን በስሩ የያዘ ኮሌጅን የሚመሩ ዲን፤ እነዚህን ትምህርቶች የሚሰጡ መምህራን ዕጣ ፋንታ ምን እንደሚሆን እስካሁን ድረስ አለመገለጹን አስረድተዋል። 

“ለመምህራኑ እንደ ሀገር ስትራቴጂ ተቀምጧል። ማንም መምህር ቢሆን መንግስት ቀጥሮት ነው እንጂ እንዲሁ የገባ የለም። አታስፈልግም ተብሎ እንደ ዕቃ ነገር ሊቆጠር አይችልም”

– ዶ/ር ንጉስ ታደሰ፤ የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት

የደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ንጉስ ግን ዩኒቨርስቲው ስለዚህ እቅድ ገለጻ በማድረግ ላይ መሆኑን በመጥቀስ ትችቱን አስተባብለዋል። “ለመምህራኑ እንደ ሀገር ስትራቴጂ ተቀምጧል። ማንም መምህር ቢሆን መንግስት ቀጥሮት ነው እንጂ እንዲሁ የገባ የለም። አታስፈልግም ተብሎ እንደ ዕቃ ነገር ሊቆጠር አይችልም። እኛም ደግሞ ነገሩን አቅርበን፤ በተረጋጋ ሁኔታ ለመነጋገር ሞክረናል” ብለዋል። ዩኒቨርስቲው ባዘጋጀው ስትራቴጂ፤ መምህራንን አስመልክቶ ሁለት መንገዶች ተግባራዊ እንደሚደረጉም ጠቁመዋል።  

በዚህም መሰረት በ“ኮመን ኮርስ” የሚሰጡ ትምህርቶችን የሚያስተምሩ መምህራን፤ በዩኒቨርስቲው እንዲቀጥሉ እንደሚደረግ ዶ/ር ንጉስ አስረድተዋል። በዚህ ውስጥ የማይካተቱ ትምህርቶችን የሚያስተምሩ መምህራን ደግሞ ትምህርቱ ወደሚሰጥባቸው ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች “እንዲሸጋሸጉ ይደረጋል” ብለዋል። ዩኒቨርስቲው ይህንን እቅድ ባስታወቀበት ወቅት ሁሉም አካላት “መቶ በመቶ እንዳልተግባቡበት” ግን ፕሬዝዳንቱ አልሸሸጉም።

በትላንትናው የትምህርት ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ መምህራንን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ሳሙኤል፤ መምህራን በአንድ ቦታ ሳይወሰኑ እየተዘዋወሩ በሌሎች ዩኒቨርስቲዎችም ማስተማር እንደሚችሉ ተናግረዋል። “ዩኒቨርስቲዎችን የከፈትነው ለስራ ፈጠራ አይደለም። ዩኒቨርስቲዎችን የከፈትነው የሀገር መፍትሔ የሚሆኑ የሰው ኃይል እንዲያፈሩልን፤ ይህንን ደግሞ በብቃት እንዲያዘጋጁልን ነው” ሲሉ የዩኒቨርስቲ መምህራን “በሌሎች አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው መስራት” እንዳለባቸው ሚኒስትር ዲኤታው አስገንዝበዋል። 

“ዩኒቨርስቲዎችን የከፈትነው ለስራ ፈጠራ አይደለም። ዩኒቨርስቲዎችን የከፈትነው የሀገር መፍትሔ የሚሆኑ የሰው ኃይል እንዲያፈሩልን፤ ይህንን ደግሞ በብቃት እንዲያዘጋጁልን ነው”

– ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ፤ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ

ከመጪው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ በሚደረገው አዲስ አሰራር የሚያስተምሩባቸው የትምህርት ክፍሎች የሚዘጉባቸው መምህራንን፤ ትምህርት ሚኒስቴር በራሱ ይመድብ እንደሆነ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለዶ/ር ሳሙኤል ጥያቄ አቅርባ ነበር። “ይህ የሚወሰነው፤ እቅዱ ተተግብሮ ምን ያህል መምህራን በየትኛው ዩኒቨርስቲ እንደሚያስፈልግ ከታወቀ በኋላ ነው” ሲሉ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ምላሽ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)