በሃሚድ አወል
በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙት የፓርላማ አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ ተሻገር በጠበቆቻቸው አማካኝነት “አካልን ነጻ የማውጣት” (habeas corpus) አቤቱታ ለፍርድ ቤት አቀረቡ። አቤቱታው የቀረበለት ፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት፤ የፌደራል ፖሊስ በጽሁፍ ምላሽ እንዲሰጥ አዝዟል።
የአቶ ክርስቲያን እና ዶ/ር ካሳ ጠበቆች አቤቱታቸውን ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 2፤ 2015 ያቀረቡት፤ የፌደራል ፖሊስ ያለመከሰስ መብት ያላቸው ደንበኞቻቸውን ካለፈው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ “ያለምንም ፍርድ በእስር ላይ ያቆያቸው” መሆኑን በመጥቀስ ነው። በጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ እና ሰለሞን ገዛኸኝ አማካኝነት የቀረበው አቤቱታ፤ በምክር ቤት የህዝብ ተወካዮቹ የተያዙበትን መንገድ ለፍርድ ቤቱ አብራርቷል።
በአንድ ገጽ የተዘጋጀው ይህ አቤቱታ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ ባለፈው ሳምንት አርብ ከመኖሪያ ቤታቸው “እየተደበደቡ ተይዘው” በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መታሰራቸውን አትቷል። ዶ/ር ካሳ ተሻገርም በዚሁ ቀን ከለሊቱ ስድስት ሰዓት ገደማ በፌደራል ፖሊስ ተይዘው፤ በተመሳሳይ ቦታ ታስረው እንደሚገኙ በአቤቱታው ላይ ሰፍሯል። የፌደራል ፖሊስ ሁለቱንም ግለሰቦች የያዛቸው “ለጥያቄ እፈልጋቸዋለሁ” በሚል መሆኑንም በአቤቱታው ተመላክቷል።
ተቃዋሚውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው ፓርላማ የገቡት አቶ ክርስቲያን፤ በህገ መንግስቱ ያለመከሰስ መብት ተሰጥቷቸዋል። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት “ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም፤ በወንጀልም አይከሰስም” ሲል ይደነግጋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የብልጽግና ፓርቲ ተወካዩ ዶ/ር ካሳም፤ በከተማይቱ ቻርተር መሰረት ተመሳሳይ መብት አላቸው። በህዝበ ተወካዮች ምክር ቤት ጠባቂነት የወጣው የከተማዋ ቻርተር፤ እንደ ህገ መንግስቱ ሁሉ ተመሳሳይ ድንጋጌን ይዟል።
እነዚህን የህገ መንግስቱን እና የከተማዋን ቻርተር ድንጋጌዎች የጠቀሱት ጠበቆች፤ የፌደራል ፖሊስ ግለሰቦቹ “ያለ መከሰስ መብት እንዳላቸው እያወቀ በሕገ ወጥ መንገድ አስሯቸዋል” ሲሉ አቤት ብለዋል።ጠበቆቹ አክለውም የደንበኞቻቸው “ያለመከሰስ መብታቸውን የተመረጡበት ምክር ቤት ተሰብስቦ ባለማንሳቱ”፤ የፌደራል ፖሊስ “ሰብዓዊ መብታቸውን በመጣስ ላይ ይገኛል” ሲሉ በአቤቱታቸው ጠቅሰዋል።
ደንበኞቻቸው “አላግባብ” በእስር ላይ እንደሚገኙ የጠቀሱት ሁለቱ ጠበቆች፤ ጉዳዩ የቀረበለት ችሎት “በእስር ላይ ያሉት አመልካቾች ያለምንም ቅደመ ሁኔታ ነጻነታቸው እንዲከበር እና ከእስር እንዲለቀቁ” ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል። አቤቱታውን የተመለከተው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት፤ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ በአቤቱታው ላይ ያለውን አስተያየት ለነገ ረቡዕ ከሰዓት በጽሁፍ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)