በአማኑኤል ይልቃል
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከመጪው 2016 ዓ.ም. ጀምሮ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን የሚቀበለው በምደባ ሳይሆን በውድድር መሆኑን አስታወቀ። ዩኒቨርስቲው ክፍያ የሚፈጽሙ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን “በልዩ” ሁኔታ ለማስተማር እንዳቀደም ገልጿል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይህንን ያስታወቀው የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ መሆኑን አስመልክቶ ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 16፤ 2015 በዋናው ቅጥር ግቢ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። መግለጫውን የሰጡት የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሙ ራስ ገዝ ለመሆን ላለፉት ሁለት ዓመታት ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር ስር ያሉ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ የተዘጋጀው አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው ባለፈው ግንቦት ወር ነበር። የዚህን አዋጅ መውጣት ተከትሎም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ እንዲሆን ያስቻለው ደንብ፤ ከሶስት ሳምንት በፊት ሐምሌ 28፤ 2015 በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የራስ ገዝነት ትግበራን የሚመራ ጽህፈት ቤት እና ግብረ ኃይል ያቋቋቋመው ባለፈው ጥር ወር ነበር። ግብረ ኃይሉ ጥናት ሲያደርግባቸው ከቆየባቸው ጉዳዮች መካከል የስትራቴጂክ እቅድ ክለሳ እንዲሁም የ“ሌጂስሌሽን” ክለሳ እና የመመሪያ ዝግጅት ይገኝበታል። ይኸው ቡድን በአስተዳደራዊ ማስፈጸሚያ ደንቦች እና መመሪያ ዝግጅት፣ የአደረጃጀት አሰራር እና አመራር፣ የሀብት ማመንጨት እንዲሁም የመሰረተ ልማት እና “ዲጂታይዜሽን” መስኮች ላይም ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል።
እነዚህ ጥናቶች ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ተጠናቅቀው ለውይይት እንደሚቀርቡ ፕሮፌሰር ጣሰው ተናግረዋል። “ጥናቱ ተጠናቅቆ፣ አግባብነት ባለው አካል ጸድቆ፣ [ደረጃ] በደረጃ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ትግበራ [በመግባት]፣ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሙሉ ሽግግር ይካሄዳል” ሲሉም የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት አካሄዱን አስረድተዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ራስ ገዝ መሆኑ፤ “በአስተዳደራዊ እና አካዳሚያዊ ጉዳዮች ላይ ነጻነት እንደሚሰጠው” ፕሮፌሰር ጣሰው በዛሬው መግለጫቸው ላይ በአጽንኦት አንስተዋል። ራስ ገዝነቱ ለዩኒቨርስቲው ከሚሰጠው አካዳሚያዊ ነጻነት ጋር ተይይዞ “ይመጣሉ” ከተባሉ ለውጦች ውስጥ፤ የስርዓተ ትምህርት በየጊዜው መከለስ፣ መምህራን “ሙሉ ጊዜያቸውን በዩኒቨርስቲ ውስጥ እንዲያሳልፉ” ማድረግ እንዲሁም “በርካታ የምርምር ፕሮጀክቶችን ማካሄድ” የሚሉት በማሳያነት ተጠቅሰዋል።
ዩኒቨርስቲው የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የሚቀበልበት መንገድ “በጣም ተገድቦ” እንደነበር የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ የራስ ገዝ ትግበራው በዚህ ረገድም ለውጥ እንደሚያመጣ ተናግረዋል። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በየዓመቱ ሰባት ሺህ ገደማ አዳዲስ ተማሪዎችን እንደሚቀበል ከዩኒቨርስቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል። መደበኛ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲው የሚገቡት፤ ልክ እንደሌሎች የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ሁሉ የትምህርት ሚኒስቴር በሚያደርገው ምደባ ነው።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ራስ ገዝነትን መተግበር ከሚጀምርበት ቀጣዩ 2016 የትምህርት ዘመን አንስቶ ግን የቅደመ ምረቃ ተማሪዎች የሚገቡበት ይህ አሰራር እንደሚቀር ፕሮፌሰር ጣሰው አስታውቀዋል። “ከ2016 ጀምሮ ዩኒቨርስቲው የመቁረጫ ነጥቡን ያለፉ ተማሪዎችን አወዳድሮ፣ የዩኒቨርስቲ ተልዕኮዬን ያሳኩልኛል የሚላቸውን ተማሪዎች ተቀብሎ ያስተምራል” ሲሉ ዩኒቨርስቲው የሚከተለውን አዲስ አሰራር ገልጸዋል።
አንጋፋው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የቅደመ ምረቃ ተማሪዎችን የሚያወዳድረው፤ ዩኒቨርስቲውን ከመቀላቀላቸው በፊት በሚሰጥ የመግቢያ ፈተና መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ማቲዮስ ኢንሰርሙ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ዩኒቨርስቲው እነዚህን የቅደመ ምረቃ ተማሪዎችን አወዳድሮ የሚያስገባው መንግስት በሚመድብለት በጀት እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ማቲዮስ፤ ከዚህ ውጪ ደግሞ ክፍያ እየፈጸሙ በዩኒቨርስቲው የሚማሩ ተማሪዎች እንደሚኖሩ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ “የትምህርት ጥራት ብዙም አይደለም” በሚል ምክንያት ወደ ውጭ ሀገር የሚጓዙ ተማሪዎች እንዳሉ የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ “በልዩ ሁኔታ” የሚሰጠው ትምህርት ቅደመ ክፍያ የሚፈጸሙ እነዚህን መሰል ተማሪዎች ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ አስታውቀዋል። እነዚህ ተማሪዎች እንዲማሩባቸው 50 “ስማርት” የመማሪያ ክፍሎች መዘጋጀታቸውን የጠቀሱት ዶ/ር ማቲዮስ፤ ለዚህም ዩኒቨርስቲው 26 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን ገልጸዋል።
“ለዚህ የሚመጥኑ መምህራንን ከውጭ እንቀጥራለን። ከዚህ ደግሞ የተሻሉ መምህራንን እንመድባለን። ጎን ለጎን ግን በመንግስት በጀት የሚገቡትን በሀገሪቱ የትምህርት ስታንዳርድ ማስተማር እንቀጥላለን” ሲሉ የዩኒቨርስቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ክፍያ እየፈጸሙ የሚማሩ ተማሪዎችን በተመለከተ የሚኖረውን የተለየ አሰራር አብራርተዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ “በልዩ ሁኔታ” ተማሪዎችን ለመቀበል ቢያቅድም፤ በእነርሱ እና በመንግስት በጀት የሚማሩ ተማሪዎች በሚወስዷቸው ትምህርቶች ስርዓተ ትምህርት ላይ ግን ልዩነት እንደማይኖር ዶ/ር ማቲዮስ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ዩኒቨርስቲው ይህን አዲስ አሰራር ከመጪው 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀምር የገለጹት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ ለዚህ የትምህርት አሰጣጥም “ከፍ ያለ” ክፍያ እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]