በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለሞቱ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀዘን ስነ ስርዓት አከናወኑ

በትግራይ ክልል ከትላንት ቅዳሜ ጥቅምት 3፤ 2016 ጀምሮ የታወጀውን የሀዘን ቀን እና የመርዶ ስነ ስርዓት ተከትሎ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት እና ፖለቲከኞች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ህይወታቸውን ላጡ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የጸሎት እና የጧፍ ማብራት ስነ ስርዓት በዛሬው ዕለት አከናወኑ። በስነ ስርዓቱ ላይ የሰባት ሀገራዊ እና ክልላዊ ፓርቲዎች አመራሮች እና አባላት ተገኝተው ሀዘናቸውን ገልጸዋል። 

የመርሃ ግብሩ ተሳታፊዎች በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በትግራይ ክልል የደረሰው ሀዘን የጋራ መሆኑን ጠቅሰዋል። በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ህይወታቸውን ያጡ የአማራ እና የአፋር ዜጎችንም ጭምር ለማሰብ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሀዘን ቀናት ሊታወጅ ይገባ እንደነበርም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት የነበረው “የእርስ በእርስ መገዳደል” በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎች ቦታዎች መቀጠሉ የሚያሳዝን እና መፍትሔ ሊበጅለት የሚገባ እንደሆነም አሳስበዋል። 

በአዲስ አበባ ካዛንቺስ አካባቢ በሚገኘው የኢህአፓ ጽህፈት ቤት ዛሬ እሁድ ጥቅምት 4፤ 2016 በተካሄደው ስነ ስርዓት ላይ መልዕክቶቻቸውን ካስተላለፉት ውስጥ፤ የሀዘን ቀን ባታወጀበት ትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱት የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ)፣ የራያ ራዩማ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ራዴፓ) እና የትንሣኤ 70 እንደርታ ፓርቲ (ትሰእፓ) አመራሮች ይገኙበታል። የትዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ መስፍን ደሳለኝ በስነ ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ለዚህ ጉዳይ ምክንያት የሆኑ ፖለቲከኞች በሙሉ “እንደ ሰው ማሰብ መጀመር” እና “ህዝባቸውን ማገልገል አለባቸው” ብለዋል።

አቶ መስፍን አክለውም “ሁላችንም ያለፈውን መመለስ አንችልም ግን ከዚህ በኋላ የተሻለ ስርዓትን በመገንባት ህዝቡን መካስ መቻል አለብን” ሲሉ አሳስበዋል። በቅርቡ መስራች ጉባኤውን ያደረገው የትንሣኤ 70 እንደርታ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጊደና መድሕን፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለገባችበት ውድቀት ተጠያቂው ህዝቡ ሳይሆን ፖለቲከኞች መሆናቸውን በማንሳት ተችተዋል። በትግራይ የተቀሰቀሰው ጦርነት “በጥቂት ሰዎች ስህተት [የመጣ ነው]” የሚሉት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር፤ ለዚህ ተጠያቂው “የፖለቲካ ኤሊቱ” መሆኑን አስረግጠው ተናግረዋል።

በዛሬው ስነ ስርዓት ላይ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የአንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ ፓርቲ (አኢዴፓ) አመራሮችም እንዲሁ መልዕክቶቻቸውን አስተላልፈዋል። ራሳቸውን ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ያገለሉ የቀድሞ አመራሮች እና አባላት፤ በዛሬው መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው የሀዘን መልዕክቶቻቸውን አስደምጠዋል።

የመኢአዱ ሊቀመንበር  አቶ ማሙሸት አማረ “የዛሬው ቀን ምን ተብሎ እንደሚሰየም ባላውቅም፤ ትግራይ፣ አፋር፣ አማራ ላይ ላለቁት ወገኖቻችን፣ አጠቃላይ እንደ ሀገር በወደቁት ወንድሞቻችን የመከላከያ ሰራዊት ጭምር እንዳናስበው፣ የጋራ እንዳናደርገው ሌላ ደግሞ ችግር አለብን። ሌላ ችግር ውስጥ ነው ያለነው። ከአንዱ ችግር ወደ [ሌላ] ችግር ነው እንጂ፤ ከአንዱ ችግር ወደተሻለ ነገር መሸጋገር አልቻልንም” ሲሉ በስነ ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል። 

አቶ ማሙሸት በዚሁ ንግግራቸው “ይሄ ሁሉ ህይወት፣ ይሄ ሁሉ ዋጋ የተከፈለበት ዓላማው ምንድነው? ግቡ ምንድነው? በውጤቱስ ምን ተገኘ? ብለን ብናስብ፤ ምንም የለም። ዜሮ እንኳ አይሆንም” ሲሉ ተደምጠዋል። የመኢአዱ ሊቀመንበር “ክፉ” ሲሉ የጠሩትን ዘመን እና “አስተሳሰቡን” መቀየር ካልተቻለ፤ “በየተራ” ተመሳሳይ ችግር ማጋጠሙ እንደማይቀርም አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)