በሃሚድ አወል
በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ 50 ገደማ ከተሞች የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አማራጮችን በተመለከተ ግብዓት ሲያሰባስብ የቆየው የባለሙያዎች ቡድን፤ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት አራት የምክክር መድረኮችን ሳያካሄድ መቅረቱን አስታወቀ። የባለሙያዎች ቡድኑ ረቂቅ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሰነዱን በመጪው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ለማጠናቀቅ ማቀዱንም ገልጿል።
የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሰነድ የሚያዘጋጀው፣ አስራ አራት አባላት ያሉበት የባለሙያዎች ቡድን በፍትህ ሚኒስቴር አማካኝነት የተቋቋመው ባለፈው ህዳር ወር ውስጥ ነበር። የባለሙያዎች ቡድኑ የሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አማራጮች ላይ የሚያደርጋቸውን ምክክሮች የሚመራበት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ወደ ውይይት የገባው ከአራት ወራት በፊት ነው።
በአዳማ ከተማ የተጀመረው የምክክር መድረክ፤ 46 ከተሞችን አካልሎ በነሐሴ ወር መጀመሪያ በአዲግራት ከተማ በተካሄደ ውይይት መጠናቀቁን የባለሙያዎች ቡድኑ ዛሬ ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ቡድኑ በአጠቃላይ ሊያካሄዳቸው አቅዷቸው የነበሩ የምክክር መድረኮች ብዛት 59 ቢሆኑም፤ በጸጥታ ችግር ምክንያት አራት ያህሉን መሰረዙን የባለሙያዎች ቡድን አባል የሆኑት ዶ/ር ማርሸት ታደሰ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል።
የባለሙያዎች ቡድኑ በዚህ ምክንያት ምክክር ማድረግ ያልቻለባቸው ከተሞች በኦሮሚያ ክልል የሚገኙት ደምቢ ዶሎ እና ያቤሎ እንዲሁም በአማራ ክልል በሚገኙት ሰቆጣ እና ደብረ ማርቆስ መሆናቸውን ዶ/ር ማርሸት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። የባለሙያዎች ቡድኑ ከእነዚህ ከተሞች በተጨማሪ የትግራይ እና የአማራ ክልሎች “የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው” ወልቃይት እና ሁመራ ከተሞች ሊያካሄድ አቅዶት የነበረውን ምክክርም ሳያከናውን ቀርቷል።
በሽግግር ፍትህ የፖሊሲ አማራጮች ላይ በወልቃይት እና ሁመራ ምክክር ያልተደረገው፤ በአካባቢው ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት መሆኑን ዶ/ር ማርሸት አስረድተዋል። “አሁን አውዱ አይፈቅድም። ‘የሆነ ቡድን ተሳታፊ ተደርጓል፤ የሆነ ቡድን ተሳታፊ አልተደረገም’ የሚል ቅሬታ እንዲነሳ አንፈልግም” ሲሉ በሁለቱ ከተሞች ከተሰረዘው ምክክር ጀርባ ያለውን ምክንያት የባለሙያዎች ቡድኑ አባል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶች የቡድኑ ስራ ላይ “ተግዳሮት” ቢፈጥሩም፤ የጸጥታ ችግሮች እያሉም ቢሆን የሽግግር ፍትህ ሂደቱን ማድረግ “አንገብጋቢ እና ግዴታም ጭምር” መሆኑን ዶ/ር ማርሸት በዛሬው መግለጫ ላይ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የጸጥታ ችግሮች የሂደቱን አስፈላጊነት “አጉልተው የሚያሳዩ ናቸው” የሚሉት ዶ/ር ማርሸት፤ እሳርቸው እየተሳተፉበት ያሉበት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ዝግጅት ሁኔታዎችን “ወደ ተሻለ ሁኔታ ለማምጣት የሚረዳ መንገድ” አድርገው እንደሚቆጥሩት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የባለሙያዎች ቡድን አባሉ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ “በሁሉም አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም” መፍጠር እንደሚያስፈልግ በዛሬው መግለጫቸው አስገንዝበዋል። “ለምናስበው ትግበራ እነዚህን ሁኔታዎች እና ችግሮች ካልተፈቱ ትግበራውን በተሟላ መንገድ ለማከናወን የሚቻል አይሆንም” ሲሉ ዶ/ር ማርሸት አጽንኦት ሰጥተዋል። የሽግግር ፖሊሲው ወደ ተግባር ከመግባቱ አስቀድሞ ግን በባለሙያዎች ቡድኑ ዘንድ የሚከናወኑ ስራዎች እንዳሉ ሌላኛው የባለሙያዎች ቡድን አባል ዶ/ር ታደሰ ካሳ ተናግረዋል።
የቡድኑ ቀጣይ ስራ በ47 ከተሞች በተደረጉ ምክክሮች የተሰበሰበውን ግብዓት “ሲስተማቲክ በሆነ መንገድ ማደራጀት እና መተንተን” መሆኑን ዶ/ር ታደሰ ጠቁመዋል። ይህን ትንተና ተከትሎ የሚቀጥለው ስራ የማጠቃለያ ሪፖርት ማዘጋጀት መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ታደሰ፤ በመጪዎቹ “ጥቂት ሳምንታት” የረቂቅ ፖሊሲው ሰነድ እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል። የባለሙያዎች ቡድኑ ረቂቅ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ሰነዱን ለማጠናቀቅ ያቀደው በመጪው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ መሆኑን ሌላኛው የቡድኑ አባል ዶ/ር ማርሸት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)