በባቢሌ አካባቢ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች መካከል በነበረ የተኩስ ልውውጥ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ

የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎችን በሚያዋስነው የባቢሌ አካባቢ፤ በሁለቱ ክልሎች የጸጥታ ኃይሎች መካከል መስከረም 7፤ 2016 ዓ.ም በተደረገ የተኩስ ልውውጥ፤ ቢያንስ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን እና በርካታ ሰዎች መቁሰላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። በተኩስ ልውውጡ ህይወታቸውን ያጡት ሰዎች በቆሎጂ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ እንደነበሩ ኮሚሽኑ ገልጿል። 

መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተቋም ይህን የገለጸው ዛሬ ሰኞ መስከረም 21፤ 2016 ባወጣው መግለጫ ነው። ኢሰመኮ በዚሁ መግለጫው በወቅቱ በነበረው የተኩስ ልውውጥ ከተፈናቃዮች በተጨማሪ በአካባቢው በሚኖሩ የሲቪል ሰዎች ላይ የሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን ይፋ አድርጓል። 

የመስከረም ሰባቱን ክስተት በተመለከተ ተጎጂዎችን፣ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልል የጸጥታ አካላትን፣ የቆሎጂ መጠለያ ሠራተኞችን እና የሆስፒታል ባለሙያዎችን ማነጋገሩን የገለጸው ኢሰመኮ፤ በወቅቱ በሲቪል ሰዎች ላይ ጉዳት የደረሰው “የጸጥታ ኃይሎች ተገቢ የሆነውን ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው መሆኑን” አመልክቷል። ጉዳቱ እንዲደርስ ባደረጉ የጸጥታ ኃይሎች ላይ “አስፈላጊው ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ” እና ተጎጂዎችም “እንዲካሱ” ኮሚሽኑ ጠይቋል። 

“ቀድሞውኑ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለዓመታት በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ አስቸጋሪ ህይወት ይመሩ የነበሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ለሞት እና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸው አሳሳቢ ነው”

ራኬብ መሰለ – የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ምክትል ዋና ኮሚሽነር

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ “ቀድሞውኑ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ለዓመታት በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ አስቸጋሪ ህይወት ይመሩ የነበሩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ለሞት እና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸው አሳሳቢ ነው” ሲሉ ድርጊቱን ኮንነዋል። የመንግስት የጸጥታ አካላት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚገኙባቸውን የመጠለያ ጣቢያዎች ደህንነት “አደጋ ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ተግባራት ሊቆጠቡ ይገባል” ሲሉም ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አሳስበዋል።

በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች “በአሁኑ ወቅት ግጭቱ መቆሙን” የጠቆመው ኢሰመኮ፤ ይህም ቢሆን ግን ሁለቱ ክልሎች “በቅንጅት በመስራት በአካባቢው ለተከሰተው ግጭት ምክንያት ለሆኑ ጉዳዮች ሰላማዊ መፍትሔ መስጠት” እንደሚገባቸው አመልክቷል። ክልሎቹ የአካባቢውን ነዋሪዎችን እና የተፈናቃዮችን ደህንነት በዘላቂነት የማረጋገጥ ስራ እንዲሰሩም ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል። (በተሰፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)