በአማኑኤል ይልቃል
ኢትዮ ቴሌኮም በ2016 በጀት ዓመት አጠቃላይ ገቢውን 90.5 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ማቀዱን አስታወቀ። ተቋሙ በተጀመረው በጀት ዓመት የደንበኞቹን ቁጥር በስድስት ሚሊዮን ለማሳደግም አቅዷል።
መንግስታዊው የቴሌኮሚዩኒኬሽን አቅራቢ ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን ያስታወቀው የ2016 እቅዱን አስመልክቶ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 20፤ 2016 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። የተቋሙን እቅድ ለጋዜጠኞች ያብራሩት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ ኢትዮ ቴሌኮም “ሊድ” የተሰኘውን ስትራቴጂውን በአዲሱ በጀት ዓመት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ይሁንና የእዚህ ዓመት እቅድ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
የተጠናቀቀውን የ2015 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በገቢ ረገድ የእቅዱን 101 በመቶ ማሳካቱን አስታውቆ ነበር። ኢትዮ ቴሌኮም በ2015 በጀት ዓመት ካገኘው 75.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ውስጥ 18.78 ቢሊዮን ብር በትርፍነት የተመዘገበ መሆኑን መግለጹ አይዘነጋም። ተቋሙ አገኘሁት ያለው ይህ ትርፍ፤ ከ2014 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር 109 በመቶ ዕድገት ያሳየ ነው።
በሐምሌ ወር በተጀመረው የ2016 በጀት ዓመት ደግሞ ተቋሙ ገቢውን በ19.4 በመቶ በማሳደግ በዓመቱ መጨረሻ 90.5 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ማቀዱን ፍሬሕይወት በዛሬው መግለጫ ላይ ተናግረዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ዕቅዱን ማሳካት ከቻለ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ካገኘው በ14.73 ቢሊዮን ብር ከፍ ያለ ገቢ ያስመዝግባል።
ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው የዓመታዊ ዕቅድ መግለጫው የደንበኞቹን ቁጥር አሁን ካለበት 72 ሚሊዮን ወደ 78 ሚሊዮን ለማሳደግ ማቀዱም ይፋ ተድርጓል። ተቋሙ ይህንን እቅድ ሲያስቀምጥ “የውድድር ገበያ ከመኖሩ አንጻር ብዙ ውይይት” ማድረጉን የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ ይሁንና ይሳካል በሚል እቅዱ መቀመጡን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።
እስከዚህ ዓመት መጀመሪያ ድረስ ብቸኛ የቴሌኮም አገልግሎቶች አቅራቢ የነበረው ኢትዮ ቴሌኮም፤ ደንበኞቹን በስድስት ሚሊዮን ለማሳደግ ሲያቅድ ለዚሁ አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር የተለያዩ ማስፋፊያዎችን ለማድረግ እቅድ ይዟል። ከእነዚህ የማስፋፊያ ስራዎች ውስጥ፤ አጠቃላይ የሞባይል ኔትወርክ ደንበኛ የማስተናገድ አቅሙን ወደ 92 ሚሊዮን ማድረስ እንደሚገኝበት በመግለጫው ተጠቅሷል። ተቋሙ ተጨማሪ 998 የሞባይል ጣቢያዎችን በዚህ ዓመት ለመክፈት ማቀዱንም አስታውቋል።
ኢትዮ ቴሌኮም የአዲሱን በጀት ዓመት እቅድ ሲይዝ፤ የሀገሪቱ “የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታ ይሻሻላል” የሚል ግምት ታሳቢ አድርጎ እንደሆነ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ በዛሬው መግለጫቸው ላይ አመልክተዋል። የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት የመስጠት ስራን በዚህ ዓመት ከጀመረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጋር፤ “ጤናማ የውድድር ገበያ ይኖራል” የሚል ግምገማ ላይ ተመርኩዞ ተቋማቸው ዕቅድ መያዙን ፍሬሕይወት አስረድተዋል። ሳፋሪኮም በቅርቡ ይጀምረዋል ተብሎ የሚጠበቀው “ኤምፔሳ” የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት እንዲሁም በዚህ በጀት ዓመት የኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያን ይቀላቀላል ተብሎ የሚጠበቀው ሶስተኛው የቴሌኮም አቅራቢ ኩባንያ ውድድርን ኢትዮ ቴሌኮም ከግምት ውስጥ ማስገባቱንም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)