ከተበተኑ የአማራ ክልል የልዩ ኃይል አባላት መካከል፤ “አብዛኛዎቹ” ታጣቂ ቡድኖችን መቀላቀላቸውን የሰላም ሚኒስትሩ ገለጹ  

በአማኑኤል ይልቃል

በአማራ ክልል የልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የጸጥታ መዋቅሮች የማስገባት ስራ ከተጀመረ በኋላ 50 በመቶ የሚሆኑ የልዩ ኃይል አባላት “እንደተበተኑ” እና ከእነዚህ ውስጥ “አብዛኛዎቹ” ታጣቂ ቡድኖችን እንደተቀላቀሉ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዷለም ተናገሩ። በአማራ ክልል ከሰሞኑ የተቀሰቀሰው ግጭት የተጀመረው፤ ታጣቂዎች በመከላከያ ሰራዊት ካምፕ ላይ “ዘግናኝ የሚባል ጥቃት መክፈታቸውን” ተከትሎ እንደሆነም ገልጸዋል። 

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ ይህንን የተናገሩት፤ በአማራ ክልል ከሰሞኑ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር አስመልክቶ ትላንት ሰኞ ነሐሴ 8፤ 2015 ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በአዲስ አበባው ካፒታል ሆቴል በተደረገ ውይይት ላይ ነው። አቶ ብናልፍ እና የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በመሩት በዚህ ስብሰባ 16 የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ተሳትፈውበታል። 

በውይይቱ መጀመሪያ ላይ 30 ደቂቃ ገደማ ለሚጠጋ ጊዜ ማብራሪያ የሰጡት የሰላም ሚኒስትሩ፤ ከፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮቹ ጋር ውይይት ለማድረግ የታሰበው “ከመንግስት በተነሳ ሀሳብ” መሆኑን ለተወካዮቹ ተናግረዋል። አቶ ብናልፍ በዚሁ ማብራሪያቸው፤ መንግስት በአማራ ክልል ያጋጠመው ግጭት “ዝም ብሎ በድንገት የተፈጠረ” ነው የሚል እምነት እንደሌለው እና “በተለያዩ ጊዜ የሚነሱ እና እየተደመሩ የመጡ ችግሮች የፈጠሩት” እንደሆነ አስረድተዋል። 

የሰላም ሚኒስትሩ በዚሁ ማብራሪያቸው ላይ በአማራ ክልል ለተፈጠረው ችግር ምክንያት የሆኑ “የህዝብ ጥያቄዎች” እና “አባባሽ” ያሏቸውን ጉዳዮች ዘርዝረዋል። በክልሉ የሚነሱ ጥያቄዎች ተብለው በአቶ ብናልፍ ከተጠቀሱት ውስጥ፤ የወሰን እና ማንነት ጉዳይ፣ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና የእኩልነት ጥያቄ እንዲሁም “የፈለጉትን የፖለቲካ ሀሳብ ለማራመድ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖር” የሚሉት ይገኙበታል። 

በተለይም ከወሰን እና ማንነት ጋር የተያያዘው ጥያቄ “በተፈለገው ፍጥነት ምላሽ እያገኘ አይደለም” የሚል ቅሬታ እንደተነሳበት የገለጹት የሰላም ሚኒስትሩ፤ የዚህም ምክንያቱ ጥያቄውን ለመመለስ የሚያስችል ሁኔታ በክልሉ ውስጥ “አለመፈጠሩ” እና “በክልሉ አመራር ላይ ክፍተት መኖሩ” እንደሆነ አንስተዋል። በአማራ ክልል ከሚነሱት ጥያቄዎች በተጨማሪ ጉዳዩን “የሚያባብሱ ሁኔታዎች በተከታታይ” መፈጠራቸውን አቶ ብናልፍ በማብራሪያቸው ላይ አስረድተዋል።      

የሰላም ሚኒስትሩ ላለፉት ሶስት ዓመታት የአማራ ክልልን “በቀጣይነት፣ ያለ እረፍት ችግር ውስጥ እንዲወድቅ አድርጓል” ያሉት የሰሜኑን ጦርነት፤ “አባባሽ ጉዳዮች” በሚል ከዘረዘሯቸው ክስተቶች ውስጥ በቀዳሚነት አስቀምጠውታል። በዚህ ጦርነት የአማራ ክልል ህዝብ “በከፍተኛ ቁጥር mobilized መሆኑን” የገለጹት አቶ ብናልፍ፤ ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ የታጠቁ ሰዎችን ወደ መደበኛ ህይወታቸው መመለስ ላይ “ውጤት ያለው ስራ ተሰርቷል” ማለት “እንደማይቻል” ተናግረዋል። 

የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላትን ወደ ሌሎች የመንግስት የጸጥታ መዋቅሮች ለመቀላቀል የተጀመረው ስራም ሌላ ችግር መፍጠሩን አስረድተዋል። የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ኃይሎች አባላት “ወደ ተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች እንዲገቡ” የሚያደርግ “ተግባራዊ እንቅስቃሴ” መጀመሩን ያስታወቀው ባለፈው መጋቢት ወር መጨረሻ ነበር። በዚህ የመንግስት ውሳኔ መሰረት በየክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አባላት፤ እንደ ፍላጎታቸው ወደ መከላከያ ሰራዊት፣ ፌደራል ፖሊስ ወይም የክልል ፖሊስ አባልነት መቀላቀል እንደሚችሉ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

በዚህ እቅድ አፈጻጸም ላይ በአማራ ክልል “ከፍተቶች” እንደነበሩ አቶ ብናልፍ በትላንት ማብራሪያቸው ላይ አምነዋል። የክልል ልዩ ኃይል አባላትን የተመለከተውን ዕቅድ ወደ ተግባር ለመለወጥ እንቅስቃሴ በተጀመረበት ወቅት፤ ከአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ውስጥ ግማሽ ያህሉ የሚሆኑት መበተናቸውንም አክለዋል። “Almost 50 ፐርሰንት የልዩ ኃይል ተበትኖ ነበር። ያ የተበተነው ልዩ ኃይል ደግሞ ወደ የቤተሰቦቹ ከሄደ በኋላ አብዛኛው በሚባል ደረጃ፤ ታጥቀው ‘የምንፈልገውን ነገር በኃይል እናደርጋለን’ ከሚሉ ሰዎች ጋር የተቀላቀለበት ሁኔታ በመፈጠሩ፤ ይሄም ሌላ አባባሽ ምክንያት ሆኗል” ብለዋል። 

አቶ ብናልፍ ይህንን ቢሉም በታጣቂዎች የተገደሉት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ በሚያዝያ ወር ለመጀመሪያ ለክልሉ የቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፤ ከክልሉ ልዩ ኃይል አባላት መካከል “ተደናግጠው የተበተኑት” “ጥቂት” መሆናቸውን ገልጸው ነበር። አቶ ግርማ በዚሁ ቃለ መጠይቃቸው ላይ “ከሰባ በመቶ በላይ” የሚሆነው የክልሉ ልዩ ኃይል “በሙሉ አደረጃጀቱ” እና “ ከእነ ሙሉ አመራሩ” “በካምፕ እና በምሽግ” ውስጥ ሆኖ “ተጨማሪ ትዕዛዝ እየተጠባበቀ” እንደሚገኝ መግለጻቸው አይዘነጋም። 

የሰላም ሚኒስትሩ በትላንቱ ማብራሪያቸው፤ የአማራ ክልልን የጸጥታ ችግር “በጣም ከባባሱት” ጉዳዮች አንዱ በሌሎች ክልሎች ውስጥ በሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች እንደሆኑ አስረድተዋል። “ማንነትን መሰረት ያደረጉ” ናቸው በተባሉ በእነዚህ ጥቃቶች የአማራ ተወላጆች “መገደላቸው እና መፈናቀላቸው”፤ “ተገፍተናል፣ ጥቃት ደርሶብናል፤ በሀገራችን በነጻነት መኖር አልቻልንም” የሚል ቅሬታ እንዲስፋፋ ማድረጉን አቶ ብናልፍ ተናግረዋል። 

የአማራ ክልል ነዋሪዎች “ወደ አዲስ አበባ እንዳንገባ ተደርገናል” በማለት የሚያነሱት ቅሬታ እና በተጓዦች ላይ የሚፈጸሙ እገታዎችም “በማንነታችን ጥቃት ደርሶብናል” የሚል ብሶት መፍጠሩንም አስረድተዋል። እነዚህ ቅሬታዎች “ቀላል የማይባል ቁጥር” ያላቸው ግለሰቦች “በቀላሉ አመጽ ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ሰዎችን እንዲደግፉ እና እንዲተባበሩ” እንዳደረጉም አክለዋል። 

“አባባሽ” በሚል ከተዘረዘሩ ምክንያቶች ባሻገር፤ በህዝቡ ዘንድ ያለውን ቅሬታ የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈጸም የሚፈልጉ የፖለቲካ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳደረጉት የሰላም ሚኒስትሩ አመልክተዋል። “ ‘በኃይል ስርዓት እንቀይራለን፣ መንግስት እንገለብጣለን ወይም ደግሞ የመንግስት ለውጥ እናደርጋለን’ ብለው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች አሉ። እነዚህ ኃይሎች አሁን የተፈጠረውን ነገር እንደ ምቹ ሁኔታ ወስደው ተጠቅመውበታል” ሲሉ አቶ ብናልፍ ወንጅለዋል። 

እነዚህ ኃይሎች በተለይም በመከላከያ ሰራዊት ላይ “ክፍተኛ የሆነ የሚዲያ ዘመቻ” በማካሄድ “ህዝቡ ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዲያድርበት” ማድረጋቸውን የሰላም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።  “በዚህ ምክንያት ግጭቱ ሲጀመር፣ አሁን ክልሉ ላይ የተፈጠረው ችግር ሲጀምር፤ መከላከያን በማጥቃት ነው የተጀመረው። እንደምታውቁት ጥላቻ ከአስተሳሰብ ነው የሚጀምረው። ከዚያ በኋላ ነው ወደ ድርጊት የሚሄደው” ሲሉም የጉዳዩን ቅደም ተከተል አስረድተዋል።  

“ሚዲያው bombard የሚያደርገው ዘመቻ ሰውን ሲሞላው፣ እየዋለ እያደረ ሲሄድ እዛው መከላከያ የተሰማራባቸው አካባቢዎች ላይ በካምፓቸው ላይ ጭምር እየሄዱ በጣም ዘግናኝ በሆነ በሚባል ደረጃ መከላከያው ላይ ጥቃት እንዲፈጸምበት ተደርጓል” በማለትም በአማራ ክልል ከሰሞኑ ለተከሰተው የጸጥታ ችግር መንስኤ ነው ያሉትን አቶ ብናልፍ ለፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮቹ አስረድተዋል። 

በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት “የታጠቁት ኃይሎች በግንባር ቀደምነት” እንደመሩት የጠቀሱት የሰላም ሚኒስትሩ፤ በአንዳንድ አካቢዎች ላይ “በተወሰነ ደረጃ ከህብረተሰቡ ክፍልም  ተባባሪ” የሆኑ እንደነበሩ “በግልጽ መታየቱን” ተናግረዋል። በአማራ ክልል ውስጥ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ “የመንግስት መዋቅሮችን ለማፍረስ የተሰራ” መሆኑን ያነሱት አቶ ብናልፍ፤ “ማረሚያ ቤቶች እየተሰበሩ ታራሚዎች እንዲለቀቁ” መደረጉን በምሳሌነት አንስተዋል።

በአማራ ክልል በዋነኛነት ተፈጻሚ እንዲሆን የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ እንዲያስፈጽም የተቋቋመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ከሳምንት በፊት በሰጠው መግለጫ፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ “ዘራፊ ኃይሎች” “አንዳንድ የዞን እና የወረዳ ከተሞችን መቆጣጠራቸውን” እንዲሁም በተወሰኑ ቦታዎች “ወንጀለኞችን ከማረሚያ ቤት ማስለቀቃቸውን” በተመሳሳይ አስታውቆ ነበር። እነዚሁ ኃይሎች “የክልሉን መንግስት በማፍረስ ወደ ፌደራል ስርዓት የመሄድ” ፍላጎት እና ግብ ያላቸው መሆናቸውም ዕዙ በወቅቱ መግለጹ ይታወሳል።  

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ የተደረገው፤ የአማራ ክልል መንግስት የጸጥታ ችግሩ ከአቅሙ በላይ መሆኑን ለፌደራል መንግስት በማስታወቁ ምክንያት መሆኑን የሰላም ሚኒስትሩ ለፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች አስገንዝበዋል። እርሳቸው አባል የሆኑበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28፤ 2015 ባደረገው ስብሰባ፤ ችግሩን “በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቀልበስ” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉንም ጠቅሰዋል።   

በአማራ ክልል እና እንዳስፈላጊነቱ በሌሎችም የኢትዮጵያ ክልሎች ተፈጻሚ እንደሚሆን የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ በትላንትናው ዕለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቁ አይነዘጋም። የስድስት ወራት የቆይታ ጊዜ ያለው ይህ አዋጅ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ በኋላ በተወሰዱ እርምጃዎች፤ “በአብዛኛው አካባቢ ግጭት እንዲቆም” እና “ከተሞች እንዲረጋጉ” ማድረግ መቻሉን የሰላም ሚኒስትሩ በትላንቱ ማብራሪያቸው ገልጸዋል።   

“አሁን አብዛኛው አካባቢ ግጭቱ እንዲቆም የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ብዙ ከተሞች ወደተረጋጋ ነገር መጥተዋል፡፡ የተወሰኑ ጥቂት አካባቢዎች ናቸው የሚቀሩት፤ ኪስ ወረዳዎች አካባቢ፡፡ እነሱም በሚቀጥሉት ቀናት፤ ምናልባት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ድረስ የተረጋጋ ነገር ውስጥ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡” 

– አቶ ብናልፍ አንዷለም፤ የሰላም ሚኒስትር

አሁንም በግጭት ውስጥ ያሉት “የተወሰኑ ኪስ ወረዳዎች” መሆናቸውን ያነሱት አቶ ብናልፍ፤ “በሚቀጥሉት ቀናት፣ ምናልባትም እስከዚህ ሳምንት መጨረሻ ድረስ፤ የተረጋጋ ነገር ውስጥ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል” ሲሉ የአማራ ክልል ወደ ቀደመ ሰላሙ ለመመለስ በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት መረጋጋት ውስጥ ገብተዋል በተባሉት ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን እና ላሊበላ ላይ ከአካባቢው ህዝብ ጋር ውይይት መደረግ እንደጀመረ የገለጹት አቶ ብናልፍ፤ መንግስት የክልሉን ሁኔታ የተመለከተውን ይህ አይነት ውይይት ከአማራ ክልል ውጪም ከምሁራን፣ ከባለሀብቶች፣ ከፖለቲከኞች እና የኪነ ጥበብ ሰዎች ጋር እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)