በሃሚድ አወል
የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብይን ሰጠ። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ሰኞ ነሐሴ 22፤ 2015 በነበረው የችሎት ውሎ ከቀድሞው የክልል ርዕሰ መስተዳድር ጋር በአንድ መዝገብ ከተከሰሱ ግለሰቦች መካከል 16 ተከሳሾችን በነጻ ማሰናበቱን የአቶ አብዲ ጠበቃ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የአቶ አብዲን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የጸረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ችሎት፤ ለዛሬ ቀጠሮ ይዞ የነበረው ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ ላይ ብይን ለመስጠት ነበር። በዚህም መሰረት ጉዳያቸው በችሎቱ እየታየ ካሉት 42 ተከሳሾች ውስጥ 26 የሚሆኑት በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል።
በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ከተባሉት ተከሳሾች መካከል፤ የሶማሌ ክልልን ለስምንት ዓመት ያስተዳደሩት አቶ አብዲ መሐመድ ይገኙበታል። “አብዲ ኢሌ” በሚለው ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር እንዲከላከሉ የተበየነባቸው፤ “የጦር መሳሪያ ይዞ በማመጽ፣ ወይም የእርስ በርስ ጦርነት በማስነሳት በመንግስት ላይ የሚደረግ ወንጀልን” ፈጽመዋል በሚል በዐቃቤ ህግ የቀረበባቸውን ዋና ክስ መሆኑን ጠበቃቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ ደንበኛቸው ይህን የወንጀል ክስ “ይከላከሉ” የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰው፤ በችሎት የተሰሙ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች “ከሰጡት ቃል ተነስቶ” መሆኑን መግለጹን ጠበቃ እስክንድር አስረድተዋል። አቶ አብዲ ይህን ክስ በሚገባ መከላከል ሳይችሉ ጥፋተኛ የሚባሉ ከሆነ፤ የእድሜ ልክ ወይም የሞት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው በወንጀል ህጉ ላይ ተደንግጓል።
በዛሬው የችሎት ውሎ የፌደራል ዐቃቤ ህግ በአቶ አብዲ ላይ ከመሰረተው ዋና ክስ በተጨማሪ ያቀረበው “አማራጭ ክስ” ላይም ብይን መሰጠቱንም ጠበቃው አስታውቀዋል። በአማራጭነት የቀረበው ይህ ክስ፤ “በህገ መንግስትና እና በህገ መንግስት ስርዓት ላይ የሚደረግ ወንጀልን” የሚመለከትት መሆኑን አቶ እስክንድር ተናግረዋል። ነገር ግን ችሎቱ “ አማራጩን ክስ መሰረት አድርጎ በዐቃቤ ህግ በኩል የቀረበ የሰውም የሰነድም ማስረጃ የለም” በሚል ክሱን ውድቅ ማድረጉን የተከሳሽ ጠበቃው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በሶማሌ ክልል የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ በሌሎች የክልሉ ከፍተኛ ኃላፊዎች ላይ ክስ የመሰረተው፤ ከአምስት ዓመታት በፊት በጅግጅጋ ከተማ ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት እንደነበር ይታወሳል። ከግጭቱ መቀስቀስ በኋላ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ነሐሴ 20፤ 2010 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ፤ ከስብሰባው ሶስት ሳምንት በፊት ከስልጣናቸውን የተነሱትን የቀድሞውን የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ጨምሮ የሌሎች ምክር ቤት አባላትን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ አይዘነጋም።
ከዚህ የክልሉ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ ማግስት፤ አቶ አብዲ በአዲስ አበባ ከተማ በፌደራል ፖሊስ ተይዘው በቁጥጥር ስር ውለዋል። አቶ አብዲ አሌ ከታሰሩ ከስድስት ወራት በኋላ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከሌሎች 46 ተከሳሾች ጋር በአንድ መዝገብ ክስ መስርቶባቸው ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው ሲከታተሉ ቆይተዋል። በዚሁ የክስ መዝገብ ላይ ለቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እስር ምክንያት በሆነው ግጭት ሳቢያ፤ ከ59 ሰዎች በላይ መገደላቸውን እና ከ266 በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል እና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ሰፍሯል።
በሶማሌ ክልል ተቀስቅሶ በነበረው ግጭት በባንኮችና ኢንሹራንስ ተቋማት፣ በንግድ ድርጅቶችና በመንግስት መስሪያ ቤቶች እንዲሁም በግለሰብ መኖሪያ ቤቶችና ንብረት ላይ 412.4 ሚሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት በተጨማሪነት መድረሱ መግለጹ ይታወሳል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የዛሬውን የችሎት ውሎ ከማጠናቀቁ በፊት ክሳቸውን እንዲከላከሉ ብይን የሰጠባቸው ተከሳሾች፤ ከህዳር 3 እስከ ህዳር 7፤ 2016 መከላከያቸውን እንዲያቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)