የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ መንግስት መስጠት ያቋረጠውን ቀጥተኛ የበጀት ድጋፍ ለመቀጠል፤ አሁንም መሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አስታወቀ። ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ትብብር ወደ ነበረበት ለመመለስ “የደረጃ በደረጃ አካሄድን” እንደሚከተል ገልጿል።
ሃያ ሰባት አባል ሀገራትን በስሩ ያቀፈውን የአውሮፓ ህብረትን አቋም ያሳወቁት፤ የአውሮፓ ህብረት የዓለም አቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ዩታ ኡርፒላይነን ናቸው። ኮሚሽነሯ ከገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ጋር ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 22፤ 2016 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል ውይይት ካደረጉ በኋላ፤ የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያን አሁንም እንደ “ስትራቴጂካዊ አጋር” እንደሚመለከታት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የአውሮፓ ህብረት እና የኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት፤ በጥቅምት 2013 በትግራይ ክልል ከተቀሰቀሰው ጦርነት ወዲህ ተቀዛቅዞ ቆይቷል። ህብረቱ በጦርነቱ ምክንያት ለኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጠውን 90 ሚሊዮን ዩሮ ከሚጠጋው የበጀት ድጋፍ ማገዱ ይታወሳል። ከዚህም በተጨማሪ በተመሳሳይ ምክንያት ለኢትዮጵያ ያዘጋጀውን አንድ ቢሊዮን ዩሮ የልማት እርዳታ ሳይያጸድቅ ቀርቷል።
ህብረቱ የባለብዙ ዘርፍ ዓመታዊ ድጋፍ (multi annual indicative program) በተሰኘው ማዕቀፉ፤ ለኢትዮጵያ የ650 ሚሊዮን ዮሮ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት እንደሚሰጥ ኮሚሽነር ኡርፒላይነን ዛሬ ይፋ አድርገዋል። የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጠውን ቀጥተኛ በጀት እንደገና ለመልቀቅ አስቦ እንደው ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው ኮሚሽነሯ፤ ይህ የገንዘብ ድጋፍ ከመደረጉ በፊት በኢትዮጵያ በኩል መሟላት የሚገባቸው “ፖለቲካዊ ሁኔታዎች” እንዳሉ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)