በትግራይ ክልል ትላንት እና ዛሬ ለሶስት ጊዜ ያህል የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው ንዝረት መከሰቱ ተገለጸ  

በአማኑኤል ይልቃል

በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች ትላንት ምሽት እና ዛሬ ጠዋት፤ ለሶስት ጊዜ ያህል የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው ንዝረት መከሰቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጂኦፊዚክስ፣ ህዋ ሳይንስ እና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት አስታወቀ። በክልሉ ዋና ከተማ መቐለ እና በሌሎች አራት ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎች ንዝረቱ በአካባቢያቸው ማጋጠሙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። 

ይህን ንዝረት ያስከተለው የመጀመሪያው እና ዋናው የመሬት መንቀጥቀጥ ትላንት ማክሰኞ ሐምሌ 25፤ 2015 የተከሰተው፤ በኤርትራ ባህር ዳርቻ ዳህላክ ደሴት አካባቢ መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶሲሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በሬክተር ስኬል 5.4 ሆኖ የተለካው ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ የተመዘገበው፤ ትላንት ምሽት ሁለት ሰዓት ከ15 ደቂቃ ላይ እንደነበር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስር ባለ ኢንስቲትዩት የመሬት መንቀጥቀጥን የሚያጠናውን የትምህርት ክፍል የሚመሩት ፕሮፌሰር አታላይ አስረድተዋል። 

የትላንቱ የመሬት መንቀጥቀጥ “መለስተኛ” (moderate) የሚባል ምድብ ውስጥ የሚወድቅ ቢሆንም “የሚናቅ” እንዳልሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳይንስ ተመራማሪ እና ባለሙያው ተናግረዋል። “ይህንን ያህል መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ አዲስ አበባ [ከተማ ውስጥ] ቢፈጠር ብዙ ህንጻዎች ይወድማሉ” ሲሉ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ፕሮፌሰር አታላይ አነጻጽረዋል።   

የትላንቱ የመሬት መንቀጥቀጥ “መለስተኛ” የሚባል ምድብ ውስጥ የሚወድቅ ቢሆንም “የሚናቅ” እንዳልሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳይንስ ተመራማሪ እና ባለሙያው ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ተናግረዋል | ፎቶ፦ ኢንተርናሽናል ሳይንስ ፕሮግራም

በኤርትራ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ትላንት ምሽት እና ዛሬ ጠዋት “ንዝረት” (shock) ማስከተሉን ፕሮፌሰር አታላይ ተናግረዋል። የትላንቱ የመሬት መንቀጥቀጥ በተመዘገበበት ዳህላክ ደሴት አካባቢ፤ ዛሬ ንጋት 12፡37 አካባቢ እና ጠዋት 2፡10 ላይ ተጨማሪ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የዘርፉ ባለሙያ አክለዋል። ሆኖም የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል ምን ያህል እንደሆነ በተቋማቸው ገና ስሌቱ አለመሰራቱንም አመልክተዋል። 

በኤርትራ የባህር ዳርቻ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ምን ያህል ቦታ እንደሸፈነ መረጃው ገና እየተጠናቀረ ቢሆንም፤ በትላንናው ዕለት የተከሰተው ግን ሀገሪቱን ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስኑ የትግራይ ክልል አካባቢዎች ድረስ የተሰማ እንደሆነ ገልጸዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የሽሬ፣ አዲግራት፣ አድዋ፣ አክሱም እና መቐለ ከተማ ነዋሪዎች የመሬት መንቀጥቀጡ ያስከተለው ንዝረት በአካባቢያቸው አጋጥሞ እንደነበር ማረጋገጫ ሰጥተዋል። 

የአምስቱም ከተሞች ነዋሪዎች የትላንቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት የተከሰተው ምሽት ሁለት ሰዓት ገደማ እንደነበር ተናግረዋል። ንዝረቱ ሲጀምር በቤት እቃዎች እና ቆርቆሮዎች ላይ ንቅናቄዎች መስማታቸውን የሚገልጹት ነዋሪዎች፤ በመጀመሪያ የሁኔታውን ምንነት ወዲያውኑ ለመረዳት ተቸግረው እንደነበር ጠቁመዋል። 

የአዲግራት፣ አክሱም እና ሽሬ ነዋሪዎች የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረቱ በተከሰተበት ሰዓት “ከፍተኛ ድምጽ” መሰማቱን ገልጸዋል። አንዲት የሽሬ ከተማ ነዋሪ የተሰማውን ድምጽ “የከባድ መሳሪያ” አይነት ሲሉ ገልጸውታል። ሌላ የአዲግራት ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው፤ “የማታው በጣም ኃይለኛ ነበር። የቤት እቃዎች ሁሉ፣ በርም ሲንገጫገጭ [ነበር]። ድምጽም ሁሉም ነበረው” ሲሉ የሽሬ ከተማ ነዋሪዋን ገለጻ አስተጋብተዋል።

እኚሁ የአዲግራት ከተማ ነዋሪ፤ ዛሬ ንጋት 12 ሰዓት ገደማ ላይም በድጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት መስማታቸውን ጠቅሰው፤ ከትላንቱ ጋር ሲነጻጸር የዛሬው “ቀለል ያለ” እንደነበር ጠቅሰዋል። በዚህም ምክንያት “ብዙም ሰው ላይሰማው ይችላል” ሲሉም አክለዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የመቐለ፣ አድዋ፣ አክሱም እና ሽሬ ከተሞች ነዋሪዎች፤ ከትላንት ምሽት የመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት በኋላ ሌላ ተመሳሳይ ክስተት አለማስተዋላቸውን አስረድተዋል። 

በትግራይ ክልል ያሉ የአምስት ከተማ ነዋሪዎች፤ በመሬት መንቀጥቀጥ ንዝረት ምክንያት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች “በሰዎች ላይ ጉዳት አልደረሰም” ብለዋል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በዚሁ ክስተት የደረሰ ጉዳት መኖር አለመኖሩን ለማጣራት ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊዎች ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎች በታደርግም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም። ጉዳዩን በተመለከተ ከመቐለ እና አክሱም ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)