የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመጪዎቹ ሶስት ዓመታት “በአማካይ 8.3 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል”- ዶ/ር ፍጹም አሰፋ

በአማኑኤል ይልቃል

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት በአማካይ 8.3 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ አስታወቁ። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዚህ ዓመት በ9.2 በመቶ ያድጋል በሚል እቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ከሶስት ዓመት በኋላም በዚህ የእድገት መጠን ደረጃ ላይ እንደማይደርስ የፌደራል መንግስት ይፋ ያደረገው ሰነድ አመልክቷል። 

የፌደራል መንግስት የልማት እቅድ ሲያዘጋጅ የረጅም ጊዜውን በአስር ዓመት እና የመካከለኛ ጊዜውን ደግሞ በሶስት ዓመት ይከፋፈላል። በዚህ አሰራር መሰረት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት፤ ከ2013 ዓ.ም እስከ 2015 ድረስ የቆየ የመጀመሪያውን የመካከለኛ ጊዜ እቅድ አዘጋጅቶ እስከተጠናቀቀው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ሲተገብር ቆይቷል።   

በዚህ እቅድ የመጀመሪያ ዓመት፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ 8.5 በመቶ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ እቅድ ተይዞ ነበር። በ2014 ዓ.ም ወደ 8.7 በመቶ ከፍ እንደሚል የተገመተው የእድገት ምጣኔ፤ በዘንድሮው ዓመት ወደ 9.2 በመቶ እንደሚመነደግ በፌደራል መንግስት የእቅድ ሰነድ ላይ ሰፍሯል። ሆኖም ይህ እቅድ በተከታታይ ሶስት ዓመታት አለመሳካቱ ባለፉት ቀናት በተደረገ “የመካከለኛ ጊዜ አፈጻጸም” ግምገማ ላይ ይፋ ተደርጓል። 

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

የአስር ዓመት የልማት እቅድን መሰረት በማድረግ ከትላንት በስቲያ ሰኞ እና ትላንት ማክሰኞ ነሐሴ 16፤ 2015 የተደረገውን ግምገማ የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ናቸው። በዚህ ግምገማ ላይ የዘንድሮውን ጨምሮ ያለፉትን ሁለት ዓመታት እቅድ አፈጻጸም ያቀረቡት የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ዶ/ር ፍጹም፤ “የመጀመሪያው ሶስት ዓመት አፈጻጸም፤ ካጋጠሙ አለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ተግዳሮቶች አኳያ የተሻለ የሚባል [ነው]” ሲሉ በእቅድ ትግበራው የተገኘው ውጤት ጥሩ እንደነበር ገልጸዋል። 

እቅዱ በተተገበረባቸው ዓመታት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ “በርካታ” እና “ትልልቅ” የሚባሉ “ሁነቶች እና ተግዳሮቶች” ማጋጠማቸውን ያነሱት ዶ/ር ፍጹም፤ ለዚህም በማሳያነት የኮሮና ወረርሽኝ፣ ጦርነት እና የአየር ንብረት ለውጥን ጠቅሰዋል። እነዚህ ክስተቶች በፈጠሯቸው ተግዳሮቶች ምክንያት ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ እድገት “የመቀነስ አዝማሚያ” ማሳየቱንም ሚኒስትሯ አስታውሰዋል። 

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአንጻሩ እድገት እያሳየ መምጣቱን የጠቀሱት ዶ/ር ፍጹም፤ ይህ እድገትም በየዓመቱ መሻሻል የታየበት መሆኑን ገልጸዋል። የሶስት ዓመቱ እቅድ ትግበራ በተጀመረበት 2013 እና 2014 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ 6.3 በመቶ ማደጉን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ “ከእኛ ጋር ከሚወዳደሩ [ሀገራት] በተሻለ መልኩ ተወዳዳሪ የሆነ አፈጻጸም አይተናል” ሲሉ ግመገማውን ለታደሙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ሚኒስትሮች አስረድተዋል። 

የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ በኢኮኖሚ ዕድገት ረገድ የታየው አፈጻጸም “በመጠንም፣ በኢኮኖሚ ሁኔታም፣ በቀጣናው ካሉም ሀገራት” ጋር ሲነጻጸር “የተሻለ የሚባል ነው” ቢሉም፤ የኢትዮጵያ መንግስት በየዓመቱ “አሳካዋለሁ” በሚል ያስቀመጠው የእድገት መጠን ላይ ግን ያልደረሰ መሆኑ በገለጻቸው ላይ በተጠቀሟቸው ቁጥሮች ተንጸባርቋል። በፌደራል መንግስት የመካከለኛ ጊዜ እቅድ የመጀመሪያ ዓመት የተመዘገበው የ6.3 በመቶ እድገት፤ በእቅድ ተይዞ ከነበረው በ2.2 በመቶ የቀነሰ ነው። በ2014 ዓ.ም በተመሳሳይ ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር የ2.3 በመቶ ቅናሽ ታይቷል።

በተጠናቀቀው የ2015 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ7.5 በመቶ ማደጉን መንግስት ቢያስታውቅም፤ ይህም ቢሆን ግን በእቅድ ከተያዘው በ1.7 በመቶ ያነሰ ሆኖ ተመዝግቧል። ከኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል በሶስት ዓመቱ እቅድ የተቀመጣላቸውን ግቦች ባለማሳካት በቀዳሚነት የተቀመጡት ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ እና የወጪ ንግድ ናቸው። የግብርና ዘርፍ፣ የስራ እድል ፈጠራ እና የሬሚታንስ ፍሰት በአንጻሩ ከእቅድ በላይ የሆነ አፈጻጸም እንደታየባቸው በግምገማው ላይ የቀረበው ሰነድ አመልክቷል። 

ፎቶ፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

የፌደራሉ መንግስት ላለፉት ሶስት ዓመታት ሲተገብረው የቆየው የሶስት ዓመት የመካከለኛ እቅድ መጠናቀቁን ተከትሎ፤ ለመጪዎቹ ሶስት ዓመታት ተመሳሳይ እቅድ መዘጋጀቱን ዶ/ር ፍጹም በዚሁ ግምገማ ላይ ጠቅሰዋል። ከአስር ዓመቱ መሪ እቅድ የተቀዳው ይህ የሶስት ዓመት እቅድ ተግባራዊ የሚደረገው ከ2016 እስከ 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ነው። 

“የሁለተኛ መካከለኛ ዘመን የልማት እና ኢንቨስትመንት እቅድ” የሚል መጠሪያ በተሰጠው በዚህ ውጥን መሰረት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በየዓመቱ በአማካይ 8.3 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚገመት የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ተናግረዋል። በዚህ እቅድ መሰረት የ2016 የኢኮኖሚ እድገት 7.9 በመቶ ይሆናል በሚል ተተንብዩዋል፡፡ በ2017 ዓ.ም ይመዘገባል ተብሎ የተያዘው የኢኮኖሚ እድገት መጠን ደግሞ ከሶስቱ ዓመት አማካይ ጋር ተመሳሳይ ነው። 

ሆኖም በእቅዱ የመጨረሻ ዓመት የሚጠበቀው የኢኮኖሚ እድገት በአማካይ ከተጠቀሰው በ0.5 በመቶ ከፍ ይላል። በ2018 ይደረስበታል ተብሎ በእቅዱ የተቀመጠው የኢኮኖሚ እድገት፤ ዘንድሮ ተመዝግቧል ከተባለው በ1.6 በመቶ ጭማሪ ያለው ነው። የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ፤ አዲሱ የሶስት ዓመት እቅድ ሲዘጋጅ እንዲሳካ የሚያደርጉት “ታሳቢዎች” በግምት ውስጥ መግባታቸውን አስረድተዋል። አሁን ለተያዘው እቅድ መሳካት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ በሚል ዶ/ር ፍጹም ከጠቀሷቸው “ታሳቢዎች” ውስጥ፤ የመንግስት “ሪፎርም ውጤታማነት”፣ “የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች ወደ ውጤት መሸጋገር” እንዲሁም “የተሻለ ሰላም እና መረጋጋት” የሚሉት ይገኙበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)