በአማኑኤል ይልቃል
በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አስተላለፈ። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ አርብ ሐምሌ 28፤ 2015 ባደረገው መደበኛ ስብሰባ፤ በአማራ ክልል እየተካሄደ ነው ያለውን “በትጥቅ የተደገፈ ህገወጥ እንቅስቃሴ”፤ “በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ መሸጋገሩን” ገልጿል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ይህን ውሳኔ ያሳለፈው፤ የአማራ ክልል መንግስት በክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ መደፍረስ በተመለከተ እርምጃ እንዲወስድ በትላትናው ዕለት መጠየቁን ተከትሎ ነው። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ትላንት ሐሙስ ሐምሌ 27፤ 2015 ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጻፉት ደብዳቤ፤ “በክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ መደፍረስ” “በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች” መሆኑን በመጥቀስ፤ የፌደራል መንግስት በህገ መንግስቱ መሰረት “ተገቢውን እርምጃ” እንዲወስድ ጥያቄ አቅርበው ነበር።
በዛሬው ስብሰባው ሁለት ጉዳዮችን የተመለከተው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ በአማራ ክልል የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ቅድሚያ ሰጥቶ እንደተወያየበት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በአማራ ክልል ያለውን የጸጥታ መደፍረስ “ህገወጥ እንቅስቃሴ” ሲል የጠራው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ ይህ አይነቱ እንቅስቃሴ “የክልሉን ነዋሪ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ ያወከ እና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ” እንደሆነ አስታውቋል።
ድርጊቱ “በሃገር ደህንነት እና በህዝብ ሰላም ላይ የደቀነው አደጋ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ” መምጣቱን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውይይት መነሳቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ ጠቅሷል። “የህዝብን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ” እንዲሁም “ህግ እና ስርዓት ለማስከበር” የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም መግለጫው አመልክቷል።
“የህዝብን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ” እንዲሁም “ህግ እና ስርዓት ለማስከበር” የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት መግለጫ ላይ ሰፍሯል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት “በህገመንግስቱ የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ በሙሉ ድምጽ መወሰኑንም መግለጫው አስታውቋል። ሆኖም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚነት ለምን ያህል ጊዜ የሚቆይ እንደሆነ በመግለጫው አልተጠቀሰም።
የኢፌዲሪ ህገ መንግስት “ከክልል አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ መደፍረስ ሲያጋጥም”፤ የፌደራል መንግስቱ “በክልሉ መስተዳድር ጥያቄ መሰረት የሀገሪቱን የመከላከያ ኃይል ያሰማራል” ሲል ይደነግጋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)