በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ መድረኮች ላይ “ክፍተት እየተፈጠረብን ነው” – አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ እና የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይን በተመለከተ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት የቀደመ እንቅስቃሴ ላይ “ክፍተት እየተፈጠረ መምጣቱን” የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ በፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ስር መደረጉ ቀርቶ ራሱን ችሎ በተቋቋመ መስሪያ ቤት መመራት ይገባዋል ብለዋል። 

በኬንያ መዲና ናይሮቢ ዛሬ ሰኞ በተጀመረው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ ኃይለማርያም፤ “የኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ከፍ ብሎ መታየት አለበት የሚል እምነት አለኝ” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በእነዚህ ዘርፎች ኢትዮጵያ አሁን ያላት አደረጃጀት ላይ “የሚቀራት ነገር እንዳለ ይታያል” ያሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር፤ የአካባቢ፣ የአየር ንብረት እና የደን ጉዳዮችን የሚከታተል ራሱን የቻለ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ያላት ኬንያ በዚህ ረገድ የተሻለች መሆኗን መስክረዋል።  

“ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ visibility በጣም ደካማ ነው። በዚህ መድረክም ታያለህ። ባለፈው በCOP 27 ላይም አይተናል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተናገሩት አቶ ኃይለማርያም፤ ዘርፉን የሚከታተለው አካል ከፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ስር ወጥቶ “ይህንን ስራ ብቻ በሚከታተል አካል” መመራት እንዳለበት ምክረ ሃሳባቸውን ለግሰዋል። “ኢትዮጵያ ቀድሞ የነበራት አደረጃጀት ቢመለስ ደስ ይለኛል” ሲሉም አክለዋል። 

አቶ ኃይለማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ፤ የአካባቢ፣ የደን እና አየር ንብረትን ጉዳይን የሚከታተል ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ተቋቁሞ እንደነበር አይዘነጋም። እርሳቸው የተኳቸው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ በኢኮኖሚ ካደጉ ሀገራት ጋር በሚደረጉ ንግግሮች ላይ የአፍሪካ አህጉርን በመወከል ጠንካራ አቋም ያንጸባርቁ  እንደነበር አይዘነጋም። 

በዚህ ረገድ በአሁኑ ወቅት “ከፍተኛ የመሪነት ሚና እየተጫወቱ የሚገኙት” የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ኃይለማርያም፤ “የግድ በአንድ ሰው ጎልቶ በመውጣት ብቻ ሳይሆን እንደ ተቋም እና እንደ ሀገር ጎልቶ በመውጣት ሚና መጫወት ይቻላል” ሲሉ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ሊኖራት የሚገባት ቦታ ምን መሆን እንዳለበት አስገዝበዋል። ኢትዮጵያ ከኬንያ እና ከሌሎች ሀገራት ጋር በመተባበር “የአፍሪካን አጀንዳ ይዞ ለመውጣት” “ምቹ ሁኔታ አላት” ብለው እንደሚያምኑም አስታውቀዋል። (በአማኑኤል ይልቃል – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)