በአማኑኤል ይልቃል
በአማራ ክልል የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት፤ በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የተጀመሩ “የሰላም ጥረቶች እና ስምምነቶች” በክልሉም መደረግ የሚችልበት ዕድል እንዲፈለግ ዘጠኝ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጠየቁ። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ወቅት የጸጥታ አካላት “ያልተመጣጠነ ኃይል እንዳይጠቀሙ”፣ “ብሔርን መሠረት ያደረጉ ማግለሎች እና ጥቃቶች እንዳይስፋፉ” እንዲሁም “የጅምላ እስሮች” እንዳይፈጸሙም ድርጅቶቹ ጠይቀዋል።
ዘጠኙ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት፤ በአማራ ክልል የተከሰተው “ግጭት እና አለመረጋጋት በከፍተኛ ጥንቃቄ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲገኝለት” ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 1፤ 2015 ባቀረቡት ጥሪ ነው። ይህንን ጥሪ ካቀረቡት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መካከል የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር እና የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ይገኙበታል።
አዲስ ፓወር ሀውስ፣ የኢትዮጵያ ሴቶችና ሕፃናት ማህበራት ህብረት፣ የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት እንዲሁም ሴታዊት ንቅናቄ፤ የሰላም ጥሪውን ያቀረቡ ሌሎች ድርጅቶች ናቸው። “ግጭቶችን የመከላከል እና ሰላም የማስፈን” ጥረት ጊዜ የማይሰጠው “አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን እናምናለን” ያሉት ድርጅቶቹ፤ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭት “እጅግ እንዳሳሰባቸው” በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ፤ “ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ስር እየሰደዱ እና እየተስፋፉ” መሆኑን ያነሱ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት “ግጭቶችን ለማስቆም የሚወሰዱ እርምጃዎች የብዙሃንን ደህንነት፣ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች እና ነጻነቶች አደጋ ላይ የማይጥሉ” መሆን አለባቸው የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። ድርጅቶቹ በዛሬው መግለጫቸው “የመብት ጥሰት” ስጋታቸውን ካንጸባረቁባቸው ጉዳዮች ውስጥ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም ጉዳይ አንዱ ነው።
ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ወቅት የጸጥታ አካላት ያልተመጣጠነ ኃይል እንዳይጠቀሙ” ሲሉ ጠይቀዋል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አፈጻጸም ሂደት ውስጥ “ብሔርን መሠረት ያደረጉ ማግለሎች እና ጥቃቶች እንዳይስፋፉ” እንዲሁም “የጅምላ እስሮች (indiscriminate mass arrests) እንዳይከናወኑም” ጥሪ አቅርበዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው አርብ የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ፤ ከዚያኑ ዕለት አንስቶ በአማራ ክልል ከተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ጋር “ግንኙነት ያላቸው፣ ጉዳዮችን የሚያባብሱ፣ ስምሪት የሚሰጡ” የተባሉ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር መዋል እንደተጀመረ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማስታወቁ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመውን ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ በዋና ሰብሳቢነት የሚመሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ትናንት እሁድ በሰጡት መግለጫም፤ በቀጣይ ቀናት የሚወሰዱ እርምጃዎች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የሚወጡ መመሪያዎች እና ደንቦች፤ “ለዜጎች ተደራሽ በሆኑ አማራጮች በተከታታይ እንዲደርሱ” በዛሬው መግለጫቸው ላይ ጠይቀዋል። ድርጅቶቹ በዚሁ መግለጫቸው መንግስት እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች፤ በግጭቶች ወቅት “በሰብዓዊ መብቶች እና በሰብዓዊ ህግጋት (humanitarian laws) እንዲመሩ” እና የንፁሃንን ደህንነት እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።
ተፈላሚ ወገኖች “በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እና ሌሎችም ጉዳቶች በክልሉ እንዳይፈጸሙ ከፍተኛ የመከላከል ስራዎች እንዲያከናወኑ እና የተጠያቂነት ስርዓት እንዲዘረጋ” ድርጅቶቹ በመግለጫቸው አሳስበዋል። በአማራ ክልል እና አጎራባች አካባቢዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች ሰብአዊ እርዳታዎች “በአግባቡ እንዲደርሱ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግ” ጥሪ አስተላልፈዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት መንስኤዎች እና ዘላቂ መፍትሔው፤ በሚመለከታቸው አካላት ተለይቶ መቅረብ እንዳለበት በመግለጫቸው ላይ አንስተዋል። ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ “የበኩላቸውን ግፊት ማድረግ አለባቸው” በሚል በመግለጫው የተዘረዘሩ አካላት፤ የሲቪል ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የእምነት ተቋማት፣ መገናኛ ብዙሃን እና የሀገር ሽማግሌዎች ናቸው።
በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች የተጀመሩ የሰላም ጥረቶች እና ስምምነቶች፤ “በአማራ ክልል በሚንቀሳቀሱ ወገኖች እና በፌዴራሉ እና የክልሉ መንግሥታት መካከል መደረግ የሚችልበት ዕድል እንዲፈለግም” ዘጠኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዛሬው መግለጫቸው ጥሪ አቅርበዋል። የማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እና ብዙሃን መገናኛዎችም “ግጭት አገናዛቢ አዘጋገብን በመተግበር፣ ሀሰተኛ እና የተዛቡ መረጃዎችን ስርጭት በመግታት እንዲሁም “ሐቁን የሚያንጸባርቁ መረጃዎችን ብቻ ለዜጎች በማድረስ” ግጭት ከማባባስ እንዲቆጠቡም ድርጅቶቹ በመግለጫቸው አሳስበዋል።
በአንድ ላይ የተሰባሰቡ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሰላም ጥሪ ሲያቀርቡ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም። ሃያ አራት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች “በኢትዮጵያ እየተስተዋሉ ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ” ተመሳሳይ የሰላም ጥሪ በጳጉሜ 2013 ማቅረባቸው ይታወሳል። ከዚህ ሁነት አንድ ዓመት በኋላም፤ 35 ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰሜን ኢትዮጵያ እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች “በአስቸኳይ ቆመው ሐቀኛ እና ሰላማዊ የእርቅ ንግግሮች እንዲጀመሩ” ጥሪ ማቅረባቸው አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)