አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አቶ ጥላሁን ከበደን ርዕሰ መስተዳደር አድርጎ ሾመ

በአማኑኤል ይልቃል

በህዝበ ውሳኔ የተመሰረተው አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት፤ አቶ ጥላሁን ከበደን የክልሉ የመጀመሪያ ርዕሰ መስተዳደር አድርጎ ሾመ። የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ የቆዩት አቶ ጥላሁን ይህንን ሹመት ያገኙት፤ ዛሬ ቅዳሜ ነሐሴ 13፤ 2015 በአርባ ምንጭ ከተማ እየተደረገ ባለው የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ነው። 

መስራች ጉባኤውን በመካሄድ ላይ የሚገኘው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት በትላትናው ውሎው፤ ፌዴሬሽኑን በመቀላቀል 12ኛ የሆነውን ክልል ህገ መንግስት አጽድቋል። ምክር ቤቱ በዛሬው የጉባኤው መርሃ ግብር ለተለያዩ የክልሉ መንግስት አመራሮች ሹመት የመስጠት አጀንዳ ይዞ ነበር። በዚህም መሰረት በቅድሚያ ሹመት የተሰጠው ለምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና ምክትል አፈ ጉባኤ ኃላፊነቶች ነው። 

ፎቶ፦ የጋሞ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አድርጎ የሾመው ወ/ሮ ጸሀይን ወራሳን ሲሆን፤ ወ/ሮ ወላይቴ ቢቶ ደግሞ በምክትል አፈ ጉባኤነት ተመርጠዋል። በዛሬው ጉባኤ ላይ ቀጣይ አጀንዳ ሆኖ የቀረበው የአዲሱን ክልል ርዕሰ መስተዳደር መሰየም ነበር። በቀድሞው የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተስፋዬ ይገዙ አማካኝነት ለኃላፊነት ቦታው የቀረቡት ብቸኛ ዕጩ አቶ ጥላሁን ከበደ ናቸው።

በመንግስት መዋቅር ውስጥ ለ23 ዓመታት የቆዩት አቶ ጥላሁን፤ አብዛኛውን የስራ ኃላፊነት ያሳለፉት በትውልድ ቦታቸው በጋሞ ዞን ውስጥ ነው። በቀድሞው ጋሞ ጎፋ ዞን ውስጥ  የኡባ ደብረ ጸሀይ ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ጥላሁን፤ በዞኑ መምሪያ ጽህፈት ቤት በባለሙያነት እና በኃላፊነት ሰርተዋል። 

በጋሞ ጎፋ ዞን የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ በቆዩበት ጊዜ የንግድ እና ኢንዱስትሪ መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም በፓርቲ ውስጥ የዞኑ አደረጃጃት ዘርፍ ኃላፊም ነበሩ። አቶ ጥላሁን ወደ ደቡብ ክልል አመራርነት ከመዘዋወራቸው በፊት፤ የጋሞ ጎፋ ዞንን በዋና አስተዳዳሪነት መርተዋል። 

ፎቶ፦ የጋሞ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ

አዲሱ ተሿሚ በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የግብርና እና የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ የኃላፊነት ቦታ የተሰጣቸው 2008 ዓ.ም ነበር። በዚህ ወቅት የክልሉን የእርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊነት ደርበው ይሰሩ ነበር። አቶ ጥላሁን በእነዚህ ኃላፊነቶች ላይ ለአራት ዓመት ገደማ ከቆዩ በኋላ፤ የክልሉ ገዢ ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊነት ቦታን አግኝተዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጥላሁን፤ የፓርቲውን የደቡብ ክልል ጽህፈት ቤት ከመጋቢት 2012 ጀምሮ በኃላፊነት መርተዋል። የክልሉ የመንግስት ተጠሪ ሆነውም እስከዛሬው ሹመታቸው ድረስ ቆይተዋል። በዛሬው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ጉባኤ፤ አቶ ጥላሁን በርዕሰ መስተዳድርነት እንዲሾሙ ስማቸው በዕጩነት ሲቀርብ የምክር ቤቱ አባላት ድጋፋቸውን በጋለ ጭብጨባ ገልጸዋል። የአዲሱ ክልል ምክር ቤት አባላት የአቶ ጥላሁንን ሹመት ያጸደቁትም በሙሉ ድምጽ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)