በክልሎች መካከል የሚኖረው የንብረት ክፍፍል የተፈጻሚነት ወሰን፤ በደቡብ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ጥያቄ አስነሳ 

በሃሚድ አወል

በነባሩ የደቡብ ክልል እና በአዲሱ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል መካከል የሚኖረውን የንብረት ክፍፍል በተመለከተ የቀረበ የውሳኔ ሃሳብ (ሞሽን) በደቡብ ክልል ምክር ቤት አባላት ጥያቄ አስነሳ። የክልሉ ምክር ቤት አባላት ጥያቄውን ያነሱት፤ የንብረት ክፍፍሉ በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ላይ ጭምር “ተፈጻሚ ይሆናል” በመባሉ ነው።

ለጥያቄዎች መነሻ የሆነውን የውሳኔ ሃሳብ ዛሬ ቅዳሜ ሐምሌ 29፤ 2015 በተካሄደው የደቡብ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ያቀረቡት፤ አዲሱን ክልል የሚያደራጀው ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ኑርዬ ሱሌ ናቸው። የውሳኔ ሃሳቡ፤ በነባሩ የደቡብ ክልል እና ዛሬ በይፋ ስልጣን በተረከበው የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል መካከል የሚኖረውን አስተዳደራዊ እና ህጋዊ ጉዳዮች የሚመሩበትን ስርዓት የያዘ ነው።

በስድስት ክፍሎች በተዘጋጀው የውሳኔ ሃሳብ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል፤ የተፈጻሚነት ወሰንን የሚያትተው ይገኝበታል። በነባሩ እና በ12ኛነት ፌዴሬሽኑን በተቀላቀለው ክልል መካከል የሚነሳው የሃብት እና ዕዳ ክፍፍል፤ በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆንም በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ሰፍሯል። 

የቀድሞው ሲዳማ ዞን ከነባሩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል በመነጠል፤ በህዝበ ውሳኔ የራሱን ክልል የመሰረተው ከሶስት ዓመታት በፊት በ2012 ዓ.ም ነበር። በነባሩ ክልል ስር የነበሩ አምስት ዞኖች እና አንድ ልዩ ወረዳ ተመሳሳይ አካሄድ በመከተል “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች” የተሰኘ 11ኛ ክልል ባለፈው ዓመት መመስረታቸው ይታወሳል። ዛሬ ለደቡብ ምክር ቤት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ፤ በእነዚህ ሁለት ክልሎች ላይ “ተፈጻሚ ይሆናል” መባሉ ግን በምክር ቤት አባላት ዘንድ ግርታ ፈጥሯል። 

አንድ የደቡብ የምክር ቤት አባል በውሳኔ ሀሳቡ የቀረበው የንብረት ክፍፍል፤ በነባሩ እና በአዲሱ ክልሎች መካከል ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል” መሆኑን ጠቁመዋል። ሆኖም ምክር ቤቱ የሚያወጣው ህግ “በሲዳማ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ላይ ተፈጻሚ ሊሆን የሚችልበት አግባብ ያለ አይመስለኝም” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

አቶ ሳኒ ረዲ የተባሉ ሌላ የክልሉ ምክር ቤት አባልም፤ “ራሳቸውን ችለው ህገ መንግስት አጽድቀው በወጡ ክልሎች ላይ ይሄ ህግ አውጪ ምክር ቤት አዋጅ ሊያወጣባቸው አይችልም” ሲሉ ተመሳሳይ ይዘት ያለው አስተያየት ሰንዝረዋል። አቶ ሳኒ አክለውም ከሲዳማ እና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጋር የሚደረገው የንብረት እና ዕዳ ክፍፍል ጉዳይ፤ “በስምምነት መሰረት” ሊካሄድ እንደሚገባ አመልክተዋል። 

ፎቶ:- የደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ እና ነባሩን ክልል በአዲስ የማደራጀት ተግባር ማስፈጸሚያ ጽህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ኑርዬ ሱሌ ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፤ የውሳኔ ሃሳቡ የተፈጻሚነት ወሰን “በመርህ ደረጃ” በነባሩ እና በአዲሱ ክልል ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። ሆኖም ከሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ጋር ያለው የንብረት ክፍፍል እስካሁንም “እልባት አለማግኘቱ”፤ የውሳኔ ሃሳቡ የተፈጻሚነት ወሰን እነርሱንም እንዲያካትት ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

ነባሩ ክልል በህዝበ ውሳኔ ከተመሰረቱት የሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ጋር የሚኖረውን የንብረት ክፍፍል በተመለከተ፤ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ሞሽኖች በዚሁ ምክር ቤት መጽደቃቸውን አቶ ኑርዬ በማብራሪያቸው ላይ አስታውሰዋል።  ከሲዳማ ክልል ጋር የስልጣን ርክክብ ሲደረግ የጸደቀው ሞሽን፤ ታሳቢ አድርጎ የነበረው የሲዳማ እና ደቡብ ክልልን ብቻ መሆኑንም ምክትል ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።  

“በዚያ ሞሽን መሰረት ተግባራቱ ሳይጠናቀቁ፤ ገና የተሽከርካሪ ክፍፍል ብቻ ከተፈጸመ በኋላ፤ ሌላው ንብረት እንዳለ በሞሽኑ መሰረት ሳይፈጸም፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሆኖ ወጥቷል። [በዚህም] ምክንያት ቀደም ሲል ታሳቢ የተደረገው ሁለት ክልል ሶስት ሆነ” ሲሉ በሲዳማ እና ደቡብ ክልል መካከል ሊፈጸም ይገባ የነበረው የሃብት ክፍፍል ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አለመደረጉን አብራርተዋል። 

ፎቶ:- ደቡብ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተመሰረተ በኋላም፤ በተመሳሳይ ሁኔታ የጸደቀው ሞሽን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሳይደረግ አዲሱ “የደቡብ ኢትዮጵያ” ክልል መመስረቱን አቶ ኑርዬ ጠቅሰዋል። አዳዲሶቹ ክልሎች ከመመስረታቸው በፊት፤ ከነባሩ ክልል ጋር በአንድ ላይ ያፈሯቸው “ቁሳዊ እና ሰብዓዊ ሀብቶች” እልባት አለማግኘታቸው፤ ዛሬ በደቡብ ክልል ምክር ቤት አባላት ጥያቄ የቀረበበትን ችግር መፍጠሩን ምክትል ስራ አስኪያጁ አስገንዝበዋል። 

ዛሬ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ፤ የሃብት እና ዕዳ ክፍፍል የተፈጻሚነት ወሰንን በሚመለከት ሲዳማ እና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች የተካተቱት በዚህ ምክንያት መሆኑንም ተናግረዋል። “አራቱም ክልሎች በጋራ የሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ፣ የአራቱንም ክልሎች concern በተመለከተ፤ ይሄው ምክር ቤት በዚሁ ሞሽን ላይ ውሳኔ ማሳለፍ ስላለበት ነው” ሲሉ የውሳኔ ሃሳቡ በዚህ መልክ የቀረበበትን ምክንያት አስረድተዋል።

የንብረት እና ዕዳ ክፍፍልን በሚመለከት ተግባራዊ የሚደረጉ የህግ ማዕቀፎች የዘረዘረው የዛሬው የውሳኔ ሃሳብ፤ ከሲዳማ ክልል ምስረታ ጀምሮ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስኪደራጅ ድረስ በነባሩ ክልል ምክር ቤት የቀረቡ “ሞሽኖች” “እንደ አስፈላጊነታቸው ስራ ላይ ይውላሉ” ሲል ይደነግጋል። አራቱ ክልሎች በጋራ የሚደርሱባቸው የስምምነት ሰነዶች፣ የተጠቀሟቸው ቃለ ጉባኤዎች እና የንብረት ክፍፍልን የተመለከቱ የውሳኔ ሪፖርቶችም በተመሳሳይ መልኩ ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ሰፍሯል።

ከእነዚህ በተጨማሪ ክልሎቹ በአብሮነት ዘመናቸው ሲጠቀሙባቸው የነበሩ የፋይናንስ እና የንብረት ህግጋት፣ የፌደራል የፋይናንስ እና የንብረት ህግጋት እንዲሁም የኢትዮጵያ የፍትሐብሔር ህግ እና ሌሎች ተዛማጅ የሆኑ ህግጋቶች “እንደ አስፈላጊነታቸው” ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሚችሉ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ተዘርዝሯል። እነዚህን ድንጋጌዎች የያዘው የውሳኔ ሃሳብ፤ በዛሬው የደቡብ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ የጸደቀው በ10 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)