ነባሩ የደቡብ ክልል፤ በህዝበ ውሳኔ ለተመሰረተው አዲሱ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል ስልጣን አስረከበ

በሃሚድ አወል

አስራ ሁለተኛ ክልል በመሆን ፌዴሬሽኑን የተቀላቀለው አዲሱ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል፤ ከነባሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ስልጣን ተረከበ። ነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለአዲሱ ክልል ስልጣኑን ያስረከበው፤ ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 29፤ 2015 ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ነው።

አዲሱን ክልል በህዝበ ውሳኔ የመሰረቱት ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ምክር ቤቶች አፈጉባኤዎች፤ የየመጡባቸውን “ህዝብ ወክለው” ስልጣኑን ከነባሩ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ ተረክበዋል። አዲሱን የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል የመሰረቱት የጌዲኦ፣ የወላይታ፣ የጋሞ፣ ጎፋ፣ የኮንሶ፣ የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ የደራሼ፣ የባስኬቶ እና የአሌ ልዩ ወረዳዎች ናቸው። 

የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለ12ኛው ክልል ስልጣን ከማስረከቡ በፊት፤ በነባሩ እና በአዲሱ ክልል መካከል የሚኖረው አስተዳደራዊ እና ህጋዊ ጉዳዮች የሚመሩበትን ስርዓት ለመወሰን የቀረበ የውሳኔ ሃሳብ ላይ ውይይት አድርጓል። የክልሉ ምክር ቤቱ ከዚህ በፊት በህዝበ ውሳኔ ለተመሰረቱ ሁለት ክልሎች ስልጣን ሲያስረክብም ተመሳሳይ አካሄድን መከተሉ ይታወሳል። 

ነባሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ከ2012 መጨረሻ ወዲህ ባሉት ሶስት ዓመታት በህዝበ ውሳኔ ለተመሰረተ ክልል ስልጣን ሲያስረክብ የዛሬው ሶስተኛው ነው። ከዚህ በፊት ለሲዳማ ክልል እና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በተመሳሳይ ሂደት ስልጣን አስረክቧል።  

ዛሬ በነባሩ እና በአዲሱ ክልል መካከል የተደረገው የስልጣን ርክክብ የደቡብ ክልልን መዋቅር፣ ስያሜ እና ህገ መንግስቱን እንዲቀይር ያደርገዋል። የደቡብ ክልል ምክር ቤት ከትላንት ጀምሮ ሲያካሄደው የቆየው ስብሰባ፤ “የክልሉን ቅርጽ ይዞ የተጓዘበትን ምዕራፍ የሚያጠናቅቅበት የመጨረሻ ጉባኤ” መሆኑን የነባሩ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)