አይ.ኤም.ኤፍ እና ኢትዮጵያ በገንዘብ ድጋፍ ጥያቄ ላይ ከስምምነት ለመድረስ በመጪዎቹ ሳምንታት ሊወያዩ ነው

ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በጠየቀችው የገንዘብ ድጋፍ ላይ ከስምምነት ለመድረስ በሚያስፈልጉ ማሻሻያዎች ላይ በመጪዎቹ ሳምንታት ውይይት እንደሚደረግ አይ.ኤም.ኤፍ ገለጸ። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ልዑክ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በጠየቀው ድጋፍ ላይ ውይይት ማድረጉን ተቋሙ ዛሬ ሐሙስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 

የተቋሙ ልዑክ በአዲስ አበባ ቆይታ ያደረገው ከመስከረም 14 እስከ 22፤ 2016 እንደነበር መግለጫው ጠቁሟል። ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ ማሻሻያ በጠየቀችው ድጋፍ ላይ ለመወያየት ወደ አዲስ አበባ አቅንቶ የነበረውን ልዑክ የመሩት አልቫሮ ፒሪስ ናቸው። ፒሪስ ከዚህ ቀደም ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የአይ.ኤም.ኤፍ ልዑካንን በተደጋጋሚ በመምራት ልምድ ያካበቱ ናቸው። 

የልዑክ መሪው ከጉብኝታቸው መጠናቀቅ በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ የአይ.ኤም.ኤፍ ቡድን በአዲስ አበባ ቆይታው “ጉልህ የፊስካል እና የገንዘብ ቁጥጥርን ጨምሮ የዋጋ ንረትን ለማውረድ እና ኤኮኖሚውን ለማረጋጋት የተወሰዱ ጠቃሚ እርምጃዎችን” መታዘቡን ገልጸዋል። እነዚህ እርምጃዎች የኢትዮጵያን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ አቅም ወደ ተግባር ለመለወጥ ላለመው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስኬት “ወሳኝ መሰረት” ማስቀመጣቸውንም ፒርስ በመግለጫቸው አመልክተዋል።

እርሳቸው የመሩት ልዑክ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን እንዴት መደገፍ እንደሚችል ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር መወያየቱን የጠቀሱት ፒርስ፤ በዚህም “ጥሩ እርምጃ” ማስመዘገቡን አስታውቀዋል። በአዲስ አበባ የተጀመረው ውይይት በሞሮኮዋ ማራካሽ ከተማ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የአይ.ኤም.ኤፍ እና ዓለም ባንክ ዓመታዊ ስብሰባ ጎን ለጎን መቀጠሉን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት አስታውቋል። 

በዚሁ ዓመታዊ ስብሰባ እየተሳተፉ የሚገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ እና የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ፤ ከአይ.ኤም.ኤፍ  ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂየቫ ጋር ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ተገናኝተው መወያየታቸው ይፋ ተደርጎ ነበር። ጂዮርጂየቫ ከውይይቱ በኋላ በቀድሞው ትዊተር የአሁኑ ኤክስ ይፋዊ ገጻቸው ባሰፈሩት አጭር መልዕክት፤ ሁለቱ ባለስልጣናት “የኢትዮጵያን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር ለማራመድ ባላቸው ቁርጠኝነት መደነቃቸውን” ገልጸዋል። 

በዚሁ ወቅት አይ.ኤም.ኤፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው “እንዴት መደገፍ እንደሚችል” መወያየታቸውንም አክለዋል። የኢትዮጵያ  መንግስት ሁለተኛውን ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሰነድ ረቂቅ ካዘጋጀ ከስድስት ወራት በላይ ቢቆጠርም፤ ከምክክሮች በኋላ ይፋ አደርገዋለሁ ያለውን የተጠናቀቀ ሰነድ እስካሁን አላወጣም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)