በሃሚድ አወል
ላለፉት ሶስት ዓመታት ገደማ የሀዋሳ ከተማን በከንቲባነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ጸጋዬ ቱኬ፤ በ“ብልሹ አሰራር” እና “አፈጻጸም ድክመት” ተገምግመው ከስልጣናቸው መነሳታቸውን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የሲዳማ ክልል ምንጮች ገለጹ። አቶ ጸጋዬ ከኃላፊነት እንዲነሱ ውሳኔ የተላለፈው ትላንት ረቡዕ ነሐሴ 10፤ 2015 ከተደረገ ግምገማ በኋላ መሆኑን ምንጮቹ አስታውቀዋል።
በሲዳማ ክልል ደረጃ ያሉ የፓርቲ እና የመንግስት ስራዎች አፈጻጸም እየተገመገሙበት ያለው መድረክ መካሄድ የጀመረው ካለፈው ሳምንት መጨረሻ እሁድ ነሐሴ 7፤ 2015 ጀምሮ ነው። በዚህ መድረክ ላይ የተሳተፉ አንድ ምንጭ፤ ከሀዋሳው ከንቲባ በተጨማሪ ሌሎች የክልሉ አመራሮች ላይ ግምገማ መደረጉን አመልክተዋል። ከእሁድ ጀምሮ የነበሩትን ግምገማዎች በአካል ተገኝተው የተሳተፉት አቶ ጸጋዬ፤ እርሳቸውን በሚመለከተው የትላንት ከሰዓቱ ግምገማ ግን አለመገኘታቸውን እኚሁ ምንጭ አክለዋል።
በትላንቱ ግምገማ ላይ አቶ ጸጋዬ “ከፍተኛ ሙስና ውስጥ መግባታቸውን” የሚያመለክቱ፣ “በሰነዶች የተረጋገጡ” መረጃዎችን መቅረባቸውን በመድረኩ የተሳተፉ ሁለት የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ተናግረዋል። በዚሁ ግምገማ “ከፍተኛ ተመራጭ የነበረችው የሀዋሳ ከተማ ወደ ኋላ መሄዷ” መነሳቱን የጠቆሙት ምንጮች፤ የከተማዋ ከንቲባ “የአቅም ውስንነት ጭምር አለባቸው” መባሉን ጠቅሰዋል።
ከንቲባው ከተገመገሙባቸው ጉዳዮች መካከል፤ ባለፈው ሰኔ ወር መጨረሻ ተመርቆ ወደ ስራ የገባው የሀዋሳ ከተማ መግቢያ ግንባታ አንዱ ነው። “የሀዋሳ ከተማ መግቢያ ሚሊኒየም ፓርክ” የተሰኘው ፕሮጀክት በተመረቀበት ወቅት፤ 90 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት መገለጹ በወቅቱ በማህበራዊ ድረ ገጾች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በትላንቱ ግምገማ ላይ የፕሮጀከቱ ወጪ “በመሃንዲስ ተጠንቶ ዋጋው ከ30 ሚሊዮን ብር የማያልፍ ነው” መባሉን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች አስታውቀዋል።
አቶ ጸጋዬ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ከአዲስ ዋልታ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የፕሮጀክቱ ወጪ 90 ሚሊዮን ብር የተገመተው “ብዙ ነገሮችን ጨምሮ” እንደሆነ ገልጸው ነበር። የፕሮጀክቱ ወጪ “እስከ 90 ሚሊዮን ብር ሊደርስ ይችላል ብንልም እስካሁን [ያን ያህል] አልደረሰም” ሲሉ በቃለ ምልልሱ የገለጹት አቶ ጸጋዬ፤ የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን በፕሮጀክቱ ሁለተኛ ምዕራፍ የሚሰሩትን የፓርኩን አጥር፣ የደህንነት ካሜራዎች ተከላ እና “ሌሎች” ስራዎችን የሚያካትት መሆኑን አብራርተዋል።
የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በዚህ ቃለ ምልልሳቸው ያነሱት ሌላኛው ጉዳይ፤ ባለፉት ጥቂት ወራት በከተማይቱ ከተፈጸሙ የሴቶች ጠለፋዎች ጋር በተያያዘ ጥያቄ ሲነሳበት የቆየው የከተማዋ የጸጥታ ሁኔታ ነው። ከእነዚህ ጠለፋዎች መካከል ይበልጡኑ ትኩረት ስቦ የነበረው፤ የአቶ ጸጋዬ ጥበቃ በሆነ ግለሰብ አማካኝነት የተፈጸመው ነው። ድርጊቱን ፈጽሟል የተባለው የከንቲባው ጠባቂ በሲዳማ ክልል የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ውሎ የፍርድ ሂደቱን በመከታተል ይገኛል።
ይህንን የአንድ ሰሞን አነጋጋሪ ድርጊት በተመለከተ አዲስ ዋልታ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ጸጋዬ በሰጡት መልስ፤ “ድርጊቱ ከተከሰተ በኋላ ትልቅ እርምጃ ወስደናል” ብለዋል። የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የፖሊስ ኃይል መድቦ “ለአንድ ሳምንት ሙሉ ገጠር ሰውዬውን እየፈለገ” መቆየቱን ገልጸዋል። ድርጊቱን “አሳፋሪ” ሲሉ የጠሩት ከንቲባው፤ በከተማዋ አመራሮች ትኩረት አልተሰጠውም የሚለውን ክስም “ውሸት” ሲሉ አስተባብለዋል።
የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው፤ የከተማይቱ የጸጥታ ሁኔታን በተመለከተ “ችግሮች” መኖራቸውን ቢያምኑም፤ ሆኖም “እንደሚባለው” ሳይሆን ችግሮቹ “ትንንሽ ናቸው” ባይ ናቸው። በትላንቱ ግምገማ ላይ የጠለፋው ድርጊትም ሆነ የከተማይቱ የጸጥታ ሁኔታ አለመነሳቱን የመድረኩ ተሳታፊዎች ጠቁመዋል። ሆኖም በከንቲባው ላይ በተደረገው ግምገማ ማጠቃለያ ላይ “ ‘የአቅም ውስንነት አለበት። ከስልጣኑ ተነስቶ በህግ ይጠየቅ’ የሚለው ውሳኔ ተላልፏል” ሲሉ በስፍራው የነበሩ አንድ ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።
በሲዳማ ክልል የግምገማ ውሳኔ መሰረት አቶ ጸጋዬ በህግ የሚጠየቁ ከሆነ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት መሰል እርምጃ የተወሰደባችው ሁለተኛው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ይሆናሉ። የሀዋሳ ከተማን ከዚህ ቀደም ለሁለት ዓመት ከስምንት ወር የመሩት አቶ ቴዎድሮስ ገቢባ፤ አንድን ብሔር በሌላኛው ላይ “በማነሳሳት ድርጊት” በነሐሴ 2010 ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር ይታወሳል።
አቶ ቴዎድሮስ ከሌሎች 33 ሰዎች ክስ የተመሰረተባቸው፤ “በሀዋሳ ከተማና አካባቢዋ፣ በሲዳማ እና የወላይታ ብሄረሰብ አባላት መካከል ግጭት እንዲፈጠር አድርገዋል” በሚል ነበር። ተከሳሾቹ በዚህ ግጭት “የበርካታ ሰዎች ህይወት እንዲጠፋና ዜጎች እንዲፈናቀሉ በማድረግ እጃቸው አለበት” የሚል ክስም እንደቀረበባቸው አይዘነጋም። አቶ ቴዎድሮስ ለአንድ ዓመት ያህል ከታሰሩ በኋላ፤ በተጠረጠሩበት ወንጀል በፍርድ ቤት “ነጻ” በመባላቸው ተለቅቀዋል። በስተኋላ ላይም የሲዳማ ክልል የስራ ክህሎትና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል፡፡
የቀድሞው የሀዋሳ ከንቲንባ በወንጀል ተጠርጥረው ከመታሰራቸው ሁለት ወራት በፊት፤ “በገዛ ፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው እንደለቀቁ” የደቡብ ክልል በወቅቱ አስታውቆ ነበር። ከዚህ ክስተት በኋላ የሀዋሳ ከተማን የማስተዳደር ኃላፊነት የተረከቡት አቶ ሱኳሬ ሹዳ ናቸው። አቶ ሱካሬ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ ከተማይቱን ለአንድ ዓመት ገደማ ከመሩ በኋላ ኃላፊነታቸውን ለአሁኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ አስረክበዋል። አቶ ጥራቱ ከተማይቱን በመሩበት አንድ ዓመት ገደማ፤ ሀዋሳ ከተማ የሚገኝበት እና በደቡብ ክልል ስር የነበረው የቀድሞው የሲዳማ ዞን በህዝበ ውሳኔ ራሱን የቻለ ክልል ሆኗል።
አቶ ጥራቱ የኃላፊነት ቦታ ተሰጥቷቸው ወደ አዲስ አበባ ከተዘዋወሩ በኋላ፤ አቶ ጸጋዬ ቱኬ ሀዋሳ ከተማን በከንቲባነት እንዲያስተዳድሩ በጥቅምት 2013 ዓ.ም. ተሹመዋል። አቶ ጸጋዬ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ሆነው ከመሾማቸው በፊት የሲዳማ ክልል ከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በስነ መንግስት እና ልማት የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ “regional & local development studies” የማስተርስ ዲግሪ ያላቸው አቶ ጸጋዬ፤ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህግ እና ስነ መንግስት ኮሌጅ ዲን እንዲሁም የልማት ጥናት መምህርም ነበሩ።
አቶ ጸጋዬ ለመጨረሻ ጊዜ ቢሮ የገቡት ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ነሐሴ 6፤ 2015 መሆኑን ሁለት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሰራተኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ ጸጋዬ ቅዳሜ ረፋድ ላይ ቢሮ ሲገቡ እንደተመለከቷቸው የገለጹት አንድ የጽህፈት ቤቱ ሰራተኛ፤ “ሐሙስ ዕለት ባለጉዳዮችን ሲያስተናግዱ ነበር” ብለዋል። የሲዳማ ክልል በሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ላይ ያስተላለፈውን ውሳኔ በተመለከተ አቶ ጸጋዬን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)