35 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሀገር አቀፍ የሰላም መድረክ እንዲመቻች ጥሪ አቀረቡ

በሃሚድ አወል

ሰላሳ አምስት ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሁሉንም የማህበረሰብ አካላት የሚያሳትፍ ሀገር አቀፍ የሰላም መድረክ እንዲመቻች ጥሪ አቀረቡ። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ በዚህ ዓመት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተስተዋሉ “አዳዲስ እና ነባር ግጭቶች በመጪው ዓመትም ተባብሰው እንዳይቀጥሉ” ያላቸውን ስጋትም ገልጸዋል። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ይህን የገለጹት ዛሬ ረቡዕ ጷጉሜ 1፤ 2015 ባቀረቡት “የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ” ነው። ድርጅቶቹ መጪው 2016 ዓ.ም. “የዜጎችን መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች እና ነጻነቶችን የሚያጣብቡ ግጭቶች የሚቀጥሉበት እንዳይሆን በማሰብ” አስር ጥሪዎችን ማቅረባቸውን በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባው ካፒታል ሆቴል በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። ድርጅቶቹ በቀዳሚነት ያቀረቡት ጥሪ “ሁሉንም የማህበረሰብ አካላት የሚያሳትፍ ሀገር አቀፍ የሰላም መድረክ (የሰላም ኮንቬንሽን)” እንዲመቻች የሚጠይቅ ነው። 

በድርጅቶቹ የተጠየቀው የሰላም መድረክ ዋና ዓላማ “ወደ ነውጥ ሊያድጉ የሚችሉ ውጥረቶችን ለመከላከል እና መልስ እንዲገኝላቸው ለማስቻል” መሆኑን የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) የተሰኘው የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር አቶ በፍቃዱ ኃይሉ በመግለጫው ላይ ተናግረዋል። በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች መንስኤ ቀድሞ እንደሚታይ የጠቆሙት የካርድ ዋና ዳይሬክተር፤ “በሰላማዊ መንገድ እየተፈቱ ያሉ ግጭቶች ዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲገነባላቸው” ማስቻል ሌላኛው የሰላም መድረኮቹ ዓላማ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል። 

የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪውን ካቀረቡ ድርጅቶች አንዱ የሆነው የስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር መሰረት አሊ፤ የሰላም መድረኮቹ “ሁሉንም አካላት ያቀፈ ሁሉንም የግጭት ተዋንያን ያሳተፉ” ሊሆኑ አንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል። የሰላም መድረኮቹ ከመዲናዋ አዲስ አበባ በተጨማሪ ከቀበሌ እስከ ክልል ድረስ ባሉ መዋቅሮችም ሊካሄዱ እንደሚገባ ዋና ዳይሬክተሯ አሳስበዋል። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ የሰላም መድረክ እንዲመቻች ቢጠይቁም፤ ቀደም ሲል በመንግስት በኩል የተጀመሩ የሀገራዊ ምክክር እና የሽግግር ፍትህ ተነሳሽነቶችን ዕውቅና እንደሚሰጡ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከአራት ወራት በፊት በህዝባዊ የምክክር መድረኮች የተጀመረው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ዝግጅት፤ “በሀቀኝነት እና ህዝባዊ ተቀባይነት ባለው መንገድ” ወደ ተግባር እንዲገባ ድርጅቶቹ ጠይቀዋል።

በሰላም፣ በዲሞክራሲ እና በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሰሩት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያቀረቡት ሌላኛው ጥሪ ተጠያቂነትን የተመለከተ ነው። ድርጅቶቹ “ለነውጥ አዘል ግጭቶች መንስኤ የሆኑ”፣ “በነውጥ አዘል ግጭቶች ውስጥ በመሳተፍ ንጹሃንን ያጠቁ” እና “ንጹሃንን ለጥቃት ያጋለጡ” ያሏቸው አካላት “በነጻ እና ገለልተኛ የፍትሃዊ የምርመራ እና የዳኝነት ሂደት ተጠያቂ እንዲደረጉ” ጥሪ አቅርበዋል። 

በግጭቶች ወቅት በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን” ድርጅቶቹ በዛሬው መግለጫቸው አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ “የችግሩን አሳሳቢነት የሚመጥን ትኩረት አልተሰጠውም” ያሉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ፤ ለተጎጂዎች የጤና እና የስነ ልቦና ድጋፍ መስጠትን ጨምሮ “በቂ እርምጃዎች እንዲወሰዱ” ጠይቀዋል። ድርጅቶቹ ከዚህ በተጨማሪ “የቅድመ ግጭት መጠቆሚያ እና መከላከያ ስርዓት” እንዲኖር፣ “ተጋላጭ እና ግፉአን” ላሏቸው የማህብረሰብ ክፍሎች የጥበቃ ማዕቀፍ እንዲዘረጋ፣ የጥላቻ ንግግር እና የተዛቡ መረጃዎች ስርጭት እንዲቆም እንዲሁም የሰብዓዊ  ድጋፍ አቅርቦት ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል ጥሪ አስተላለፈዋል። 

የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች እና ጋዜጠኞች፣ በስራዎቻቸው ሳቢያ “የዘፈቀደ እስር፣ ማሰቃየት፣ አስገድዶ መሰወር፣ ሞት እና ሌሎችም የማዋከብ ድርጊቶች እየተፈጸሙባቸው” እንደሚገኝ በመግለጫቸው የጠቀሱት ድርጅቶቹ፤ ይህ ድርጊትም በህግ የተሰጣቸውን “ሀሳብን የመግለጽ፣ የመደራጀት እና የመሰብሰብ መብቶች የሚያፍን ነው” ሲሉ ተችተዋል። የሚዲያ እና የሲቪክ ምህዳር በቂ ጥበቃ እንዲደረግለት፤ መንግስትም “ህገ መንግስታዊ ግዴታውን” እንዲወጣ የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶቹ ጠይቀዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች “የአዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ” በሚል ርዕስ፤ በሀገሪቱ ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ እና ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ ሲያቀርቡ የዛሬው ለሶስተኛ ጊዜ ነው። የመጀመሪያው የሰላም ጥሪ በድርጅቶቹ በኩል የተላለፈው ከሁለት ዓመት በፊት በ2013 መጨረሻ ላይ ነበር። ይህን የሰላም ጥሪ በአንድ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን ያስተላለፉት 24 ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ነበሩ። በቀጣዩ የ2014 ዓ.ም. ጥሪውን ያቀረቡት ድርጅቶች ቁጥር በ11 ቢጨምርም የተላለፈው የሰላም ጥሪ ግን ተመሳሳይ ይዘት የነበረው ነው።

ድርጅቶቹ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የሰላም ጥሪዎችን ቢያቀርቡም በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ መደፍረስ አንዴ ጋብ አንዴ ፋም ከማለት ባለፈ ግጭቶች ከእነ አካቴው መቆም አልተቻላቸውም። ድርጅቶቹ በአዲስ አበባው ካፒታል ሆቴል በዛሬው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የእነዚህ ተደጋጋሚ ጥሪዎች ምላሽ አለማግኘትን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸዋል። 

የሰላም ጥሪውን ካቀረቡት ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳን ይርጋ “በምናደርገው ጥሪ መጠን ምላሽ እያገኘን እንዳልሆነ እኛም የምንረዳው ነው” ሲሉ በጥያቄውን የተነሳውን ሃሳብ ተጋርተዋል። “እኛ እንደ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ማድረግ የምንችለው ጥሪ ማቅረብ ነው” ያሉት አቶ ዳን፤ “በአገኘነው መድረክ የሚመለከታቸውን መንግስት አካላት እንጠይቃለን። ክትትል እናደርጋለን። የውትወታ ስራም እንሰራለን” ሲሉ ከመንግስት በኩል ምላሽ ለማግኘት ስለሚያደርጉት ጥረት አብራርተዋል። 

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጥሪያቸውን ለመንግስት አስፈጻሚ አካላት በቀጥታ ለማቅረብ አቅደው እንደሆነ ለተነሳላቸው ጥያቄ፤ የሴታዊት ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ስህን ተፈራ “ይሄንን ጥሪ ስናቀርብ መንግስት ጋር መሄድ አንችልም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ዶ/ር ስህን ምክንያቱን ሲያብራሩም “ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጥሪ ስናቀርብ የጠራነው ጋዜጣዊ መግለጫ ተከልክሏል። ከዚያም ተጠርተን ‘ትዝጋላችሁ’ ብለው አስፈራርተውናል። ስለዚህ እንዴት ነው እንድንሄድ የምትጠብቁት? መሄድ አላሰብንም” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ በፍቃዱ በበኩላቸው “ይኼኛውንም መግለጫ ስናደርግ፣ ከዚህ በፊት ያደረግናቸው ጥሪዎችም ሲወጡ፣ አስፈጻሚ አካላትን እንደደረስን ነው የምናውቀው” ሲሉ አስረድተዋል። ጥሪዎቹ በመገናኛ ብዙሃን እና በሌሎች መድረኮች ሲሰራጩ የአስፈጻሚው አካል “ሳይሰማ ይቀራል” ብለው እንደማያስቡ አቶ በፍቃዱ አክለዋል። እንደ ዶ/ር ስህን ሁሉ አቶ በፍቃዱም፤ ድርጅቶቹ ከዚህ ቀደም ባስተላለፏቸው ጥሪዎች ምክንያት “አዎንታዊ ያልሆኑ” ምላሾች እንደደረሷቸው ገልጸዋል። 

“አንዳንድ ጊዜ አዎንታዊ ያልሆኑ ምላሾች ይደርሱናል። ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ያወጣነው መግለጫ አንዳንድ የመንግስት ኃላፊዎችን እንዳናደዳቸው፤ ሰብስበውን ባደረጉት ቁጣ እና ተግሳጽ አስተውለናል” ሲሉ የዛሬ ዓመት ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ተከትሎ የነበረውን ሁኔታ አብራርተዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባው ኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል የሰላም ጥሪ ለማቅረብ ያዘጋጁት ጋዜጣዊ መግለጫ በጸጥታ ኃይሎች ቢከለከልም፤ በበይነ መረብ አማካኝነት ግን ጥሪያቸውን ማስተላለፋቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)