የአዲሱ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የምስረታ በዓል በመጪው ቅዳሜ በአርባ ምንጭ ከተማ ሊካሄድ ነው

⚫ የነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤትም ለሳምንቱ መጨረሻ አስቸኳይ ጉባኤ ጠርቷል  

በሃሚድ አወል

በህዝበ ውሳኔ የተመሰረተው 12ኛው የ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ይፋዊ የምስረታ በዓሉን በሳምንቱ መጨረሻ በአርባ ምንጭ ከተማ ሊያደርግ ነው። የነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤትም በተመሳሳይ ቀናት አስቸኳይ ጉባኤ መጥራቱን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

በአርባ ምንጭ ከተማ የሚካሄደው የ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ምስረታ ለሁለት ቀናት የሚቆይ መሆኑን የጋሞ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ ኤደን ንጉሴ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ከነገ በስቲያ አርብ ነሐሴ 12፤ 2015 በሚኖረው መርሃ ግብር፤ የአዲሱ ክልል ምክር ቤት መስራች ጉባኤውን እንደሚያደርግ ኃላፊዋ አስረድተዋል። 

በዚሁ ጉባኤ ላይ የምክር ቤቱ አባላት የአዲሱን ክልል ህገ መንግስቱን ተወያይተው ያጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል። በማግስቱ ቅዳሜ ደግሞ 12ኛው የፌደሬሽኑ ክልል በይፋ የምስረታ ፕሮግራሙን እንደሚያካሄድ ኤደን ጠቁመዋል። የአዲሱ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የካቤኔ አባላትም በዚሁ ቀን ይሾማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ገልጸዋል። 

በ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የምስረታ በዓል ላይ “ተጋባዥ” እንግዶች እና የፌደራል መንግስት የስራ ኃላፊዎች ይገኛሉ ተብሏል። ለዚሁ ስነ ስርዓት ከዛሬ ረፋድ ጀምሮ የአርባ ምንጭ ከተማን የማጽዳት ክንውኖች ሲካሄዱ መዋላቸውን እና የ“እንኳን ደህና መጣችሁ” መልዕክት የያዙ ባነሮች ሲሰቀሉ መመልከታቸውን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

አዲሱን ክልል የመሰረቱት የወላይታ፣ የጋሞ፣ የጎፋ፣ የደቡብ ኦሞ፣ የጌዴኦ፣ የኮንሶ ዞኖች እንዲሁም የደራሼ፣ የአማሮ፣ የቡርጂ፣ የአሌ እና የባስኬቶ ልዩ ወረዳዎች ናቸው። በአስራ አንዱ መዋቅሮች የተመሰረተው 12ኛው ክልል፤ ከነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ስልጣን በይፋ የተረከበው ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ነው። 

የ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” በህዝበ ውሳኔ ፌደሬሽኑን በመቀላቀል ሶስተኛው ነው። ከዚህ በፊት የሲዳማ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በህዝበ ውሳኔ ክልል ሆነው መመስረታቸው ይታወሳል። ባለፉት ሶስት ዓመታት እነዚህን ሶስት ክልሎች የሸኘው ነባሩ የደቡብ ክልል፤ የስያሜ፣ የህገ መንግስት እና የመዋቅር ለውጥ ያደርጋል። “የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል” የሚለውን ስያሜውን እና አደረጃጀቱን ለመቀየር በዝግጅት ላይ በሚገኘው በዚህ ክልል የሚቀጥሉት መዋቅሮች፤ የሀድያ፣ ሀላባ፣ ከምባታና ጠምባሮ፣ ስልጤ፣ ጉራጌ ዞኖች እና የም ልዩ ወረዳ ናቸው። 

የነባሩ የደቡብ ክልል ምክር ቤት የእነዚህ ዝግጅቶች አንዱ አካል የሆነውን አስቸኳይ ጉባኤውን፤ በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ  በሳምንቱ መጨረሻ እንደሚያካሄድ ሁለት የምክር ቤቱ አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የደቡብ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ መጥራቱን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ሆኖም የጉባኤውን አጀንዳ በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ አፈ ጉባኤዋ “ገና አልለየንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

እርሳቸው ይህን ቢሉም ሁለቱ የደቡብ የምክር ቤት አባላት ግን፤ ከነገ በስቲያ አርብ ነሐሴ 12፤ 2012 በሚካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ በሚሻሻለው የክልሉ ህገ መንግስት ላይ ውይይት እንደሚደረግ አስታውቀዋል። ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል “[ነሐሴ] 12 በህገ መንግስቱ ላይ ውይይት ይደረግ እና በ13 ለሚኖረው ጉባኤ የውይይቱ ውጤት ይቀርባል” ሲሉ የሁለቱን ቀን ስብሰባ ሂደት አስረድተዋል።

እኚሁ የክልሉ የምክር ቤት አባል፤ ህገ መንግስቱ ቅዳሜ ነሐሴ 13፤ 2015 በሚኖረው የአስቸኳይ ጉባኤው ውሎ ላይ “ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ” አስረድተዋል። ሌላ የደቡብ ክልል ምክር ቤት አባል በበኩላቸው “ወደ አዲሱ ክልል በሚሄዱ አመራሮች ምትክ ሹመት ሊሰጥ ይችላል” የሚል ግምታቸውን አስቀምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)