ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ እና ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት የሚያስፈልጓትን ነገሮች ለማግኘት “በድርድር፣ በምክክር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ” የምትመራ እንጂ፤ ያላትን ጉልበት በመጠቀም “አንበርክካ መንጠቅ የምትፈልግ ሀገር አይደለችም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኢትዮጵያ ለሁሉም ጎረቤቶቿ የሰላም ምንጭ እንጂ የጦርነት ምንጭ አትሆንም” ብለዋል።
አብይ ይህን ያሉት ቅዳሜ ነሐሴ 6፤ 2015 በብላቴ ኮማንዶ እና የአየር ወለድ ማሰልጠኛ ማዕከል በተካሄደው “የኤሊት ኃይል” የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ መልዕክታቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ያላት ቦታ ከፍ ያለ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። “ኢትዮጵያ ትልቅ ኢኮኖሚ እየገነባች ያለች ትልቅ ሀገር ናት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገሪቱ የአፍሪካ “powerhouse” መሆኗን “ጠላቶቻችን እየመረራቸው ሊውጡት የሚገባ ጉዳይ ነው” ሲሉ ጠንከር ባለ አነጋገር አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ “ስመ ገናና፣ ኃያል፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ናት” ሲሉ በንግግራቸው ያስገነዘቡት አብይ፤ “የዚህች ታላቅ ሀገር ሰራዊት ሆኖ ማገልገል፣ ቀይ መለዩ ለባሽ መሆን ታላቅ ክብር ነው” ሲሉ ለተመራቂ “ኮማንዶዎች” የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ እንደሆኑ የተነገረላቸው የዛሬዎቹ ተመራቂዎች፤ “ሙሉ የኮማንዶ እና የአየር ወለድ ስልጠና” የተከታተሉ መሆናቸው ተገልጿል።
“ይህንን ኃይል የሚያዩ የአፍሪካ ወንድሞቻችን በሙሉ በሚገጥማቸው ችግር ውስጥ ሁሉ፣ ድንበር ተሻግሮ ሰላም ለማስከበር የሚያስችል ብቃት [ያለው] እና ስልጠና የወሰደ አስተማማኝ አፍሪካዊ ‘ኤሊት ፎርስ’ እንደገነባን እንዲያስቡ… በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው መልዕክታቸው። ኢትዮጵያ በዚህ አመት በሀገር ውስጥ እና በተለያዩ ሀገራት “እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው” የ“ኤሊት ፎርስ” አባላት ማሰልጠኗን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ቢሆን የሀገሪቱ ቀዳሚ ፍላጎቷ “ሰላም መሆኑን” “ለወዳጅም፣ ለጠላትም” ማሳወቅ እንደሚፈልጉ በንግግራቸው አመልክተዋል።
“ኢትዮጵያ ለሁሉም ጎረቤቶቿ የሰላም ምንጭ እንጂ የጦርነት ምንጭ አትሆንም” የሚል ማረጋገጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ኢትዮጵያ በሚያስፈልጓት ነገር ሁሉ በድርድር፣ በምክክር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የምታምን እንጂ፤ ጎረቤቶቿን፣ አፍሪካ ወንድሞቿን ባላት ጉልበት አንበርክካ መንጠቅ የምትፈልግ የሰፈር ጎረምሳ ባህሪ ያላት ሀገር አይደለችም” ሲሉም ተደምጠዋል። አብይ በዛሬው ንግግራቸው ይህን ቢሉም፤ ከሰሞኑ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የወጡ ዘገባዎች ግን ኢትዮጵያ የራሷን ወደብ ለማግኘት “አስፈላጊ ከሆነ ኃይል ልትጠቀም ትችላለች” ሲሉ መናገራቸውን ዘግበው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)