በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች “አንዳንድ የዞን እና የወረዳ ከተሞችን መቆጣጠራቸውን” አቶ ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ

በሃሚድ አወል

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች “አንዳንድ የዞን እና የወረዳ ከተሞችን መቆጣጠራቸውን” እንዲሁም በተወሰኑ ቦታዎች “ወንጀለኞችን ከማረሚያ ቤት ማስለቀቃቸውን” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢ አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስታወቁ። አቶ ተመስገን “ዘራፊ ኃይል” ሲሉ የጠሯቸውን አካላት፤ “የክልሉን መንግስት በማፍረስ ወደ ፌደራል ስርዓት የመሄድ” ፍላጎት እና ግብ ያላቸው መሆናቸውን ተናግረዋል። 

አቶ ተመስገን ጥሩነህ ይህን የተናገሩት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ቀጣይ ስራዎችን በተመለከተ ዛሬ ሐምሌ 30፤ 2015 ከተደረገ ስብሰባ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ ነው። የዕዙ ሰብሳቢ በዚሁ ማብራሪያቸው፤ በጎጃም አካባቢ ላይ የተከሰቱ የጸጥታ መደፍረሶች፤ በርካታ “ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮችን በህብረተሰቡ ላይ ፈጥሯል” ብለዋል። በዚሁ አካባቢ “የመንቀሳቀስ መብትን የሚገድቡ ሁኔታዎች” መስተዋላቸውን አክለዋል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ዋና ዳይሬክተሩ “ኢ-መደበኛ” ሲሉ የገለጿቸው አደረጃጀቶች፤ “አንዳንድ የዞን ከተሞችን እና የወረዳ ከተሞችን በመቆጣጠር፤ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን፤ የጸጥታ አካላት እንዲሁም አንዳንድ ቦታ ላይ ወህኒ ቤቶችን ወይንም ደግሞ ማረሚያ ቤቶችን ሳይቀር በመፍታት ወንጀለኞችን እስከማስለቀቅ የደረሱባቸው ወረዳዎች አሉ” ብለዋል።

“አንዳንድ የዞን ከተሞችን እና የወረዳ ከተሞችን በመቆጣጠር፤ የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማትን፤ የጸጥታ አካላት እንዲሁም አንዳንድ ቦታ ላይ ወህኒ ቤቶችን ወይንም ደግሞ ማረሚያ ቤቶችን ሳይቀር በመፍታት ወንጀለኞችን እስከማስለቀቅ የደረሱባቸው ወረዳዎች አሉ”

አቶ ተመስገን ጥሩነህ – የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢ

በአማራ ክልል የተስተዋሉት ሁኔታዎች የክልሉ አርሶ አደር እና ህዝብ፤ “ተረጋግቶ አሁን ያለውን የሰብል ልማት እና አጠቃላይ ማህበራዊ ልማቱን እንዳያፋጠን የሚያደርግ እንቅፋት” መፍጠሩን አቶ ተመስገን አመልክተዋል። በዚህም ምክንያት “እነዚሀን ለመመለስ የኦፕሬሽን ስራዎች ይሰራሉ” ሲሉ በቀጣይ የሚወሰዱ እርምጃዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። “በሚቀጥሉት ቀናት የኦፕሬሽን ስራዎች የህዝብ ግንኙነት ስራዎች የፓርቲ እና የመንግስት አደረጃጀት እና መዋቅር የማጠናከር ስራዎች ይሰራሉ” ሲሉም አክለዋል።

የእነዚህ ስራዎች ዝርዝር እና የስራ ክፍፍል፤ ዛሬ በተካሄደው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ስብሰባ ላይ መቅረቡን አቶ ተመስገን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከትላንት በስቲያ አርብ ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ይህንኑ የሚያስፈጽመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በስሩ ግብረ ኃይሎችን ወይም ኮሚቴዎችን ሊያቋቁም እንደሚችል ደንግጓል። ዕዙ በዚሁ መሰረት የራሱን ጽህፈት ቤት ጨምሮ በስሩ አራት መምሪያዎች ማደራጀቱን ዋና ሰብሳቢው አስረድተዋል። 

ለስድስት ወር ጸንቶ የሚቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በዋነኛነት ተፈጻሚ የሚሆንበት የአማራ ክልል በአራት “ኮማንድ ፖስት” መከፈሉን አቶ ተመስገን በዛሬው ማብራሪያቸው አስረድተዋል። “የምዕራብ አማራ ኮማንድ ፖስት” የሚል መጠሪያ የተሰጠው መዋቅር፤ የአማራ ክልል መንግስት መቀመጫ ባህር ዳር ከተማን ጨምሮ ምስራቅ ጎጃም ዞን፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን እና የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደርን በስሩ የሚይዝ ነው። ጥንታዊቷ ደብረ ማርቆስ ከተማ የተካተተችበት ይህ ኮማንድ ፖስት፤ “መቀመጫውን ራሱ የሚወስን ይሆናል” ሲሉ አቶ ተመስገን ተናግረዋል።


“የሰሜን ምዕራብ አማራ ኮማንድ ፖስት” ተብሎ የሚጠራው ሁለተኛው መዋቅር ጎንደር እና ደብረ ታቦርን ከተሞችን ጨምሮ የቀድሞው ሰሜን ጎንደር ዞን የአሁኑ ሰሜን ምዕራብ ጎንደር ዞን፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን እንዲሁም ደቡብ ጎንደር ዞንን በስሩ ያደረገ ነው። “ማዕከላዊ ሸዋ ኮማንድ ፖስት” የሚባለው ሶስተኛው መዋቅር ከደብር ብርሃን ከተማ ጀምሮ እስከ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ድረስ ያሉትን የሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢዎች ያካለለ ነው።  

ደቡብ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች፣ የዋግ ኽምራ ዞን እንዲሁም ደሴ፣ ኮምቦልቻ እና ወልዲያ ከተሞች ደግሞ “ምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት” በተባለ መዋቅር ስር እንዲሆኑ መደረጋቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ዋና ሰብሳቢ አስታውቀዋል። ኮማንድ ፖስቶቹን የሚመሩት አባላት ከመከላከያ ሰራዊት፣ ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከክልሉ መንግስት፣ ከገዢው ብልጽግና ፓርቲ እና ከኮሙኒኬሽን የተውጣጡ መሆናቸውን አቶ ተመስገን ገልጸዋል። 

“ይህ ኮማንድ ፖስት ዛሬ አጠቃላይ የኮማንድ ፖስቱን፣ የጠቅላይ መምሪያ ዕዙን እና የመምሪያዎችን ዕቅድ አይቷል፤ አጽድቋል። በሚቀጥሉት ቀናት የኦፕሬሽን ስራዎች፣ የህዝብ ግንኙነት ስራዎች፣ እንዲሁም የፓርቲ እና የመንግስት አደረጃጀት እና መዋቅር የማጠናከር ስራዎች ይሰራሉ፡፡ ህግ እና ስርዓት የማስከበር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉ የዕዝ ዋና ሰብሳቢ አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]