የሀዋሳ ከተማ ምክር ቤት በመጪው ሰኞ በሚያካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ በተሰናባቹ አቶ ጸጋዬ ቱኬ ምትክ አዲስ ከንቲባ ሊሾም ነው 

በሃሚድ አወል

የሀዋሳ ከተማ ምክር ቤት በመጪው ሰኞ ነሐሴ 29፤ 2015 በሚያካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የከተማዋን ከንቲባ ጨምሮ የካቢኔ አባላትን ሹመት ሊሰጥ ነው። የከተማዋ ምክር ቤት ሹመቶችን የሚሰጠው፤ የሲዳማ ክልል ካደረገው ግምገማ በኋላ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችም እንዲነሱ መወሰኑን ተከትሎ ነው።

የሲዳማ ክልል ከአንድ ሳምንት በፊት ካካሄደው የፓርቲ እና የመንግስት አፈጻጸም ግምገማ በኋላ፤ “ብልሹ አሰራር ፈጽመዋል” ያላቸውን 10 ከፍተኛ አመራሮችን ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቆ ነበር። በዚህ ግምገማ ከስልጣናቸው እንዲነሱ ውሳኔ ከተላለፈባቸው ባለስልጣናት መካከል ሰባቱ በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ተመድበው የሚሰሩ ከፍተኛ አመራሮች መሆናቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያገኘችው ዝርዝር ያመለክታል። 

ከእነዚህ የከተማይቱ አስተዳደር አመራሮች ውስጥ በስልጣን ከፍተኛውን ቦታ የያዙት፤ ለሶስት ዓመታት ገደማ ሀዋሳን በከንቲባነት የመሩት አቶ ጸጋዬ ቱኬ ናቸው። የእርሳቸው ምክትል እና የሀዋሳ ከተማ ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሚልክያስ ባትሬ፣ የከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘርይሁን ሰለሞን፣ የከተማይቱ የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ መኩሪያ ማኒሳም ተመሳሳይ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።  

የሀዋሳ ከተማ የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታ ዳንኤል፣ የሲቪል ሰርቪስና የሰው ኃይል መምሪያ ኃላፊ አቶ ሳርሚሶ ሳሙኤል፣ የባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ዳጊቱ ጫሌ እንዲሁ ከኃላፊነት እንዲነሱ የተደረጉ አመራሮች ናቸው። ዘጠኝ ቀናት በፈጀው የሲዳማ ክልል ግምገማ ወቅት “የሀዋሳ ከተማ ጉድለት ከታየባቸው መዋቅሮች አንዱ መሆኑ ተደጋግሞ” መነሳቱን በስብሰባው የተሳተፉ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ተናግረዋል።

በዚህ ግምገማ የማጠናቀቂያ መድረክ ላይ በ“ብልሹ አሰራር” እና “አፈጻጸም ድክመት” ተገምግመው ከስልጣናቸው የተነሱ ኃላፊዎች በህግ ተጠያቂ እንደሚደረጉ ተገልጾ ነበር። ነገር ግን እስካሁን ድረስ አቶ ጸጋዬን ጨምሮ ሌሎች የሀዋሳ ከተማ አመራሮችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ሂደት አለመጀመሩን በከተማይቱ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ውስጥ የሚሰሩ ሁለት ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር  ከፍተኛ ኃላፊ “ችግር ያለባቸው እና በሙስና የተዘፈቁ ሰዎች ካሉ፤ በክልሉ ጸረ ሙስና ኮሚሽን እየተለዩ፤ ዐቃቤ ህግ ጋር እየተላለፈ የሚካሄድ ተጠያቂነት አለ” ሲሉ በቀጣይነት የሚጠበቀውን ሂደት አስረድተዋል። ሌላኛው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጭም፤ “ከጸረ ሙስና እና ከክልሉ ኦዲት ቢሮ ሪፖርት ከቀረበ በኋላ በዐቃቤ ህግ ክስ ሊመሰረት ይችላል” ሲሉ ይህንኑ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥተዋል።

ፎቶዎች፦ ከ“ሆርን ትሪቢዩን” የተወሰዱ

የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጸጋዬ እና ሌሎች ስድስት የካቢኔያቸው አባላት ከስልጣን ከተነሱ በኋላ ባሉት ሳምንታት፤ የከተማዋን የስራ እንቅስቃሴ ሲመሩ የቆዩት የሀዋሳ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሱ አሩሳ ናቸው ተብሏል። የሀዋሳ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ ደምሴ ዳንጊሶ “የከተማዋ የድርጅት ሰብሳቢ ከጸጥታ ኃላፊዎች ጋር እየተገናኙ እንዲሰሩ” በሲዳማ ክልል መንግስት “አቅጣጫ መቀመጡን” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። 

በክልል አቀፍ ግምገማው ከስልጣናቸው ያልተነሱ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ አባላት እንዳሉ ያስታወሱት አፈ ጉባኤው፤ እነዚህ አመራሮች በየዘርፋቸው በኃላፊነታቸው የሚጠበቅባቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል። ላለፉት ሁለት ሳምንታት የሀዋሳ ከተማ መንግስታዊ ስራዎች “በኮሚቴ” ይሰሩ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ደምሴ፤ የሀዋሳ ከተማ ምክር ቤት ከሁለት ቀናት በኋላ በሚያካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ በተነሱት አመራሮች ምትክ ሹመቶችን እንደሚሰጥ አመልክተዋል።  

በመጪው ሰኞ ለሚካሄደው ለዚህ አስቸኳይ ጉባኤ፤ ዛሬ አርብ ነሐሴ 26፤ 2015 ለከተማይቱ ምክር ቤት ለአባላት ጥሪ እንደተላለፈላቸው አፈ ጉባኤው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የሰኞው ጉባኤ ብቸኛ አጀንዳ፤ በሰሞኑ ግምገማ ከቦታቸው በተነሱት የሀዋሳ ከንቲባ እና ሌሎች የከተማይቱ አስተዳደር የካቢኔ አባላትን  የሚተኩ ኃላፊዎችን መሾም እንደሆነም አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)