የአውሮፓ ህብረት እና ኢትዮጵያ የ650 ሚሊዮን ዮሮ የገንዘብ ድጋፍ ተፈራረሙ

የአውሮፓ ህብረት እና ኢትዮጵያ የ650 ሚሊዮን ዮሮ የባለብዙ ዘርፍ ዓመታዊ መርሃግብር (multi-annual indicative program)  የልማት ትብብር ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራረሙ። የገንዘብ ድጋፉ፤ ለአረንጓዴ ልማት፣ ለሰብዓዊ ልማት፣ ለመልካም አስተዳደር እና ለሰላም ግንባታ  ዘርፎች የሚውል መሆኑ ተገልጿል። 

የልማት ትብብር ስምምነቱን በአውሮፓ ህብረት በኩል የፈረሙት ትላንት ምሽት አዲስ አበባ የገቡት የህብረቱ የዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ዩታ ኡርፒላይነን ናቸው። ለአራት ዓመታት በሚቆየው በዚህ የትብብር ስምምነት ሰነድ ላይ፤ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ኢትዮጵያን ወክለው ፊርማቸውን አኑረዋል። 

ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 22፤ 2016 በአዲስ አበባው ሃያት ሪጀንሲ የተደረገው ይህ የፊርማ ስነ ስርዓት፤ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያላት የልማት ትብብር “ወደ መደበኛው የትብብር ማዕቀፍ የተመለሰበትን ሁኔታ” የሚያመላክት መሆኑን አቶ አህመድ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። “ላለፉት ሁለት ዓመታት ከአውሮፓ ህብረት ጋር ያለን የገንዘብ ትብብር በተወሰነ ደረጃ ተቀዛቅዞ ነበር” ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ “አሁን በተሟላ ሁኔታ፤ በአራት ዓመት የትብብር ማዕቀፍ፤ ከዚህ በፊት እንደነበረው በተሻለ የገንዘብ መጠን ሊያግዙን የስምምነት ሰነድ ፈርመናል” ብለዋል።  

አቶ አህመድ የዛሬው መርሃ ግብር “በአውሮፓ ህብረት እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ያለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ መሻሻሉን” ያሳየ ነው ቢሉም፤ የህብረቱ የዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ግን የአሁኑ “የመጀመሪያ እርምጃ ነው” ባይ ናቸው። የአውሮፓ ህብረት እና ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ግንኙነት ቀድሞ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚከተለው “የደረጃ በደረጃ አካሄድን” እንደሆነ ኮሚሽነሯ በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ በድጋሚ በአጽንኦት አንስተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)