በሽብር ወንጀል የተከሰሱ 23 ተከሳሾች፤ ጉዳያቸውን የያዙት ዋና ዳኛ እንዲቀየሩ አቤቱታ አቀረቡ   

በሃሚድ አወል

በሽብር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው አራት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና ሌሎች 19 ተከሳሾች፤ ጉዳያቸው የሚመለከተውን ችሎት በሰብሳቢነት የሚመሩት ዳኛ ከቦታቸው እንዲነሱ ጥያቄ አቀረቡ። የተከሳሾችን አቤቱታ በጽሁፍ የተቀበለው ፍርድ ቤቱ፤ አቤቱታውን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት 15፤ 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ለዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 25፤ 2015 ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው፤ ከምስክሮች ጥበቃ ጋር በተያያዘ ብይን ለመስጠት ነበር። ሆኖም ሶስቱ የችሎቱ ዳኞች ወደ አዳራሽ ገብተው የችሎቱን መደበኛ ስራ ለማስጀመር ግራ ቀኙን ከመሰየማቸው በፊት፤ የተከሳሽ ጠበቆች የደንበኞቻቸው ቤተሰቦች “ችሎት ተገኝተው ጉዳዩን እንዳይታደሙ በጸጥታ ኃይሎች ተከልክለዋል” የሚል አቤቱታቸውን አቅርበዋል። 

የዛሬውን የችሎት ውሎ ለመታደም፤ ወደ ስልሳ የሚጠጉ የተከሳሾች ቤተሰቦች እና ወዳጆች በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተገኝተው ነበር። የፍርድ ቤቱን ውሎ ለመታደም የፈለጉ ሰዎች ከረፋዱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ ችሎቱ ከሚሰየምበት “ፍትሕ አዳራሽ” አቅራቢያ ተሰባስበው ሲጠባበቁ ቢቆዩም፤ ችሎት የሚጀመርበት ሰዓት ሲቃረብ በስፍራው የነበሩ የማረሚያ ቤት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ታዳሚዎችን ከአካባቢው እንዲርቁ አድርገዋቸዋል።

የጸጥታ አካላቱ ይህን እርምጃ የወሰዱት፤ ባለፈው ሐምሌ 12፤ 2015 በነበረው የችሎት ውሎ በፍርድ ቤቱ አዳራሽ ውስጥ ከተፈጠረው ክስተት ጋር በተያያዘ መሆኑ ሲናገሩ ተደምጠዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን የደንብ ልብስ የለበሱ አንድ ፖሊስ፤ ታዳሚዎቹን ባለፈው ቀጠሮ “ችሎት ረብሻችኋል” በሚል ወደ አዳራሹ እንዳያቀርቡ ሲከላከሉ ታይተዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት በነበረው የችሎት ውሎ፤ ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን የዋስትና ጥያቄውን ውድቅ አድርጎ ትዕዛዞችን ሲሰጥ ተከሳሾች በጭብጨባ የታጀበ መፈክር እና ዝማሬ ማሰማታቸው ይታወሳል። የችሎት ውሎ ተጠናቅቆ ዳኞች ከአዳራሽ ሲወጡም የቀጠለው የተከሳሾቹ መፈክር እና ዝማሬ፤ ከችሎት ታዳሚዎች የጭብጨባ ድጋፍን አግኝቶ ነበር። 

ከዚህ በፊት በነበሩት የችሎት ውሎዎች ተከሳሾች ወደ አዳራሽ ከገቡ በኋላ ታዳሚዎች እንዲገቡ ይደረግ የነበረ ቢሆንም፤ ዛሬ ግን “ጠብቁ” በሚል በጸጥታ ኃይሎች እንዳይገቡ ተደርገዋል። ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብት ተቋማት ባለሙያዎችም ቢሆን ወደ “ፍትሕ አዳራሽ” እንዲገቡ የተደረጉት፤ ችሎቱ ከተጀመረ ከደቂቃዎች በኋላ ነው። 

ይህን የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ የተቃወሙት የተከሳሽ ጠበቆች፤ አቤቱታቸውን በችሎቱ ለተሰየሙት ሶስት ዳኞች በማቅረብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል። ታዳሚዎችን “የከለከላቸው አካል ማን እንደሆነ ግልጽ አይደለም” ያሉት የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ፤ ጠበቆች በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲያቀርቡ ዕድል ሰጥተዋል። 

ተከሳሾቹን ከወከሉት ሰባት ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሄኖክ አክሊሉ፤ ታዳሚዎች “እንዳይገቡ የተደረጉት በችሎት ስነ ስርዓት አስከባሪዎች ነው። ይሄ ችሎት በፖሊስ ስልጣን ዝግ እንዲሆን እየተደረገ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። “ለተከሳሽ ቤተሰቦች እና ‘በጉዳዩ ላይ ምን እየተካሄደ ነው’ የሚለውን ማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ ችሎቱ ክፍት እንዲደረግ እናመለክታለን” ሲሉም ጠበቃው አክለዋል። 

የጠበቆቹን አቤታቱ ተከትሎ በችሎቱ የተሰየሙት ሶስት ዳኞች ለደቂቃዎች ያህል ምክክር አድርገዋል። ከምክክራቸው በኋላም ወደ ችሎቱ አዳራሽ እንዲገቡ የተፈቀደላቸው የመገናኛ ብዙሃን እና የሰብዓዊ መብት ተቋማት ባለሙያዎች ባሉበት፤ ፍርድ ቤቱ የዛሬውን ጉዳይ ለመመልከት መወሰኑን  አስታውቀዋል። ተከሳሾች “በግልጽ ችሎት የመዳኘት ህገ መንግስታዊ መብት አላቸው” ያሉት ዳኞች፤ ከዚህ ቀደም በነበረው የችሎት ውሎ ግን “ልክ ያልሆነ ነገር ተከስቷል”፤ “ችሎትን የሚያውክ ተግባር ተከናውኗል” ሲሉ ገስጸዋል።   

ተከሳሾች እና ታዳሚዎች “ህግ የማክበር ግዴታ” እንዳለባቸው ያስታወሱት ዳኞቹ፤ “የችሎት ስነ ስርዓት አስከባሪዎችም ስነ ስርዓት የማስከበር ግዴታ አለባቸው” ሲሉ የፖሊሶችን ኃላፊነት ጠቁመዋል። ዳኞቹ በመጨረሻም፤ ፍርድ ቤቱ “አሁን በገቡት ታዳሚዎች ችሎቱን ለማስቻል አቋም ወስዷል” ሲሉ ጠበቆች ያቀረቡትን አቤቱታ ውድቅ አድርገዋል። ሆኖም ከዚህ ትዕዛዝ በኋላ በጠበቆች በኩል የቀረበው ቅሬታ፤ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን “እንዲያሻሽል” አድርጎታል። 

በዛሬው ችሎት ከተገኙት ጠበቆች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ስሜነህ ኪሮስ፤ “ሚዲያ ብቻ ገብቶ [የተከሳሾች] ቤተሰቦች እንዳይገቡ ከተደረገ ችሎቱ ዝግ ሆኗል ብለን ነው የምናስበው” ሲሉ የችሎቱን ትዕዛዝ ተቃውመዋል። ሌላኛው ጠበቃ አቶ ቤተማርያም አለማየሁም በተመሳሳይ “ከዚህ በኋላ ‘ግልጽ ችሎት ተከልክሏል’ ብለን ነው የምንወስደው” ሲሉ ከባልደረባቸው ሃሳብ ጋር የሚስማማ አስተያየት ሰጥተዋል። ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ በበኩላቸው ታዳሚዎች በዛሬው ችሎት እንዲገቡ ተደርጎ፤ ስነ ስርዓቱ ምን እንደሆነ በችሎት ገለጻ እንዲደረግላቸው አመልክተዋል።

ይህን የጠበቆች አስተያተት ተከትሎ፤ የችሎቱ ዳኞች “ያነሳችሁትን ቅሬታ ሰምተናል። ህገ መከበር አለበት የሚለው ሊሰመርበት ይገባል” በማለት ቀደም ሲል የሰጡትን ትዕዛዝ አሻሽለዋል። በተሻሻለው የችሎቱ ትዕዛዝ መሰረትም፤ ታዳሚዎች አርባ ደቂቃ ገደማ ከፈጀ ክርክር በኋላ ወደ አዳራሽ እንዲገቡ ተደርጓል። የተከሳሽ ቤተሰቦች እና ሌሎች ታዳሚዎች ወደ አዳራሽ እየገቡ በነበሩበት ወቅት፤ ዳኞች የዕለቱን ጉዳይ ለመመልከት ዐቃቤ ህግ እና ጠበቆች መሰየማቸው እያረጋገጡ ነበሩ። 

በዚህ ጊዜ ተከሳሾች ችሎቱን በተመለከተ አቤቱታ ለማቅረብ እንዲፈቀድላቸው በጠበቆቻቸው በኩል ጥያቄ አቅርበዋል። ችሎቱ የዛሬ ጉዳዮችን ከጨረሰ በኋላ የተከሳሾችን አቤቱታ እንደሚቀበል በመግለጽ፤ ለዛሬ ቀጠሮ የተሰጠባቸውን ጉዳዮች መመልከት ቀጥሏል። ፍርድ ቤቱ ለዛሬ አሳድሮት የነበረው አንዱ ጉዳይ፤ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች “ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ወይስ አይገባም” በሚል ከዚህ ቀደም በተደረገው ክርክር ላይ ብያኔ መስጠት ነበር። ዐቃቤ ህግ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ ክስ ላቀረበባቸው 51 ተከሳሾች የቆጠራቸው ምስክሮች ብዛት 96 ነው።

ምስክሮቹ በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ የምስክርነት ቃላቸውን የሚሰጡ መሆኑ በዐቃቤ ህግ የክስ ሰነድ ላይ ተጠቅሷል። ከእነዚህ ተከሳሾች መካከል ሃያ ስምንቱ ክሱ የቀረበባቸው በሌሉበት መሆኑን ያስታወሰው ችሎቱ፤ ለምስክሮች የሚደረግ ጥበቃን በተመለከተ በተደረገው ክርክር ላይ “ተከሳሾች ተሟልተው ሲቀርቡ ብይን እንሰጥበታለን” ሲል በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ሳይሰጥ ቀርቷል።

ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ቀጠሮ ከሰጠባቸው ጉዳዮች ሌላኛው፤ ያልተያዙ ተከሳሾችን የፌደራል ፖሊስ ይዞ እንዲያቀርብ የሰጠውን ትዕዛዝ በተመለከተ ፖሊስ የሚሰጠውን ምላሽ ማድመጥ ነበር። ፍርድ ቤቱ ባለፈው የችሎት ውሎ ያስተላለፈው ይህ ትዕዛዝ ዘግይቶ እንደደረሰው የገለጸው ፌደራል ፖሊስ፤ “በቀጣይ ለማቅረብ እንድንችል ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን” ሲል ጠይቋል። ፍርድ ቤቱ ይህን የፖሊስን አቤቱታ ተቀብሎ፤ የተከሳሾችን አቤቱታ ወደ መስማት ተሻግሯል።   

ተከሳሾች አቤቱታቸውን በአንደኛ ተከሳሽ በኩል ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ እንዲያቀርቡ ቢፈቀድላቸውም፤ ተከሳሹ የጉዳዩን ጭብጥ ከአንድ አንቀጽ በላይ ማንበብ ሳይችሉ ቀርተዋል። የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ የሆኑት አቶ ረቡማ ተፈራ ከዳኝነት እንዲነሱ የሚጠይቀው የተከሳሾች አቤቱታ በሁለት ገጽ የተዘጋጀ ነበር። በዶ/ር ወንድወሰን መቅረብ ጀምሮ የነበረውን አቤቱታ ያቋረጡት ሰብሳቢ ዳኛው፤ “ይሄን አንሰማም። አቤቱታችሁን በጽሁፍ አቅርቡ” ሲሉ ለተከሳሾቹ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። 

ዶ/ር ወንድወሰን “በችሎት እንዲነሱልን የምንጠይቀው እርስዎን ነው። ምክንያታችንን ቤተሰቦቻችን እና ሚዲያ እንዲሰማ እንፈልጋለን” ሲሉ ለዳኛው ትዕዛዝ ምላሽ ሰጥተዋል። የችሎቱ የግራ ዳኛ፤ በሰብሳቢ ዳኛው እና በዶ/ር ወንድወሰን ሙግት መሃል ጣልቃ ገብተው “አቤቱታው በጽሁፍ ከመዝገቡ ጋር ተያይዞ ይቅረብ” ሲሉ ተመሳሳይ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። ሆኖም አንድ ተከሳሽ፤ “ቅሬታ የቀረበባቸው የመሃል ዳኛ ሊያቋርጡን አይገባም” ሲሉ የተከሳሾች አቤቱታ ሙሉ ይዘት ሊደመጥ እንደሚገባ አሳስበዋል። 

ይህ በተከሳሾች እና በዳኞች መካከል የነበረው የቃላት ምልልስ፤ ለደቂቃዎች ያለማቋረጥ ቀጥሏል። በመጨረሻም የግራ ዳኛው “ጥያቄያችሁ፣ አቤቱታችሁ በጽሁፍ መቅረብ አለበት። የምንቀበለው በጽሁፍ ሲቀርብ ነው። በቃል እንዲቀርብ አንፈቅድም” ሲሉ ችሎቱ የተከሳሾች አቤቱታ በንባብ እንዲቀርብ እንደማይፈቅድ በአጽንኦት አስገንዝበዋል። እርሳቸው ይህን ቢሉም ተከሳሾች የመናገር ዕድል ሳይጠይቁ፤ የችሎቱን ውሳኔ የሚቃወሙ ንግግሮችን አድርገዋል።

ከተከሳሾች መካከል አንዷ የሆነችው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዋ መስከረም አበራ፤ “በጣም ትንሹን የመናገር መብት ነው እየጠየቅን ያለነው” ስትል የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተቃውማለች። ሌሎች ሁለት ተከሳሾች በበኩላቸው “የታሰሩት ወንጀል ሰርተው ሳይሆን በማንነታቸው ምክንያት እንደሆነ” ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል። ተከሳሾች ቅሬታቸውን እየገለጹ ባለበት ወቅት፤ በጽሁፍ ያዘጋጁትን አቤቱታም በችሎት አስተናባሪ በኩል ለዳኞች ሰጥተዋል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የተከሳሾች አቤቱታ፤ ችሎቱን በሰብሳቢነት የሚመሩት ዳኛ “በገለልተኝነት እና በፍትሃዊነት ጉዳዮን ያዩታል” የሚል እምነት እንደሌላቸው የገለጹበት ነው። ተከሳሾች ለዚህ አቤቱታቸው በምክንያትነት የጠቀሱት ዳኛው “አማራ ጠል ናቸው” የሚል ነው። ለዚህ ማሳያ ይሆናል በሚልም፤ ዳኛው “በግል የፌስ ቡክ ገጻቸው አጋርተዋቸዋል” ያሏቸውን መልዕክቶች ቅጂ ከአቤቱታቸው ጋር በአባሪነት አያይዘዋል። 

ተከሳሾች ይህንን የጽሁፍ አቤቱታቸውን በንግግር ለማቅረብ በተደጋጋሚ ቢጠይቁም፤ ችሎቱ አቤቱታውን በጽሁፍ ተቀብሎ “ተገቢውን ትዕዛዝ” እንደሚሰጥ በመግለጽ በድጋሚ ሳይቀበለው ቀርቷል። ከዚህ የፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ ተከሳሾች የችሎቱን ውሳኔው የሚቃወም ቅሬታ ማቅረብ በመቀጠላቸው፤ የግራ ዳኛው “ችሎቱን ለማቋረጥ እንገደዳለን” በሚል ወደ ትዕዛዝ እና ተለዋጭ ቀጠሮ ወደ መስጠት ገብተዋል።

በዚህም መሰረት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ የፌደራል ፖሊስ ያልተያዙ ተከሳሾችን በአድራሻቸው ተከታትሎ ለቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ከዚህ በተጨማሪም የችሎቱን ሰብሳቢ ዳኛ በሚመለከት ተከሳሾች ያቀረቡትን አቤቱታ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት፤ ፍርድ ቤቱ ለሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት 15፤ 2016 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የችሎቱ ዳኞች ችሎቱን ለቅቀው ለመውጣት ሲሰናዱ፤ የተከሳሽ ጠበቆች “ያላለቀ ጉዳይ እንዳላቸው” ቢገልጹም ዳኞች አዳራሹን ለቅቀው ወጥተዋል። የዳኞችን መውጣት ተከትሎ፤ ተከሳሾች እና ታዳሚዎች እንደ ባለፈው የችሎቱ ውሎ ሁሉ በጭብጨባ ዝማሬ እና መፈክር አሰምተዋል። አራት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ጨምሮ፤ በዛሬው ችሎት በአካል የተገኙ ተከሳሾች ብዛት 23 ነው። ተከሳሾቹ ከሁለት ሳምንት በፊት በነበረው ችሎት በተላለፈባቸው ውሳኔ መሰረት፤ ወደ ቃሊቲ እና ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መዛወራቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)