አቶ አንተነህ ፈቃዱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ

በሃሚድ አወል

የቀድሞው የደቡብ ክልል የደን እና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ፤ በአዲስ መልክ የተደራጀው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ተሾሙ። በደቡብ ክልል የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ ቆዩት ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ዋና ተጠሪ ሆነዋል። 

ሁለቱን ሹመቶች የሰጡት፤ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝዳንት ሆነው ዛሬ ረፋድ ላይ ቃለ መሃላ የፈጸሙት አቶ እንደሻው ጣሰው ናቸው። አቶ እንደሻው በወልቂጤ ከተማ አስቸኳይ ጉባኤውን ያካሄዱት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባላት፤ ሰባት የካቢኔ አባላት ሹመትን እንዲያጸድቁላቸው አቅርበዋል። 

አዲሱ የክልሉ ፕሬዝዳነት የእርሳቸው ምክትል እንዲሆኑ የመረጧቸው፤ ወደ ደቡብ ክልል በቢሮ ኃላፊነት ከመዘዋወራቸው በፊት የከንባታ ጠንባሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የነበሩትን አቶ አንተነህ ፈቃዱን ነው። አዲሱ ተሿሚ በደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩ ናቸው። 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል እርሻ እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ በኃላፊነት የሰሩት አቶ አንተነህ፤ ካለፈው ዓመት መስከረም ጀምሮ የክልሉ የደንና አካባቢ ጥበቃ ቢሮን እንዲመሩ ተሹመው ነበር። እንደ እርሳቸው ሁሉ በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የቢሮ ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ፤ በአዲሱ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ተጠሪ ሆነው ተሹመዋል። 

ዶ/ር ዲላሞ በስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ለተወካዮች ምክር ቤት በተወዳደሩበት የአዲስ አበባ ምርጫ ክልል፤ የኢዜማውን መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን አሸንፈው ፓርላማ መግባታቸው ይታወሳል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርት እና የንግድ ቢሮዎችን በኃላፊነት የመሩት ዶ/ር ዲላሞ፤ በፌደራል ደረጃ ደግሞ የቀድሞው የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል። 

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ እንደሻው፤ ከምክትል ርዕሰ መስተዳደር እና የመንግስት ተጠሪ በተጨማሪ ለሌሎች ሶስት የስራ ኃላፊዎች የሰጡት ሹመት በዛሬው የክልሉ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ጸድቋል። በዚህም መሰረት አቶ ኡስማን ሱሩር የግብርና ቢሮን፣ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮን፣ ዶ/ር መሀመድ ኑርዬ ደግሞ የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮን እንዲመሩ ተሹመዋል። ሶስቱም ተሿሚዎች ኃላፊነቱ የተሰጣቸው በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)