ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ የሚገቡት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽነር፤ ለኢትዮጵያ የ39 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ይፋ ሊያደርጉ ነው

በተስፋለም ወልደየስ

የአውሮፓ ህብረት የዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ዩታ ኡርፒላይነን ከነገ ጀምሮ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ጉብኝት ሊያደርጉ ነው። ኮሚሽነሯ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ህብረቱ ለቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የ39 ቢሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ይፋ ያደርጋሉ ተብሏል። 

በጥቅምት 2013 በትግራይ ክልል ውጊያ መቀስቀሱን ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት ጦርነቱን በተመለከተ ሲያንጸባርቀው በቆየው ጠንካራ አቋም ምክንያት በህብረቱ እና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው የሁለትዮሽ ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል። የአሁኑ የህብረቱ ኮሚሽነር ጉብኝት፤ ተቀዛቅዞ የቆየውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ቀድሞ ወደነበረበት ለመመለስ ያለመ መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች ገልጸዋል።

ሃያ ሰባት አባል ሀገራትን በስሩ ያቀፈውን የአውሮፓ ህብረትን በመወከል በኢትዮጵያ ለመጨረሻ ጊዜ ጉብኝት ያደረጉት፤ የህብረቱ የቀውስ አስተዳደር ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናርቺች ናቸው። ሌናርቺች በሰኔ 2014 ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታ በአካል መመልከት ችለዋል። በወቅቱ በድርቅ ክፉኛ የተጎዳውን የሶማሌ ክልል የጎበኙት ሌናርቺች፤ ከተረጂዎች፣ ከሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች እንዲሁም ከክልሉ ባለስልጣናት ጋር ተነጋግረዋል።

በትግራይ ክልል ተመሳሳይ ጉብኝት ያደረጉት ኮሚሽነሩ፤ ከክልሉ አመራሮች ጋር ተገናኝተዋል። የሌናርቺች የትግራይ ጉብኝት፤ በክልሉ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ በአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ባለስልጣናት የተደረገ የመጀመሪያው ይፋዊ ጉብኝት ሆኖ ተመዝግቧል። ዛሬ ሰኞ መስከረም 21፤ 2016 ምሽት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ኮሚሽነር ኡርፒላይነንም ለኢትዮጵያ እንግዳ አይደሉም። 

በታህሳስ 2011 ከአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ላየን ጋር ኢትዮጵያን ጎብኝተው የነበሩት ኮሚሽነር ኡርፒላይነን፤ በጥቅምት 2014 ዓ.ም. በድጋሚ ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል። ኮሚሽነሯ በሁለተኛ ጉብኝታቸው ከፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው የሚታወስ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በየካቲት 2014 ወደ ቤልጂየም ብራስልስ ባቀኑበት ወቅት ካገኟቸው የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ባለስልጣናት አንዷ ኡርፒላይነን ነበሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኮሚሽነሯ ጋር በነበራቸው ውይይት፤ የኢትዮጵያን እና የህብረቱን አጋርነት “ለማጠናከር በሚያስችሉ አካሄዶች ላይ” መምከራቸውን በወቅቱ ገልጸው ነበር። ኮሚሽነር ኡርፒላይነን በአሁኑ የአዲስ አበባ ጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር በድጋሚ ተገናኝተው ይወያያሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኮሚሽነሯ ከዚህም በተጨማሪ ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ እንዲሁም ከፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ጋር እንደሚነጋገሩ ጽህፈቱ ቤቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። በዚህ ወቅትም የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የ650 ሚሊዮን ዩሮ (የ39 ቢሊዮን ብር) የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት እንደሚፈረም ጽህፈቱ ቤቱ አስታውቋል። ስምምነቱ ከመጪው የፈረንጆቹ ዓመት 2024 ጀምሮ ለሶስት ዓመታት የሚቆይ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)