ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ለአራተኛ ጊዜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋለ 

በሃሚድ አወል

“አልፋ ሚዲያ” የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን መስራች እና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው፤ ትላንት እሁድ ሐምሌ 30፤ 2015 የሁለተኛ ዲግሪ የምርቃት ስነ ስርዓት ተሳትፎ ወደ መኖሪያ ቤቱ ከተመለሰ በኋላ በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋሉን ቤተሰቦቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በጋዜጠኛ በቃሉ መኖሪያ ቤት ዛሬ ማለዳ ከ12፡30 ጀምሮ ለአንድ ሰዓት ያህል የቆየ ፍተሻ መካሄዱንም ቤተሰቦቹ ገልጸዋል። 

ሶስት የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ እና ሲቪል የለበሱ የጸጥታ አካላት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ አካባቢ ወደሚገኘው የጋዜጠኛው መኖሪያ ቤት በመጀመሪያ የመጡት ትላንት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ገደማ እንደሆነ ቤተሰቦቹ አስረድተዋል። የሁለተኛ ዲግሪ ምርቃቱን ከቤተሰቦቹ ጋር እያከበረ የነበረውን ጋዜጠኛ በቃሉን፤ “ለጥያቄ እፈልግሃለን” ብለው ሜክሲኮ አካባቢ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንደወሰዱትም አክለዋል።

ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአማርኛ ቋንቋ እና ስነ ጽሁፍ መጀመሪያ ዲግሪውን ያገኘው በቃሉ፤ በትላንትናው ዕለት ከ“ኒው ጀነሬሽን” ዩኒቨርሲቲ በ“Global study and international relations” በማስተርስ ዲግሪ ተመርቋል። ጋዜጠኛው ይህን ትምህርት የተከታተለው “ከመሳደድ እና እስር ጎን ለጎን” መሆኑን ከምርቃቱ በኋላ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ጽፎ ነበር። 

በቃሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለአራት ጊዜያት ያህል በእስር ላይ ቆይቷል። ጋዜጠኛው ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት፤ ፖሊስ “ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት” እንደጠረጠረው ገልጾ ነበር። በቃሉ የተጠረጠረበትን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ ጋዜጠኛው በአስር ሺህ ብር ዋስትና እንዲፈታ በመወሰኑ ከአንድ ወር እስር በኋላ መለቀቁ ይታወሳል። 

ጋዜጠኛ በቃሉ በጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም “አውሎ ሚዲያ” የተሰኘው መገናኛ ብዙሃን ዋና አዘጋጅ በነበረበት ወቅት፤ በተመሳሳይ መልኩ ለ16 ቀናት ከታሰረ በኋላ በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር ተፈትቷል። ዋና አዘጋጁ በወቅቱ የተጠረጠረው “ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት እና የመንግስት ስም በማጥፋት” ወንጀል” ነበር።

በቃሉ ከዚህ እስር ዘጠኝ ወራት በኋላ “ማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ ተንቀሳቅሷል” በሚል ከ16 የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና ሰራተኞች ጋር በድጋሚ በቁጥጥር ስር ውሏል። ጋዜጠኛ በቃሉ እና አብረውት የታሰሩ ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እና ሰራተኞች፤ በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ኪሎ ከተማ በሚገኝ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ ለ49 ቀናት ከቆዩ በኋላ በዋስትና መለቀቃቸው አይዘነጋም። 

ጋዜጠኛ በቃሉ ትላንት ለአራተኛ ጊዜ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ፤ ወደ 11 አንድ ሰዓት ገደማ አሁን በእስር ላይ በሚገኝበት የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ልብስ እና ምግብ እንዳደረሱለት ቤተሰቦቹ ተናግረዋል። ዛሬ ማለዳ በሶስት የፌደራል ፖሊስ ደንብ ልብስ የለበሱ ፖሊሶች ታጅቦ ወደ መኖሪያ ቤቱ የመጣው በቃሉ፤ ሲቪል በለበሱ የጸጥታ አባላት ፍተሻ ሲደረግ መመልከቱን ገልጸዋል። የጸጥታ አባላቱ ፍተሻውን ካጠናቀቁ በኋላ የበቃሉን ላፕቶፕ ኮምፒዩተር፣ “ሲዲ” እና “ፍላሽ ዲስክ” መውሰዳቸውን ቤተሰቦቹ አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)