የተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ

በሃሚድ አወል

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ ሳምንት በፊት የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ። አዋጁን 16 የፓርላማ አባላት ሲቃወሙት፤ 12 አባላት ደግሞ ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28፤ 2015 በሙሉ ድምጽ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት፤ በአማራ ክልል እና “እንዳስፈላጊነቱ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች” ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማጽደቅ በዛሬው ዕለት የተገኙት የፓርላማ አባላት ብዛት 360 ነበር። በዛሬው አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ አስራ ስድስት የፓርላማ አባላት መካከል፤ የአዋጁ መጽደቅ የሚቃወም ሀሳብ የሰነዘሩት አራቱ ብቻ ናቸው።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተቃወሙት ሁሉም የፓርላማ አባላት ከአማራ ክልል ተመርጠው የተወካዮች ምክር ቤትን የተቀላቀሉ ናቸው። የገዢው የብልጽግና ፓርቲ ተመራጮች ከሆኑ ሶስት የፓርላማ አባላት በተጨማሪ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዩ አቶ አበባው ደሳለው ተቃውሟቸውን በዛሬው ስብሰባ ላይ አሰምተዋል።

ፎቶ፦ ከ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ፋይል የተወሰደ

አቶ አበባው የተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከማጽደቁ በፊት፤ ከዚህ በፊት የጸደቁት አዋጆች “የህዝብን ችግር ፈትተዋል ወይ?” የሚለውን መመልከት እንዳለበት አሳስበዋል። “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጅምላ እስሮች ነበሩ። ዜጎች ረዥም ጊዜ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይታሰራሉ። አሁንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እናጽድቅ ካልን፤ እነዚህ ድርጊቶች ተባብሰው ይቀጥሉ እንደማለት ነው” ሲሉ የአብን ተወካዩ አዋጁ እንዳይጸድቅ ጠይቀዋል። 

“የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን ለመምታት ነው ጥረት እየተደረገ ያለው” ያሉት አቶ አበባው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲጸድቅ የሚፈለገው ይህንኑ “አጠናክሮ ለመቀጠል” በመፈለግ እንደሆነ አስረድተዋል። “ ‘አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አጽድቁልን። እኛን የሚቃወሙንን ተቃዋሚዎች በሙሉ እናጠፋለን’ አይነት ነገር ነው” ሲሉም የገዢውን ፓርቲ እና የመንግስትን አካሄድ ተችተዋል። 

ሌላኛው ከአማራ ክልል ተወክለው ፓርላማ የገቡት ዶ/ር ሞላ ፈለቀም በተመሳሳይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መጽደቅ ተቃውመው አስተያየት ሰጥተዋል። የብልጽግና ፓርቲ ተወካዩ ዶ/ር ሞላ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከተቃወሙባቸው ምክንያቶች አንዱ ከአዋጁ የተፈጻሚነት ወሰን ጋር የተያያዘ ነው። “በአንድ ክልል የአስተዳደር ወሰን ውስጥ ሰላም ለማስፈን የታሰበን አዋጅ የተፈጻሚነት ወሰን፤ ከዚያ የአስተዳደር ክልል ውጭ ማድረግ ለምን አስፈለገ?” ሲሉም ጠይቀዋል።

ፎቶ፦ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፋይል የተወሰደ

የምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫ ምርጫ ክልል ተወካዩ ዶ/ር ሞላ ጥያቄ ያነሱበት ሌላኛው ጉዳይ፤ ለአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የተሰጠውን ስልጣን ነው። ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ከተሰጡት ስልጣኖች መካከል “የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖችን እና መዋቅሮችን መልሶ የማቋቋም፣ የማደራጀት እና የአስተዳደርና የጸጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔዎችን የማስተላለፍ እና ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ ይችላል” የሚለው ይገኝበታል። 

ለጠቅላይ መምሪያ ዕዙ የተሰጠውን ይህን ስልጣን ዶ/ር ሞላ፤ “በእኔ መረዳት ሉዓላዊ ስልጣን ያለውን ሲቪል አስተዳደር በወታደራዊ አገዛዝ እንደመቀየር አድርጌ ወስጄዋለሁ” ሲሉ ተችተውታል። ዕዙ የሲቪል አስተዳደር መልሶ ማደራጀት እና ማቋቋም ከቻለ፤ በክልሉ አስተዳደር ውስጥ ሙሉ በሙሉ “የመወሰን ስልጣን አለው” እንደማለት መሆኑን የፓርላማ አባሉ አብራርተዋል።

የፓርላማ አባሉ ያነሷቸው ሁለት ጉዳዮች፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ “መሻሻል እና መሰረዝ አለባቸው” ያላቸውን ጉዳዮች በዘረዘረበት ሰነድ ላይም ተካትተዋል። ኢሰመኮ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባለፈው ቅዳሜ ባቀረበው የምክረ ሃሳብ ሰነድ ላይ፤ ለአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ የተሰጡት አንዳንድ ስልጣኖች እንዲሰረዙ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። 

ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ “የተለያዩ የአስተዳደር እርከኖችን እና መዋቅሮችን መልሶ የማቋቋም፣ የማደራጀት እና የአስተዳደርና የጸጥታ ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔዎችን የማስተላለፍ እና ሌሎች እርምጃዎችን ለመውሰድ” የተሰጠው ስልጣን፤ “ለተለጠጠ ትርጓሜ ወይም ተገቢ ላልሆነ አፈጻጸም ክፍት” እንደሆነ ኮሚሽኑ በምክረ ሃሳቡ ላይ አመልክቷል። ይህ ድንጋጌ “በክልሎች የዞን፣ የወረዳ እና ተያያዥ የአስተዳደር እርከኖች እና መዋቅር ላይ ከህገ መንግስታዊ ስርዓት ውጪ ለውጥ የማድረግና ውሳኔ የማሳለፍ እንድምታ የሚሰጥ” እንደሆነ አብራርቷል።

ይህ አይነቱ ድርጊት “የጥብቅ አስፈላጊነት፣ ተመጣጣኝነት እና ሕጋዊነት መርሆዎች ጋር ሊቃረን የሚችል” መሆኑን በምክረ ሃሳቡ ላይ ያነሳው ኢሰመኮ፤ ከዚህም ባሻገር ለሌላ “የፖለቲካ ውጥረት እና ለግጭት ተጨማሪ ስጋት” የመሆን እድል እንዳለውም አስገንዝቦ ነበር። ኮሚሽኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከአማራ ክልል በተጨማሪ “እንደ አስፈላጊነቱ በየትኛውም የሃገሪቱ አካባቢ ተፈጻሚነት” እንደሚኖረው መደንገጉንም መቃወሙ አይዘነጋም።  

“ከአንድ ክልል ብቻ በቀረበ የጸጥታና ደህንነት አደጋ ምክንያት ጠቅላላ ሀገሪቱን የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥ ማስገባት እና አጠቃላይ የሀገሪቱን የሕግ አስከባሪ አካሎች በአስቸኳይ ጊዜ መምሪያው ዕዝ ስር ማድረግ” በመደበኛው የፍትህ አስተዳደር ስራ ላይ “እጅግ አሉታዊ አንድምታ የሚፈጥር” እንደሆነም ኮሚሽኑ በምክረ ሃሳቡ አጽንኦት ሰጥቶ ነበር። የተወካዮች ምክር ቤት አዋጁን ለማጽደቅ በሚሰበሰብት ወቅት፤ የተፈጻሚነት ወሰኑን “ጥያቄው በቀረበበትና አደጋው ተከስቷል በተባለበት ክልል ብቻ የተገደበ እንዲሆን” እንዲያደርግ ኢሰመኮ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የኢሰመኮ ምክረ ሃሳብም ሆነ የአራቱ የፓርላማ አባላት የተቃውሞ አስተያየቶች፤ በአዋጁ ላይ ማሻሻያ ለማድረግ ምክንያት መሆን አልቻሉም። በአራት ክፍሎች ተዘጋጅቶ ለፓርላማው የቀረበው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ አስተያየታቸውን ባስደመጡት 12 የተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ሆነ በስተመጨረሻ በድጋፍ እጃቸውን ባወጡ አብዛኛው የፓርላማ አባላት ድጋፍ ተችሮታል። አብዛኛዎቹ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ደጋፊዎች፤ አዋጁ “ኢትዮጵያን ለማዳን፣ ሰላሟን ለማስጠበቅ የቀረበ” ሲሉ አሞካሽተውታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ  ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]