በአማራ ክልል በአስር ዞኖች የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ታገደ

በአማኑኤል ይልቃል

የአማራ ክልል መንግስት በአስር ዞኖች እና አንድ የከተማ አስተዳደር ስር ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ አገደ። የክልሉ መንግስት ይህን ትዕዛዝ ያስተላለፈው፤ በአስሩ ዞኖች እና በደብረ ታቦር ከተማ የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚጠቀሙባቸው “ደረሰኞች እና ቼኮች በመዘረፋቸው” መሆኑን ገልጿል።

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ እገዳው ተግባራዊ እንዲደረግ፤ የክልሉ “የመንግስት ሀብት ለሚንቀሳቀስባቸው” ባንኮች ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ነሐሴ 9፤ 2015 በጻፈው ደብዳቤ ማሳወቁን የቢሮው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ አለምነህ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እግዱ ከተጣለባቸው አስር ዞኖች መካከል፤ በስራቸው ያሉ ሁሉም መዋቅሮች ላይ  እርምጃው ተግባራዊ የሚደረግባቸው አራቱ ናቸው።  

የገንዘብ እንቅስቃሴ እገዳው ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ የሚደረገው በምዕራብ ጎጃም፣ ምስራቅ ጎጃም፣ ሰሜን ጎጃም እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች እንደሆነ በአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አደራጀው ካሴ ተጽፎ ለባንኮች የተሰራጨው ደብዳቤ ያመለክታል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” በተመለከተችው በዚሁ የደብዳቤ ክፍል ላይ እገዳው ተግባራዊ የሚደረግበት ብቸኛ የከተማ አስተዳደር ደብረታቦር ነው። 

ፎቶ፦ የደብረ ታቦር ከተማ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

የክልሉ መንግስት እገዳ “በተመረጡ አካባቢዎቻቸው” ብቻ ተፈጻሚ የሚሆንባቸው፤ የማዕከላዊ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎንደር፣ ሰሜን ሸዋ፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ ዞኖች እንዲሁም የአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር መሆናቸው በደብዳቤው ላይ ሰፍሯል። የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ይህንን ትዕዛዝ በዞኖች ላይ ከማስተላለፉ አራት ቀናት አስቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ለሁሉም የሀገሪቱ ባንኮች በጻፈው ደብዳቤ፤ የክልሉ መንግስት በሚያስተዳድራቸው የባንክ ሂሳቦች ስር ያለ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት መንገድ ላይ ገደብ ጥሎ ነበር።

በዚህ ገደብ መሰረት፤ የአማራ ክልል የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ሰማ ጥሩነህ እና የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጥላሁን መሐሪ “በጋራ ፈርመው ትዕዛዝ ካልሰጡ በስተቀር” የክልሉን መስሪያ ቤቶች ገንዘብ ማንቀሳቀስ እንደማይቻል የብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። የብሔራዊ ባንክ ይህንን ገደብ ያስቀመጠው፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያስፈጽም የተቋቋመው ጠቅላይ መመሪያ ዕዝ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ነው። 

ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ለብሔራዊ ባንክ ያቀረበው ጥያቄ፤ የአማራ ክልል መንግስት የባንክ ሂሳቦች “ላልተፈለገ ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዳይውሉ እና እንዳይመዘበሩ የጥንቃቄ እርምጃ” እንዲወሰድ የሚያሳስብ ነበር። በዚህ ጥያቄ መሰረት ነሐሴ 5፤ 2015 የተላለፈው የብሔራዊ ባንክ ገደብ ተግባራዊ ሆኖ የቆየው ለአራት ቀናት ብቻ ነው። የብሔራዊ ባንክ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በጻፈው ሌላ ደብዳቤ፤ ከአስቸኳይ ጊዜ ጠቅላይ መመሪያ ዕዝ በቀረበ ጥያቄ ትዕዛዙ መሻሩን አስታውቋል። 

የገደቡ መነሳት የአማራ ክልል መንግስት የባንክ ሂሳቦች፤ በመደበኛው የአስተዳደር ስርዓት እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል። ብሔራዊ ባንክ በአማራ ክልል ያለው የገንዘብ ዝውውር ወደ መደበኛ ስርዓቱ እንዲመለስ የተደረገው፤ “የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ተረጋግቶ እየተመለሰ ስለሚገኝ” እንደሆነ በባለፈው ሳምንቱ ደብዳቤው ላይ ጠቅሷል። ሆኖም ይህ ገደብ በተነሳበት ዕለት፤ የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ለባንኮች ሌላ የእግድ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

በደብዳቤ የተላለፈው ይህ እግድ በአስር ዞኖች እና አንድ የከተማ አስተዳደር ስር ያሉ አካባቢዎችን የሚመለከት እንደሆነ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ በደብዳቤው ላይ ዘርዝሯል። “ወረዳዎች ላይ፣ ዞኖች ላይ፣ አሁን በክልሉ በተፈጠረው ጸጥታ ምክንያት አንዳንድ ችግሮች ስላሉ፣ ቼኮች ደረሰኞች የጠፉበት ሁኔታ ስላለ፤ እነሱ እስከሚጣሩ ድረስ ዞኖች የሰጡንን መረጃ መሰረት በማድረግ የባንክ አካውንቶቹ እንዲታገዱ [ተደርጓል]” ሲሉ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ቢሮው ይህንን እርምጃ የወሰደው “የመንግስት ሀብት ለብልሽት እንዳይዳረግ፣ እንዳይባክን በማሰብ” መሆኑን የሚናገሩት አቶ ደሳለኝ፤ ይህ እግድ የሚቆየው “ዝርፊያ ተፈጸመ” በተባለባቸው አካባቢዎች የሚደረገው ማጣራት እስከሚጠናቀቅ ድረስ እንደሆነ አክለዋል። የማጣራት ስራው ተጠናቅቆ በአካባቢዎቹ የባንክ ሂሳቦች ውስጥ ያለው ገንዘብ እስከሚለቀቅ ድረስ ግን “የስራ ማንቀሳቀሻ እንቅስቃሴዎች የሚቆሙበት ሁኔታ ይፈጠራል” ሲሉ እግዱ ለጊዜው የሚያስከትለው ችግር እንደሚኖር ኃላፊው አምነዋል። 

ፎቶ፦ የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ

እገዳው በመንግስት ስራ ላይ መስተጓጎል ሊፈጥር ቢችልም፤ የመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ክፍያ ግን “እንደማይቋረጥ” አቶ ደሳለኝ ተናግረዋል። በዚህ ረገድ ችግር የማይፈጠረው፤ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ “በአካውንታቸው [በቀጥታ] የሚገባ” በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል። 

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ የገንዘብ እንቅስቃሴ እግድ መጣሉን ቢያረጋገጥም ትዕዛዙ ከተላለፈባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው የምስራቅ ጎጃም ዞን፤ ይህ አይነቱ ክልከላ እስካሁን በይፋ እንዳልደረሰው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል። የገንዘብ እንቅስቃሴ ላይ ስለተጣለ እግድ “መረጃ” እንዳልደረሳቸው እና እስካሁንም ስለጉዳዩ “አለመስማታቸውን” የሚናገሩት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አያሌው፤ “አሁን ስራ ስለጀመርን፤ የዞን አስተዳደር [ገንዘብ] እናንቀሳቅሳለን” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)