በጎንደር ዩኒቨርስቲ የ12ተኛ ክፍል ፈተና ፈታኝ እና ሁለት ፖሊሶች መገደላቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ

በአማኑኤል ይልቃል

በጎንደር ዩኒቨርስቲ የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሲሰጥ የነበረ አንድ ፈታኝ እና ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት መገደላቸውን እንዲሁም አንዱ መቁሰሉን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ግድያውን የፈጸሙት “የታጠቁ ኢ-መደበኛ ኃይሎች” መሆናቸውን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል። 

የትምህርት ሚኒስቴር ይህንን ያስታወቀው የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መጠናቀቅን አስመልክቶ ዛሬ አርብ ሐምሌ 28፤ 2015 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። ዛሬ ጠዋት የተጠናቀቀውን ይህንን ፈተና 840,859 ተማሪዎች መፈተናቸውን መግለጫውን የሰጡት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል። 

ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እንዲሰጥ የተደረገውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና፤ ተማሪዎች የወሰዱት በሁለት ዘርፍ ተከፍለው ነው። ቀድመው ወደ ዩኒቨርስቲዎች እንዲገቡ የተደረጉት የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች፤ ከሐምሌ 19፤ 2015 ጀምሮ ፈተናውን ተፈትነው አጠናቅቀዋል። ከዚህ ሳምንት ማክሰኞ እስከ ዛሬ አርብ ድረስ ደግሞ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች በፈተና ላይ ቆይተዋል።  

የዘንድሮው የፈተና አሰጣጥ “እጅግ ስኬታማ” እንደነበር በዛሬው መግለጫቸው ላይ የተናገሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ያጋጠሙ ችግሮችንም በዝርዝር ጠቅሰዋል። የትምህርት ሚኒስትሩ ካጋጠሙ ችግሮች ውስጥ በቀዳሚነት የጠቀሱት፤ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ሶስት ካምፓሶች በትላንትናው ዕለት ተፈጥሯል ያሉትን ክስተት ነው።

በዕለቱ “በአካባቢው ያሉ የታጠቁ ኢ-መደበኛ ኃይሎች በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ተኩስ መክፈታቸውን” ተከትሎ፤ በተካሄደ  የተኩስ ልውውጥ በጎንደር ዩኒቨርስቲ የ12ተኛ ክፍል ፈተና ሲሰጥ የነበረ አንድ ግለሰብ እና ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባሎች መገደላቸውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል። አንድ የፌደራል ፖሊስ አባልም መቁሰሉን የትምህርት ሚኒስትሩ አክለዋል።

በዚህ ክስተት ምክንያትም በጎንደር ዩኒቨርስቲ “ማራኪ”፣ “ቴዎድሮስ” እና “ፋሲል” ካምፓሶች የ12ተኛ ክፍል ፈተና ሲፈተኑ የነበሩ 16 ሺህ ገደማ ተማሪዎች፤ ትላንት ከሰዓት እና ዛሬ ጠዋት የተሰጡትን ፈተናዎች አለመውሰዳቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል። “እነኚህ [ተማሪዎች ያልተፈተኑት] በእነሱ ፍላጎት ሳይሆን በደረሰው [ችግር] ስለሆነ በምን መልክ እንደምናስተናግዳቸው አንዴ ሁኔታው ከተጠናቀቀ በኋላ የምናየው ይሆናል” ሲሉ ፈተናውን ላልወሰዱት ተማሪዎች ሌላ አማራጭ እንደሚዘጋጅ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ጠቁመዋል።

በአማራ ክልል አሁን ባለው የጸጥታ ሁኔታ፤ ተማሪዎች እና ፈታኞችን ወደ መጡባቸው አካባቢዎች የማመላለስ ስራ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው የትምህርት ሚኒስትሩ፤ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ሶስት ካምፓሶች ላይ ካጋጠመው ችግር ውጪ በክልሉ በሚገኙት ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች የተሰጠው ፈተና “በሰላም መጠናቀቁን” ተናግረዋል። “ተማሪዎችን፣ ፈታኞችን በሰላም መመለስ እንደ ዋና ኃላፊነታችን አድርገን ነው የምንወስደው” ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ ተማሪዎቹን የማጓጓዝ ስራው መጀመሩን ገልጸዋል።

ይህ ስራ እየተከናወነ ያለው “በአካባቢው ሽማግሌዎች፣ የአካባቢው መስተዳድር አመራሮች እና ወላጆች ተባብረው” እንደሆነም አስረድተዋል። ይሁንና ይህ ስራ በሁሉም ቦታዎች ተፈጻሚ አለመሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ አልሸሸጉም። የአውሮፕላን በረራ በተቋረጠባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የፈተና አስፈጻሚዎች፤ “ሁኔታው እስከሚረጋጋ ድረስ ትንሽ ቀን” መጠበቃቸው ግድ እንደሆነ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። 

በዘንድሮው የ12ተኛ ክፍል ፈተና በሚሰጥበት ወቅት ከጎንደር ዩኒቨርስቲ በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች ያጋጠሙ ችግሮችም እንደነበሩ በዛሬው መግለጫ ላይ ተነስቷል። በጋምቤላ ዩኒቨርስቲ በተከሰተ “የምግብ ብክለት” ፈተናውን ለመውሰድ ከገቡ ተማሪዎች መካከል “ከ300 እስከ 400” የሚደርሱ ተማሪዎች ሆስፒታል ገብተው እንደነበር ተገልጿል። ከእነዚህ ተማሪዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ ፈተናውን ሲወስዱ፤ 38 ያህሉ ግን ፈተናውን ሳይወስዱ ቀርተዋል ተብሏል። 


የትምህርት ሚኒስትሩ በዛሬው መግለጫቸው ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደው ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል፤ ከአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቤቶች “በመጡ ተማሪዎች ላይ” ታይቷል የተባለው “የቡድን ጸብ” አንዱ ነው። ለፈተና ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የገቡ ተማሪዎች በትምህርት ቤቶቻቸው ተቧድነው ጸብ መፍጠራቸውን የተናገሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ይህ ድርጊት “በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ” ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አምስት ኪሎ፣ አራት ኪሎ እና ልደታ ካምፓሶች የቡድን ጸብ እንደነበር የዘረዘሩት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ “ከሁሉም ትንሽ የከፋ” ያሉት ድርጊት የተፈጸመው ግን በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ካምፓስ እንደሆነ ተናግረዋል።  በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ካምፓስ የነበሩ ተማሪዎች “በቡድን ሆነው ተማሪዎችን ከማስፈራራት እና ከመስረቅ ባሻገር የተማሪዎችን የመኝታ ቤት በር እና መስታወት እንዲሁም የተማሪ ሎከር እንደሰበሩ” ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡ 

ከእነዚህ ድርጊቶች ጋር በተያያዘ 87 ተማሪዎች ላይ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ጠቁመዋል። ከእነዚህ ውስጥ 49 ያህሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ካምፓስ ከተፈጸመው ድርጊት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆኑንም አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]