በሃሚድ አወል
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዛሬ አርብ ነሐሴ 19፤ 2015 ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ አቶ አረጋ ከበደን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ ሾመ። አቶ አረጋ ከበደ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተሾሙት ላለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ ክልሉን የመሩት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ያቀረቡት የስልጣን መልቀቅ ጥያቄ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ነው።
አቶ አረጋ ከበደ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እስከተሾሙበት ዕለት ድረስ የአማራ ክልል የስራ ፈጠራና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ነበሩ። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በልማት አስተዳደር የሰሩት አቶ አረጋ፤ ወደ ክልል የኃላፊነት ቦታ የመጡት፤ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ረዳት የህዝብ ተሳትፎ አማካሪ በመሆን ነው። ከዚያ በመቀጠልም የክልሉ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል።
ከአራት ዓመታት በፊት በክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ ከተፈጸመው ጥቃት በኋላ አቶ አረጋ፤ የክልሉን ሚሊሺያ ጽህፈት ቤት በኃላፊነት እንዲመሩ ተሹመዋል። ነገር ግን በዚህ የኃላፊነት ቦታ ላይ የቆዩት ለአንድ ዓመት ያህል ብቻ ነው። በሐምሌ 2012 የክልሉ ቴክኒክ ሙያ እና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ኃላፊ በመሆን፤ የወቅቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህን ካቢኔ ተቀላቅለዋል።

አቶ አረጋ ከስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በኋላ በአማራ ክልል አዲስ መንግስት ሲመሰረት፤ የክልሉ የስራ ፈጠራ እና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል። አቶ አረጋ ወደ ክልል ኃላፊነት ከመምጣታቸው በፊት፤ በምስራቅ ጎጃም ዞን በወረዳ እና በዞን አመራርነት ሰርተዋል። አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የምስራቅ ጎጃም ዞንን በምክትል አስተዳዳሪ እና በዋና አስተዳዳሪነት መርተዋል።
በምስራቅ ጎጃም ዞን የእናርጅ እናውጋ ወረዳ ሚሊሺያ ጽህፈት ቤት፣ የአስተዳደር እና ጸጥታ ጉዳዮች እና የማስታወቂያ ጽህፈት ቤት አቶ አረጋ በኃላፊነት ካገለገሉባቸው ቦታዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። አቶ አረጋ በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ለአማራ ክልል ምክር ቤት የተወዳደሩትም፤ በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች ካገለገሉበት ከእናርጅ እናውጋ ወረዳ ደብረወርቅ ምርጫ ክልል ነው።
የአቶ አረጋ ሹመት የአማራ ክልልን ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ የርዕሳነ መስተዳድር ሹም ሽር የተካሄደበት ክልል አድርጎታል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ወደ ስልጣን ካመጣው የፖለቲካ “ለውጥ” በኋላ፤ አቶ አረጋ ክልሉን ለማስተዳደር ሲሾሙ አምስተኛው ርዕሰ መስተዳድር ናቸው።

ከ2006 ጀምሮ ክልሉን ለአምስት ዓመታት የመሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአራት ዓመታት ገደማ በፊት የስራ መልቀቂያ በማስገባታቸው፤ ዶ/ር አምባቸው መኮንን ክልሉን የማስተዳደር ኃላፊነት በየካቲት 2011 ዓ.ም. ተረክበው ነበር። ሆኖም ዶ/ር አምባቸው በስልጣን ላይ መቆየት የቻሉት ለሶስት ወራት ያህል ብቻ ነው። በሰኔ 2011 ዓ.ም. ዶ/ር አምባቸው ከሌሎች የክልሉ ባለስልጣናት ጋር በስብሰባ ላይ በነበሩበት ወቅት በተፈጸመባቸው ጥቃት መገደላቸው ይታወሳል።
የርዕሰ መስተዳድሩን ግድያ ተከትሎ በጊዜው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ የነበሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ ክልሉን የማስተዳደር ኃላፊነት ተረክበዋል። አቶ ተመስገን ክልሉን ለአንድ ዓመት ከሶስት ወራት ያህል ካስተዳደሩ በኋላ ከርዕሰ መስተዳድርነታቸው ተነስተው የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሹመዋል።
አቶ ተመስገን ወደ ፌደራል የኃላፊነት ቦታ መዘዋወራቸውን ተከትሎ፤ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በወቅቱ የተሾሙት አቶ አገኘሁ ተሻገር ናቸው። አቶ አገኘሁ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ከመሾማቸው በፊት የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ለዘጠኝ ወራት በኃላፊነት መርተዋል። አቶ አገኘሁ ወደ ክልሉ የፓርቲ ጽህፈት ቤት ከመምጣታችወው አስቀድሞ የአማራ ክልል የሰላም ግንባታ እና የህዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ ሆነውም ለስምንት ወራት ሰርተዋል።
አቶ አገኘሁ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው ለአስራ አንድ ወራት ያህል የአማራ ክልልን ካስተዳደሩ በኋላ፤ ለተሰናባቹ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ይልቃል ስልጣናቸውን አስረክበዋል። ተሰናባቹ ርዕሰ መስተዳድር ስልጣኑን የተረከቡት በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ጦርነት እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነበር። እርሳቸው በክልሉ ምክር ቤት ፊት ቃለ መሃላ በሚፈጽሙበት ወቅት የተወሰኑ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች በጊዜው ከመንግስት ጋር ውጊያ ላይ በነበሩት የትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ነበሩ።
የክልሉ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳደረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በግጭት ማቆም ስምምነት ቢጠናቀቅም የዶ/ር ይልቃል አመራር ግን ሌላ ፈተና አላጣውም። ከጥቂት ወራት በፊት የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ኃይሎችን “መልሶ ለማደራጀት” ከወሰነ በኋላ፤ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የጸጥታ ችግሮች በተደጋጋሚ ተከስተዋል። ከፍተኛ የክልሉን አመራሮች ጨምሮ ወረዳ እና የዞን ባለስልጣናትም በታጣቂዎች ግድያ ተፈጽሞባቸዋል።
በአማራ ክልል ያጋጠመው ይህን “የጸጥታ መደፍረስ” “በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች” መሆኑን በመግለጽ ዶ/ር ይልቃል ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በጻፉት ደብዳቤ፤ የፌደራል መንግስት በህገ መንግስቱ መሰረት “ተገቢውን እርምጃ” እንዲወስድ ጥያቄ አቅርበው ነበር። ከዚህ የርዕሰ መስተዳድሩ ደብዳቤ አንድ ቀን በኋላ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
ለ23 ወራት የአማራ ክልልን በርዕሰ መስተዳድርነት ከመሩ በኋላ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ያስታወቁት ዶ/ር ይልቃል፤ አብዛኛውን ዘመናቸውን ያሳላፉት በትምህርት ዘርፍ ላይ ነው። በታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሶሻል አንትሮፖሎጂ ደግሞ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙት ዶ/ር ይልቃል፤ ዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ባገኙበት ተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ከሕንዱ አንዱራ ዩኒቨርስቲ ተቀብለዋል።
ዶ/ር ይልቃል የአማራ ክልል መንግስትን በኃላፊነት ከመቀላቀላቸው በፊት በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ለ25 ዓመታት ያህል አገልግለዋል። ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ድረስ ያስተማሩት ዶ/ር ይልቃል፤ በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለሰባት ዓመታት ያህል በአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል። ለአንድ ዓመት ያህልም ዩኒቨርሲቲውን በፕሬዝዳንትነት መርተዋል።
ዶ/ር ይልቃል በቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በአማራ ክልል ካቢኔ የኃላፊነት ቦታ የተሰጣቸውም ከትምህርት ዘርፍ ጋር በተገናኘ ነው። ተሰናባቹ ርዕሰ መስተዳድር በ2009 ዓ.ም. የተሾሙበትን የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊነትን፤ ከአቶ ገዱ በኋላ በተተኩት ሶስት ርዕሳነ መስተዳድር ካቢኔዎች አስጠብቀው የቀጠሉ ነበሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)