የሶማሌ ክልል ካቢኔ የሀገር ሽማግሌዎች እና የጎሳ መሪዎች ጉባኤ እንዲቋቋም ውሳኔ አሳለፈ 

በሃሚድ አወል

የሶማሌ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት 114 አባላት ያሉት የሀገር ሽማግሌዎች እና የጎሳ መሪዎች ጉባኤ እንዲቋቋም ውሳኔ አሳለፈ። የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ትላንት ማክሰኞ ነሐሴ 23፤ 2015 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፤ የጉባኤውን ስልጣን እና ኃላፊነት የሚዘረዝረውን አዋጅ ለክልሉ ምክር ቤት መርቷል።

የጉባኤው አባላት የሚሆኑ የሀገር ሽማግሌዎች እና የጎሳ መሪዎች ዋነኛ ስራቸው “የማማከር ስራ” መሆኑን የሶማሌ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲቃድር ረሺድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። “በአንዳንድ አዳዲስ የሰፈራ ፕሮግራሞች ግጭት ስለሚከሰቱ፤ በግጭት ዙሪያ፣ በጎሳ ግጭት ዙሪያ፣ በልማት ዙሪያ የሚያማክሩን ይሆናል” ሲሉ የቢሮው ኃላፊው አስረድተዋል።

የጉባኤው አባላት በመሆን የሚመረጡት የሀገር ሽማግሌዎች የተለያዩ የጎሳ ማህበረሰብ ቅንርጫፎችን የሚወክሉ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አብዲቃድር፤ “ከአዋጁ መጽደቅ በኋላ በሚወጣ መመሪያ የአባላት ምርጫ በግልጽ የሚቀመጥ ይሆናል” ብለዋል። በዚህ መመሪያ መሰረት የሚመረጡት የጉባኤው አባላት በሚያደርጉት ስብሰባ፤ የጉባኤውን ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር እንደሚመርጡም አመልክተዋል። የጉባኤው ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበር በበኩላቸው፤ በአዋጁ በተቀመጠላቸው ስልጣን መሰረት “አስፈላጊ የሆኑ ሹመቶችን” እንደሚሰጡ የቢሮ ኃላፊው አክለዋል። 

የሶማሌ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ጉባኤውን በሚያቋቁመው አዋጅ ላይ ተወያይቶ ለክልሉ ምክር ቤቱ ያስተላለፈው፤ በክልሉ ህገ መንግስት ድንጋጌ መሰረት ነው። በ1994 ዓ.ም. የተሻሻለው የሶማሌ ክልል ህገ መንግስት፤ የሀገር ሽማግሌዎች እና የጎሳ መሪዎች ጉባኤ እንደሚቋቋም እና ዝርዝሩ በህግ እንደሚወሰን ደንግጎ ነበር። ሆኖም ይህ ድንጋጌ ለ22 ዓመት ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል። 

“ጉባኤውን ለማቋቋም አልዘገያችሁም ወይ?” የሚል ጥያቄ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የቀረበላቸው የሶማሌ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ፤ “አሁን ያለው [የክልሉ] መንግስት በምርጫ ከተመሰረተ ሁለተኛ ዓመታችን ነው። ኃላፊነት የምንወስደው የእኛ መንግስት ከተቋቋመ በኋላ ስላለው ጊዜ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ ክልሉን እየመራ የሚገኘው የአሁኑ አስተዳደር፤ ጉባኤውን ለማቋቋም “ህጎችን በማጥናት፣ ልምድ በመውሰድ [እና] ሰነዶችን ሲያዘጋጅ” መቆየቱን አቶ አብዲቃድር አብራርተዋል።   

እንዲህም ቢሆን ግን አሁን በስልጣን ላይ ያለውም ሆነ ከዚያ ቀደም የነበረው የክልሉ መንግስት፤ የሀገር ሽማግሌዎችን በአጋዥነት ሲጠቀም መቆየቱን የቢሮ ኃላፊው ገልጸዋል። “በአዋጅ ደረጃ ነው ያልጸደቁት እንጂ፤ የሀገር ሽማግሌዎች እስከ ዛሬ ድረስ በinformal ደረጃ ከመንግስት ጎን ሆነው ሲያግዙ ነበር” ሲሉ አቶ አብዲቃድር ተናግረዋል። “በአዋጅ ደረጃ ሀገር ሽማግሌዎችን እውቅና የሰጠናቸው፤ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ግጭቶችም ስለሚኖሩ፣ በማህበረሰቡም በግጦሽ፣ በውሃ፣ በመሳሰሉት ነገሮች ግጭቶች እንዳይኖሩ፣ እንዲያግዙን ለማድረግ ነው” ሲሉም ጉባኤውን የሚያቋቁመው አዋጅ የተዘጋጀበትን ምክንያት አስረድተዋል። 

አዋጁ “ሀገር ሽማግሌዎቹ ራሳቸው ቢያጠፉ ተጠያቂ የሚደረጉበትን” ድንጋጌ እንዳካተትም የሶማሌ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አመልክተዋል። ሀገር ሽማግሌዎች እና የጎሳ መሪዎች ጉባኤን የሚያቋቁመው አዋጅ፤ የሶማሌ ክልል ምክር ቤት በሚያካሄደው ቀጣይ ስብሰባ ላይ ለውይይት ከቀረበ በኋላ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)