“ትንሣኤ 70 እንደርታ” የተሰኘ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀስ ፓርቲ፤ መስራች ጉባኤውን በነገው ዕለት ሊያካሄድ ነው  

በሃሚድ አወል

በትግራይ ክልል “የተንሰራፋውን ጭቆና እና የአንድ ፓርቲ ስርዓት” ለመታገል መነሳቱን የገለጸው ትንሣኤ 70 እንደርታ ፓርቲ (ትሰእፓ) የተሰኘ ክልላዊ ፓርቲ፤ መስራች ጉባኤውን ነገ አርብ ጷጉሜ 3 በአዲስ አበባ ከተማ ሊያካሄድ ነው። በትግራይ ክልል “ህብረ ብሔራዊ ስርዓት እንዲፈጠር” እንደሚታገል የጠቆመው ፓርቲው፤ ይህ የማይሳካ ከሆነ የእንደርታ ህዝብ “ከሌሎች ህዝቦች ጋር በጋራ ወይም ለብቻው” “የራሱን ክልላዊ መንግስት” እንዲመሰርት እንደሚታገልም አስታውቋል።

ከሰባት ወራት በፊት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ ምዝገባ ፈቃድ ያገኘው ትሰእፓ፤ ጠቅላላ ጉባኤውን ከዛሬ ሐሙስ ጷጉሜ 2፤ 2015 ጀምሮ እንደሚያካሄድ አስቀድሞ ገልጾ ነበር። ይህንን ተከትሎም የፓርቲው አባላት እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ጠቅላላ ጉባኤው በሚካሄድበት የአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ ተገኝተው ነበር። 

ሆኖም መስራች ጉባኤውን ለመታዘብ በቦታው የተገኙት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች፤ ስብሰባው ከመደረጉ አስቀድሞ መሟላት የሚገባቸው ነገሮች አለመሟላታቸውን በማስታወቃቸው ጠቅላላ ጉባኤው ለነገ መተላለፉን የፓርቲው አመራሮች በስፍራው ለተገኘው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ ተናግረዋል። አመራሮቹ በምርጫ ቦርድ “ማሟላት ይገባችኋል” የተባሏቸውን ጉዳዮች ግን ከመናገር ተቆጥበዋል። 

ፎቶ፦ ትንሣኤ 70 እንደርታ ፓርቲ

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከምርጫ ቦርድ ባገኘችው መረጃ መሰረት ግን ጠቅላላ ጉባኤው ወደ ነገ እንዲዘዋወር የተደረገው በምልዓተ ጉባኤ አለመሟላት ምክንያት ነው። በኢትዮጵያ የምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ መሰረት፤ በጠቅላላ ጉባኤ የሚሳተፉ አባላት ቁጥር ከዝቅተኛው የፓርቲ መስራች አባላት ቁጥር ቢያንስ አምስት በመቶ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል።

አንድን ክልል አቀፍ ፓርቲ ለመመስረት፤ አራት ሺህ መስራች አባላት ሊኖሩ እንደሚገባ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። የትንሣኤ 70 እንደርታ ፓርቲ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ጊደና መድሕን፤ ፓርቲው በትግራይ ክልል እና በአዲስ አበባ ከተማ አምስት ሺህ ገደማ መስራች አባላት ማስፈረሙን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ከእነዚህ መስራች አባላት ውስጥ 60 ከመቶ ያህሉ ፓርቲው በሚንቀሳቀስበት ትግራይ ክልል ነዋሪ መሆናቸውንም ተናግረዋል። 

ፓርቲው በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀስ ክልላዊ ፓርቲ ሆኖ እያለ ጉባኤውን ለምን በአዲስ አበባ እንደሚያካሄድ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ጊደና፤ “በክልሉ ጉባኤ ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታ ስለሌለ እንዲሁም ደግሞ እዚህ ብናደርገው ይበልጥ ጉባኤውን በነጻነት እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ይካሄዳል በሚል ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ከዚህ በተጨማሪም “ከአባላት በቀረበ ጥያቄ መሰረት” ጠቅላላ ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰኑን አክለዋል። 

ትሰእፓ ለነገ ባዛወረው ጠቅላላ ጉባኤው፤ የፓርቲውን ፕሮግራም እና ህገ ደንብ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። ከሁለቱ ሰነዶች መጽደቅ በኋላ የመስራች ጉባኤው አባላት፤ የፓርቲውን 15 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን እንደሚመርጡ አቶ ጊደና ተናግረዋል። ሰባት አባላት ያሉት የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር እና ጸሐፊ የሚመረጡት በማዕከላዊ ኮሚቴው መሆኑንም የፓርቲው አስተባባሪ አመልክተዋል። 

ትንሣኤ 70 እንደርታ ፓርቲ የሚያካሄደው መስራች ጉባኤ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተቀባይነት አግኝቶ የምዝገባ ሰርተፍኬት የሚያገኝ ከሆነ፤ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀስ ዕውቅና ያለው ሶስተኛው ክልላዊ ፓርቲ ይሆናል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ከምርጫ ቦርድ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው፤ በቦርዱ የምዝገባ ሰርተፍኬት ያገኙት ክልላዊ ፓርቲዎች ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲ ሉዓላዊነት ፓርቲ (ዓረና) እና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ) ብቻ ናቸው። 

ምርጫ ቦርድ በትግራይ ክልል ለሚንቀሳቀሱ ሌሎች ሁለት ክልላዊ ፓርቲዎች፤ መስራች ጉባኤያቸውን እንዲያካሄዱ ባለፈው ግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ መወሰኑን አስታውቆ ነበር። የምስረታ ጉባኤ እንዲያካሄዱ በደብዳቤ የተገለጸላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሔራዊ ባይቶ ዓባይ ትግራይ (ባይቶና) እና ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት) ናቸው።

ሁለቱ ፓርቲዎች በሀገሪቱ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት “ከቦርዱ ጋር የነበራቸው ግንኙነት መቋረጡን” እና በጦርነት ምክንያት ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ አለመቻላቸውን በመግለጽ ሂደቱ እንዲቀጥል ለቦርዱ ጥያቄ አቅርበው ነበር። ይህን ጥያቄ ተከትሎ ምርጫ ቦርድ፤ ፓርቲዎቹ “ህግን ተከትለው ለመስራት ያላቸውን አቋም የገለጹ በመሆኑ” ፓርቲዎቹን የመመዝገብ እና ፈቃድ የመስጠት ሂደቱን ለማስቀጠል መወሰኑን ከሶስት ወራት በፊት አስታውቋል። 

ከባይቶና እና ሳወት በተጨማሪ ሌሎች ስድስት ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከምርጫ ቦርድ ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ቢያገኙም፤ እስካሁን ጠቅላላ ጉባኤያቸውን በይፋ አላካሄዱም። በትግራይ ክልል ለመንቀሳቀስ ጊዜዊ ፈቃድ ያገኙት ፓርቲዎች፤ ዩኒቲ ፓርቲ፣ ራዕይ ፓርቲ፣ ዓሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ትንሳኤ ስርዓት ቃጪ ሓቂ፣ የተምቤን ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያ ፓርቲ እና ኣኽሱማይ ዋዕላ ናቸው።  

ውድብ ናጽነት ትግራይ (ውናት) የተሰኘ ሌላ ክልላዊ ፓርቲ የምዝገባ ሂደት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፤ ለሁለት ዓመት በቆየው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት “ሂደቱ ሳይጠናቀቅ” መቆሙን  ከምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ውናት ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ሂደቱን ለማስቀጠል ለምርጫ ቦርድ እስካሁን ጥያቄ አለማቅረቡም ተገልጿል። ዋና ጽህፈት ቤቱን በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ ያደረገው ውናት፤ በክልሉ በሚደረጉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አሁንም እየተሳተፈ የሚገኝ ነው።  

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ የነበረውን ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ህጋዊ ሰውነት በ2013 ዓ.ም አጋማሽ ላይ መሰረዙን ማስታወቁም አይዘነጋም። ቦርዱ የህወሓትን ህጋዊ ሰውነት የሰረዘው፤ “ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጻ ተግባር ላይ መሳተፉን አረጋግጧል” በሚል ነበር። ይህንን  የምርጫ ቦርድን ውሳኔ የተቃወመው ህወሓት፤ ጉዳዩ መታየት ያለበት በፊደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተደረገው የግጭት ማቆም ስምምነት መሰረት መሆኑን በወቅቱ አስታውቆ ነበር።

የትግራይ ክልልን ለሶስት አስርት ዓመታት ሲመራ የቆየውን የህወሓትን አስተዳደር የ“አንድ ፓርቲ ስርዓት” እና “አምባገነንነት የተንሰራፋበት” ሲል የሚኮንነው ትንሣኤ 70 እንደርታ ፓርቲ፤ ይህንኑ እንደሚታገል በፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይ አስፍሯል። በ12 ገጾች የተዘጋጀው ይኼው ፕሮግራም፤ የፓርቲውን መመስረት ግድ ያደረገው የእንደርታ ህዝብ “ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ እና ባህላዊ መብቶች አለመከበር” መሆኑን ያትታል። የእንደርታ ህዝብ በመቐለ፣ ህንጣሎ፣ ገርአልታ፣ ውቅሮ፣ ውጅራት አካባቢዎች እንደሚኖሩ የፓርቲው አስተባባሪዎች ይናገራሉ። 

ትሰእፓ በፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይ “በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች፣ ራስን በራስ የማስተዳደርና የተመጣጠነ ውክልና የተረጋገጠባት” የትግራይ ክልልን ዕውን የማድረግ አላማ እንዳለው አስፍሯል። ፓርቲው በትግራይ ክልል በሚደረግ ምርጫ ተወዳድሮ ስልጣን የሚይዝ ከሆነ፤ “የቀድሞ አውራጃዎችን መሰረት ያደረገ የዞን አደረጃጃት ተግባራዊ” እንደሚያደርግ በዚሁ ሰነዱ ላይ አስቀምጧል። የተለየ ብሔረሰባዊ ማንነት ያላቸው አካባቢዎችን “በንኡስ አውራጃ (ዞን) እንዲደራጁ” እንደሚደረግም በሰነዱ ላይ ተቀምጧል።  

ፎቶ፦ ትንሣኤ 70 እንደርታ ፓርቲ

በትግራይ ክልል “ህብረ ብሔራዊ ስርዓት እንዲፈጠር” እንደሚታገል የጠቆመው ፓርቲው፤ ይህ የማይሳካ ከሆነ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት፤ የእንደርታ ህዝብ “ከሌሎች ህዝቦች ጋር በጋራ ወይም ለብቻው”፤ “የራሱን ክልላዊ መንግስት በህዝቡ ፈቃደኝነት እንዲመሰረት” እንደሚታገል አስታውቋል። በቀድሞው የትግራይ ጠቅላይ ግዛት ስር ከነበሩት ስምንት አውራጃዎች መካከል አንዱ የእንደርታ አውራጃ እንደነበር ይታወሳል። ኢትዮጵያ በፌደራል አወቃቀር መተዳደር ከጀመረች በኋላ ደግሞ እንደርታ በትግራይ ክልል ደቡብ ምስራቅ ዞን ስር ከተካለሉ ወረዳዎች አንዱ ሆኗል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)