የአማራ ክልል የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና የርዕሰ መስተዳድሩ የጸጥታ አማካሪ ከስልጣናቸው ተነሱ   

በአማኑኤል ይልቃል

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪያቸውን እና የክልሉን ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊን ከስልጣናቸው አነሱ። ዶ/ር ይልቃል የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪያቸውን ከኃላፊነት ያነሱት የተሰጣቸውን “ተግባር እና ኃላፊነት በአግባቡ አልተወጡም” በሚል ነው። 

ዶ/ር ይልቃል ሁለቱን ኃላፊዎች ከስልጣናቸው ያነሱት ከትላንት በስቲያ ሰኞ ሐምሌ 17፤ 2015 በጻፉት ደብዳቤ ነው። በአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ በምክትል ኃላፊነት ደረጃ የርዕሰ መስተዳድሩ የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ከፋለ እሱባለው እና የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኮማንደር መንገሻ አውራሪስ፤ ውሳኔውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። 

ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ከአማካሪነታቸው የተነሱት አቶ ከፋለ፤ በዚህ የኃላፊነት ቦታ ለአምስት ዓመት ገደማ ቆይተዋል። አቶ ከፋለ ይህንን ኃላፊነት ያገኙት በቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአመራርነት ጊዜ ሲሆን፤ የአሁኑን ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃልን ጨምሮ ባለፉት ዓመታት ክልሉን የመሩትን አምስት ርዕሰ መስተዳድሮች በአማካሪነት አገልግለዋል። 

ፎቶ፦ አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (አሚኮ)

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሶሲዮሎጂ እንዲሁም በሰላም እና ደህንነት ጥናት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው የቀድሞው አማካሪ፤ አሁን በስራ ላይ ያለውን የአማራ ክልልን የጸጥታ ተቋም “ካደራጁ ሰዎች መካከል አንዱ” መሆናቸው ይነገርላቸዋል። በርዕሰ መስተዳድሩ ዶ/ር ይልቃል ፊርማ የወጣ እና ለአማካሪው የደረሰው የስንብት ደብዳቤ፤ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪነት “የተሰጠዎትን ተግባር እና ኃላፊነት በአግባቡ ያልተወጡ በመሆኑ ከኃላፊነት የተነሱ መሆኑን አሳውቃለሁ” ሲል የውሳኔውን ምክንያት ይጠቅሳል።

ይህ ውሳኔ ከመተላለፉ አንድ ቀን አስቀድሞ በተካሄደ “የድርጅት ግምገማ” ጥሩ አፈጻጸም ማሳየታቸው ተገልጾ እንደነበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት አቶ ከፋለ፤ ውሳኔው “ያልተጠበቀ” እንደሆነባቸው ገልጸዋል። የቀድሞው የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪ ከኃላፊነት የተነሱት በአሁኑ ጊዜ ካለው የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ይሆን እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ “አዎ፤ ጊዜው ባይሆንም ቀስ ብዬ የምገልጻቸው ነገሮች ይኖራሉ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

በአማራ ክልል በቅርቡ የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች፤ በክልሉ “የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ” ላይ “ተጽዕኖ” ማሳደራቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የአማራ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተናግረው ነበር። ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከኃላፊነት ያነሷቸው የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮማንደር መንገሻም በተመሳሳይ ውሳኔው ድንገተኛ እንደሆነባቸው “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ከኃላፊነት የተነሱበት ውሳኔ በተላለፈበት ቀን “በስምሪት ላይ” እንደነበሩ የጠቀሱት ኮማንደር መንገሻ፤ “የተነገረኝ ምክንያት የለም” ሲሉ ከምክትል ቢሮ ኃላፊነት የተነሱበትን ምክንያት እንደማያውቁ ተናግረዋል። 

ኮማንደር መንገሻ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሆነው የተሾሙት በቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አማካኝነት ነበር። ተሰናባቹ ምክትል የቢሮ ኃላፊ በዚህ ቦታ ከመሾማቸው አስቀድሞ፤ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር እና የሰው ልማት ዳይሬክተር በመሆን ሰርተዋል። በሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ለሶስት ዓመት ከአራት ወር ገደማ የሰሩት ኮማንደር መንገሻ፤ በአማራ ክልል የጸጥታ መዋቅር ውስጥ በአጠቃላይ ለ20 ዓመታት ገደማ አገልግለዋል።

የሁለቱን ኃላፊዎች ስንብት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ጥያቄ ብታቀርብም፤ ጽህፈት ቤቱ “ደብዳቤው እኛ ጋር አልደረሰም” የሚል ምላሽ በመስጠት ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቧል። በአማራ ክልል የልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች ለማስገባት የተጀመረውን እንቅስቃሴ ተከትሎ፤ በተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ ችግሮች መከሰታቸው አይዘነጋም። በክልሉ በቅርብ ጊዜያት በተፈጸሙ ጥቃቶች፤ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የጸጥታ መዋቅር ኃላፊዎች መገደላቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)