የአማራ ክልል ምክር ቤት ለመጪው አርብ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ  

በሃሚድ አወል

የአማራ ክልል ምክር ቤት በባህር ዳር ከተማ በሚገኘው የክልሉ ምክር ቤት አዳራሽ በመጪው አርብ ነሐሴ 19፤ 2015 የሚካሄድ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ። በዚህ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ለክልሉ ምክር ቤት አባላት ጥሪ የተላለፈው ትላንት ሰኞ ረፋድ መሆኑን ሁለት የምክር ቤቱ አባላት  ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አባላት ስብሰባው ከሚካሄድበት ዕለት አንድ ቀን በፊት በምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ተገኝተው ሪፖርት እንዲያደርጉ ቢነገራቸውም፤ የስብሰባው አጀንዳ እንዳልተገለጸላቸው አመልክተዋል። ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የክልሉ ምክር ቤት አባል “አስቸኳይ ስብሰባ ስለሆነ አጀንዳውን መናገር አልፈለጉም” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

ሆኖም እኙሁ የምክር ቤት አባል “ወቅታዊ የክልሉ ጉዳዮች”፤ የስብሰባው አጀንዳ ሊሆኑ እንደሚችሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር “ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ” በመሆኑ፤ የፌደራል መንግስት በክልሉ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወሳል። ከሐምሌ 28፤ 2015 ጀምሮ በክልሉ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ እንኳን አስፈላጊ ቢሆን፤ “አዋጁን ማውጣት የነበረበት የክልሉ ምክር ቤት ነው” የሚል ትችት ሲሰነዘር ቆይቷል። 

የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤውን ለመጨረሻ ጊዜ ያካሄደው ባለፈው ሐምሌ ወር አጋማሽ ነው። በዚሁ የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ላይ በክልሉ ያለው ወቅታዊ የሰላም እና የጸጥታ ጉዳይ ተነስቶ ውይይት ተደርጎበታል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ በወቅቱ ለምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር፤ “ያለምንም ገደብ በመመካከር የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ በፍጥነት ወደ መደበኛ ህይወታችን ልንመለስ ይገባል” ሲሉ አሳስበው ነበር። 

ዶ/ር ይልቃል፤ በአማራ ክልል ያለውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት በየዞኑ ካሉ የምክር ቤት አባላት አምስት አምስት ሰው ተመርጦ ምክክር እንዲጀመር ለክልሉ ምክር ቤት ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸው አይዘነጋም። ነገር ግን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይህን ሃሳብ ካቀረቡ ከሁለት ሳምንት በኋላ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በጻፉት ደብዳቤ “በክልሉ ያጋጠመውን የጸጥታ መደፍረስ” “በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች” በመሆኑ የፌደራል መንግስት በህገ መንግስቱ መሰረት “ተገቢውን እርምጃ” እንዲወስድ ጠይቀዋል። 

በዚህ ጥያቄ መሰረት እንደተነገገ በተገለጸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳቢያ፤ የአማራ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዩሃንስ ቧያለውን ጨምሮ 226 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል ፖሊስ አስታውቋል። በአርቡ የአማራ ክልል ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ “በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ” ይደረጋል ተብሎ ከሚጠበቀው ውይይት በተጨማሪ “ሹመት ሊኖር ይችላል” ሲሉ አንድ የምክር ቤት አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሌላ የክልሉ የምክር ቤት አባልም “በአንዳንድ አመራሮች ላይ ሹም ሽር የመደረግ ዕድል አለ” ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)